የኦሞ ወንዝ ባስከተለው የውሃ መጥለቅለቅ 15 ሺህ ሰዎች ተፈናቀሉ

በተስፋለም ወልደየስ  

በደቡብ ክልል የሚገኘው የዳሰነች ወረዳ በኦሞ ወንዝ ውሃ በመጥለቀለቁ፤ 15 ሺህ ገደማ ሰዎች መፈናቀላቸውን የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች መምሪያ አስታወቀ። ወንዙ ባስከተለው ጎርፍ 15 ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በሌሎች ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱንም ገልጿል። 

የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ለማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት የኦሞ ወንዝ ላስከተለው የውሃ መጥለቅለቅ መንስኤው፤ የግልገል ጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ግድብ ከመጠን በላይ በመሙላቱ የተለቀቀ ውሃ ነው። በዚህም ምክንያት በዳሰነች ወረዳ ከሚገኙ 40 ቀበሌዎች ውስጥ ሃያ ስምንቱ በዚህ ሳምንት በወንዙ መጥለቅለቃቸውን አስረድተዋል።

በዳሰነች ወረዳ በውሃ የተከበቡ 16 ደሴቶች እንዳሉ የሚገልጹት ኃላፊው ቀደም ብሎ በተከናወኑ የነፍስ አድን ስራዎች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ማትረፍ መቻሉን አስረድተዋል። ውሃ እንደሚለቀቅ ቀደም ብሎ መረጃ በመገኘቱም እስካሁን ድረስ በጎርፍ ምክንያት የሰውም ሆነ የእንስሳት ሞት አለመከሰቱን አብራርተዋል።    

ፎቶ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት

“የጊቤ ሶስት ቅድመ ማስጠንቀቂያ [ቡድን] እዚህ እኛ ጋር መጥተው ተወያይተው ነበር። ውሃው ሞልቶ ሊፈስ ስለሚችል በዚህ አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦችን እንድናነሳ መልዕክት ሰጥተውን ነበር። በዚያ አካባቢ የሚኖር የዳሰነች ማህበረሰብ አለ። ስለዚህ እነርሱን የማውጣት ስራ እየሰራን ነበር። እስካሁን ድረስ ከ15,195 በላይ ሰዎች አውጥተናል” ሲሉ አቶ መላኩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ኤልሬት በተባለ ቦታ ሰፍረው ከሚገኙ ከእነዚህ ተፈናቃዮች በተገኘ መረጃ፤ አሁንም ከ150 እስከ 200 የሚሆኑ ሰዎች በደሴቶች ላይ በውሃ ተከብበው እንዳሉ መረጃ መገኘቱን አቶ መላኩ ጠቁመዋል። የነፍስ አድን ስራው እስካሁን ሲከናወን የቆየው በአካባቢው አገልግሎት ላይ የሚወሉ የእንጨት ጀልባዎችን እና ከደቡብ ክልል ለዚሁ ተብሎ የተላኩ የሞተር ጀልባዎችን በመጠቀም ነበር ያሉት ኃላፊው፤ ቀሪዎቹ ሰዎች አሉበት የተባለው ቦታ በጀልባ እንኳ የማይደረስበት እንደሆነ አመልክተዋል።    

በውሃ ተከብበው ያሉትን እነኚህን ሰዎች በሄሌኮፕተር ለማውጣት ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ መቅረቡን የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር አስታውቋል። አቶ መላኩ የተጠየቀው ሄሌኮፕተር ነገ ሰኞ ነሐሴ 11፤ 2012 ወደ አካባቢው ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። በሄሌኮፕተሩ አማካኝነት ከሚደረግ ቅኝት በኋላ፤ ሰዎቹን አሉበት ከተባለበት የኬንያ ድንበር እና ቱርካና ሀይቅ አቅራቢያ የማውጣት ስራ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።    

በውሃ መጥለቅለቅ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች፤ ከኦሞራቴ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ ደረቃማ አካባቢ ላይ በጊዜያዊነት ሰፍረው እንደሚገኙ ተነግሯል። የዞኑ የአደጋ እና ስራ አመራር ቢሮ ለተፈናቃዮቹ የዕለት ደራሽ እርዳታ እያቀረበ ቢገኝም ተጨማሪ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉም ተጠቁሟል። ሌላው ለዞኑ ኃላፊዎች አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ከግልገል ጊቤ ግድብ በሁለተኛ ዙር የተለቀቀው ውሃ ነው። ከቀናት በፊት የተለቀቀው ውሃ ዛሬ አካባቢያቸው ላይ መድረሱን የሚናገሩት የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች መምሪያ ኃላፊ፤ የውሃው ከፍተኛ መጠን ደረቃማዎቹንም ስፍራዎች እንዳያጥለቀልቅ አስግቷቸዋል።  

ኦሞ ወንዝ ፎቶዎች፦ የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች መምሪያ

የኦሞ ወንዝ ያስከተለው ጎርፍ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ እስካሁን ጥረት ቢደረግም በ873 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ማሽላ፣ በቆሎ እና ሙዝ እርሻዎች በጎርፉ መውደማቸውን አቶ መላኩ አስታውቀዋል። ጎርፉ ከዚህ በተጨማሪ በዘጠኝ መደበኛ እና ስድስት አማራጭ ትምህርት ቤቶች፣ ሶስት የጤና ኬላዎች፣ የእንስሳት ጤና ጣቢያዎች እና የመስኖ ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሱን ዘርዝረዋል።   

በዳሰነች ወረዳ ባለፉት ቀናት ሲከናወን የቆየው የነፍስ አድን ስራ የአካባቢው ማህብረሰብ ሁነኛ መተዳደሪያ የሆኑትን እንስሳትን የጨመረ ነበር። በዚህም 97 ሺህ እንስሳትን ከየቦታው ማውጣት መቻሉን የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች መምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ 20 ሺህ ያህሉ የሚያጠቡ እንስሳት በመሆናቸው አፋጣኝ የሆነ የእንሳስት መኖ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። 

የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ባለፈው ግንቦት ወር ባወጣው ማሳሰቢያ፤ በሐምሌ እና ነሐሴ ወራት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ እና በመካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር። የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (OCHA) ባለፈው ሳምንት ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዚህ ዓመት የክረምት ወራት በሚከሰቱ ድንገተኛ ጎርፎች እና የወንዝ ሙላቶች ሁለት ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ይጠቃሉ ተብሎ ተገምቷል። ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ በአፋር፣ በጋምቤላ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች በተከሰተ ጎርፍ 30 ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የOCHA ሪፖርት ይፋ አድርጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)