ኦነግ ሰፊ የኦሮሞ ምክክር መድረክ እንዲካሄድ ጥሪ አቀረበ

በተስፋለም ወልደየስ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሁሉን ያቀፈ እና አሳታፊ የሆነ ሰፊ የኦሮሞ ምክክር መድረክ  (broad based Oromo national dialogue) እንዲካሄድ ጥሪ አቀረበ። ፓርቲው ሰኞ ነሐሴ 4፤ 2012 በሂልተን ሆቴል በሰጠው መግለጫ፤ ውይይቱን የማካሄጃ “ጊዜው አሁን ነው” ብሏል። 

ውይይቱ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኦሮሞ ልሂቃን፣ አክቲቪስቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የእምነት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም አራማጅ ድርጅቶች (civic organizations) እና ቄሮና ቀሬን ያሳተፈ እንዲሆን ጠይቋል። በውይይቱ ላይ የኦነግ ነባርና መስራች አባላት፣ የቀድሞ የኦነግ አባላት እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ከድርጅቱ የራቁ፣ ከድርጅቱ ጋር ትስስር ያላቸውና ግዴታቸውን የተወጡ እና በመወጣት ላይ ያሉ አባላትን ያቀፈ መሆን እንዳለበት ጠቁሟል።

ኦነግ በዛሬው መግለጫው 600 አባላቱ በእስር ላይ እንዳሉ አስታውቋል። የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ “ንጹህ የሆኑ ሰዎች በጅምላ የታሰሩበት ሁኔታ አለ” ሲሉ አብዛኞቹ አባሎቻቸው ተጠርጥረው በታሰሩበት ጉዳይ እጃቸው እንደሌለበት ተናግረዋል። ይህንኑ አባባል የኦነግ ቃል አቃባይ ቶሌራ አዳባም አስተጋብተዋል። 

አንዳንዶቹ አባላቶቻቸው በኦነግ- ሸኔ አባልነት ተወንጅለው መታሰራቸውን ያነሱት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው “ABO- ሸኔ የሚባለውን እንደ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር አናውቀውም። እንደዚህ አይነት ድርጅትም የለም” ሲሉ በፓርቲው ላይ የሚቀርበውን ውንጀላ ሞግተዋል። 

በዛሬው የኦነግ መግለጫ ላይ ከአቶ ቀጄላ እና አቶ ቶሌራ በተጨማሪ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሳ ቢቂላ ተገኝተው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል። የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከሰሞኑ ከቤታቸው ውጭ እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ እንደተጣለባቸው ሲነገር መቆየቱን ያነሱት ጋዜጠኞች ሊቀመንበሩ አሁን ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ጥያቄ አቅርበው ነበር። 

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ “የአቶ ዳውድን ስልክ እኛ ማግኘት አልቻልንም።  መጀመሪያ ስንገናኝበት የነበረው ስልክ ዝግ ነው። አንድ፣ ሁለት ስልኮች የማውቃቸው፤ በየቀኑ የምንገናኝበት [አሁን] የሉም። ሚዲያዎች ግን ቢቢሲም፣ ቪኦኤም አልፎ አልፎ የሚያነጋግራቸው ይመስለኛል። በዚያ በኩል እናንተም ፈልጋችሁ፤ ከእርሳቸው ከአፋችሁ ብትሰሙ የተሻለ ይሆናል” ብለዋል። 

“ባለፈው ጊዜ ‘ቤት ታጉረዋል፣ ለደህንነታቸው ተብሎ ነው፣ እንደዚህ ነው’ ተብሎ ነበር እኛ የሰማነው ከእርሳቸው አንደበት። ኋላ ግን መንግስት ‘መንግስት ቤት አጉሯቸዋል’ ብላችኋል ተብለንም ተወቅሰናል” ሲሉ ሊቀመንበሩ ራሳቸው ቢናገሩ ይሻላል ያሉበትን ምክንያት አስረድተዋል።    

የኦነግ ሊቀመንበር በሌሉበት በቅርቡ የተካሄደው የኦነግ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ፤ በአቶ ዳውድ ተቀባይነት አለማግኘቱን የተመለከተ ጥያቄም በጋዜጠኞች ተነስቶ ነበር።  የፓርቲው ቃል አቃባይ አቶ ቶሌራ ስብሰባው በፓርቲው ደንብ መሰረት መከናወኑን ገልጸዋል።

“እርሳቸው የራሳቸው ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል። እኛ የምንለው ግን ‘ሊቀመንበሩ በሌለበት ቦታ ምክትል ሊቀመንበሩ ተክቶ ይሰራል’ የሚል ደንብ አለን፤ በዚያ መልክም ነው የሄድነው። እስከ መጨረሻ ሰዓትም እውቅና ነበረው።  ለምን እንዳሉ ግን ኧእርሳቸው የበለጠ ቢያብራሩ ይሻላል” ሲሉ አቶ ቶሌራ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

ሊቀመንበርን በምክትል ሊቀመንበር ተክቶ ዕለታዊ ስራዎችን መተግበር፤ በድርጅታቸው ብቻ ሳይሆን በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በማንኛውም ድርጅት የተለመደ አሰራር መሆኑን አቶ ቶሌራ ጠቁመዋል። ጉዳዩም “ምንም አከራካሪ አይመስለኝም” ብለዋል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)