የወላይታ የማህበረሰብ ሬድዮ ወደ ስርጭት ተመለሰ

በጸጥታ ኃይሎች ትዕዛዝ ካለፈው አርብ ነሐሴ 8፤ 2012 ጀምሮ ስርጭቱን አቋርጦ የነበረው የወላይታ ዎጌታ የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያ ከዛሬ ሰኞ ማለዳ ጀምሮ መደበኛ ዝግጅቱን ማስተላለፍ ጀመረ። ጣቢያው ስራውን የጀመረው የጸጥታ ሁኔታ እየተቆጣጠረ ከሚገኘው ኮማንድ ፖስት ኃላፊዎች ጋር ከተደረገ ውይይት በኋላ ነው ተብሏል።

በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በተደረገው ውይይት የራዲዮ ጣቢያው የስራ ኃላፊዎች፣ የወላይታ የሀገር ሽማግሌዎች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን የራዲዩ ጣቢያው አስታውቋል። ራዲዮ ጣቢያው ባለፈው አርብ ስርጭቱን ለማቋረጥ የተገደደው፤ ማሰራጫ ስቱዲዩው ወደሚገኝበት የጉተራ አዳራሽ ግቢ የገቡ የታጠቁ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሰጡት ትዕዛዝ እንደነበር የጣቢያው ጋዜጠኞች ገልጸው ነበር።

የወላይታ ዎጌታ ራዲዮ ጣቢያ ከታህሳስ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በወላይትኛ እና አማርኛ ቋንቋዎች የተለያዩ ፕሮግራሞችን ሲያሰራጭ የቆየ ጣቢያ ነው። ጣቢያው በ96.6 ሜጋ ኸርዝ ኤፍ ኤም የአየር ሞገድ የሚያስተላልፈው የ15 ሰዓታት ስርጭት በወላይታ ዞን ያሉ አብዛኛዎቹን አካባቢዎች የሚሸፍን ሲሆን በአካባቢው ባሉ ሌሎች የደቡብ ክልል ዞኖችም ይደመጣል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)