የቢሾፍቱ ከተማ ፍርድ ቤት አቶ ልደቱ አያሌው ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

የኦሮሚያ ፖሊስ በኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል በሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ላይ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በፍርድ ቤት ተፈቀደለት። የክልሉን ፖሊስ ጥያቄ በዛሬ ረፋድ የችሎት ውሎው የተመለከተው የቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሰባት የምርመራ ቀናትን መፍቀዱን የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ ባለፈው ሳምንት ሰኞ በነበረው ችሎት ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ ለዛሬ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አዳነ ሆኖም ፖሊስ በዛሬው የችሎት ውሎም “ምርመራዬን አልጨረስኩም” በማለት ተጨማሪ 14 ቀናት መጠየቁን ገልጸዋል። በዛሬው የችሎት ውሎ የተሰየሙት አዲስ ዳኛ “ለመጨረሻ ጊዜ” ተብሎ የተሰጠውን ትዕዛዝ ወደ ጎን በማድረግ ተጨማሪ ሰባት የምርመራ ቀናት መፍቀዳቸውንም አብራርተዋል። 

በችሎቱ አዲስ ዳኛ ሲሰየም የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን የሚያስረዱት የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ይህንኑ ጉዳይ በመቃወም በአቶ ልደቱ ጠበቃ አማካኝነት በዛሬው ችሎት አቤቱታ መቅረቡን ጠቁመዋል። በኦሮሚያ ክልል ፍቃድ ያለው ጠበቃ ለማግኘት ተቸግረው የነበሩት አቶ ልደቱ፤  በነጻ ጥብቅና ለመቆም ፍቃደኝነታቸውን ከገለጹላቸው ጠበቆች በአንዱ ዛሬ መወከላቸውንም አመልክተዋል።  

“ጠበቃው አዲስ ዳኛ በየጊዜው መሾሙ፤ ጉዳዩን እንደ አዲስ ጥሬ ለማድረግ ሆን ተብሎ የሚደረግ እርምጃ ነው የሚል ቅሬታ አቅርበዋል”

አቶ አዳነ ታደሰ- የኢዴፓ ፕሬዝዳንት

“[ጠበቃው] አዲስ ዳኛ በየጊዜው መሾሙ፤ ጉዳዩን እንደ አዲስ ጥሬ ለማድረግ ሆን ተብሎ የሚደረግ እርምጃ ነው የሚል ቅሬታ አቅርበዋል። ግን እንደሚታወቀው እስሩም ፖለቲካዊ ስለሆነ በህግ ስርዓቱ የሚመጣ ለውጥ ይኖራል ብለን አናስብም” ይላሉ አቶ አዳነ።

በፍትህ ስርዓቱ ላይ “እንደ ፓርቲ ተስፋ መቆረጣቸውን” የሚገልጹት የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ለዚህም በዛሬው ችሎት የነበረ አንድ ሂደትን በማሳያነት ጠቅሰዋል። የልብ ህመም እንዳለባቸው እና ለዚሁ ህመም በአሜሪካን ሀገር ለሚያደርጉት ክትትል ለመሄድ በመዘጋጀት ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከዚህ ቀደም በነበሩ ችሎቶች የገለጹት አቶ ልደቱ፤ የህክምና ቀጠሯቸውን ለፍርድ ቤቱ አስገብተው እንደነበር አቶ አዳነ አስታውሰዋል። 

“ከዚህ በፊት ፍርድ ቤቱ የህክምና ማስረጃ እንዲያቀርብ ጠይቆት፤ ከህክምና ተቋም ያለበት የልብ ህመም ለኮሮና ተጋላጭ እንደሚያደርገው፣ አደጋ ውስጥ እንደሆነ በሚል ደብዳቤ አስገብቶ ነበር። እርሱንም ፍርድ ቤት ሊቀበል አልቻለም” ብለዋል። አቶ ልደቱ በዛሬው የችሎት ውሎ፤ ከምንጊዜውም በተለየ ሁኔታ በነስር እየተቸገረ መሆኑን እንደነገራቸው እና እስካሁንም ወደ ህክምና አለመወሰዱን ለፍርድ ቤቱ ጭምር መግለጹን አስረድተዋል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ ይህንን ጉዳይ ችላ በማለት ለነሐሴ 18 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ተችተዋል።

አቶ ልደቱ በፌደራል ፖሊስ አባላት አማካኝነት በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ወደ ቢሾፍቱ ከተማ የተወሰዱት ሐምሌ 17፤ 2012 ነበር። ዕውቁ ፖለቲከኛ ሰኔ 23 እና 24፤ 2012 በቢሾፍቱ ከተማ የተቀሰቀሰውን ሁከት በማስተባበር እና በገንዘብ በመደገፍ መጠርጠራቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጾ ነበር። አቶ ልደቱ በቢሾፍቱ ከተማ የመኖሪያ ቤት ያላቸው ሲሆን በከተማይቱ ሁከት መቀስቀሱን ተከትሎ በፖሊስ ማሳሰቢያ መሰረት በአዲስ አበባ እንዲቆዩ መደረጋቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)