ታከለ ኡማ ከስልጣናቸው ተነሱ

በተስፋለም ወልደየስ

የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ ሆነው ለሁለት ዓመት ሲያገልግሉ የቆዩት ታከለ ኡማ ከስልጣናቸው ተነሱ። ምክትል ከንቲባው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካኝነት የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። 

ከዛሬው ሹም ሽር ጋር ይገናኝ እንደው በግልጽ ባይነገርም የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 12፤ 20102 አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚያካሄድ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የምክር ቤቱም አጀንዳ በይፋ አልተገለጸም።  

አቶ ታከለ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሹመት ተከትሎ በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “አዲስ አበባን መምራት ትልቅ ዕድል ነው። ደጋግመን እንደምንለው፤ ‘በታሪክ አጋጣሚ ያገኘነውን እድል’ ላለማባከን ጥረናል” ሲሉ ጽፈዋል። አዲስ አበባን በሚመሩበት ጊዜ ላገዟቸው ልባዊ ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ከንቲባው “በፍጹም ቅንነት ላጎደልናቸው ነገሮችም ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል። 

ታከለ ኡማን ይተካሉ ተብሎ ከፍተኛ ግምት ሲሰጣቸው የቆዩት እና ከወራት በፊት ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሆነው የተሾሙት አዳነች አቤቤ በምክትላቸው ጌድዮን ጢሞቴዎስ መተካታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይፋ ካደረጉት የሹመት ዝርዝር መረዳት ተችሏል።

በአዲስ አበባ መስተዳድር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ሆነው ሲሰሩ የቆዩት እንዳወቅ አብቴም በዛሬው ሹም ሹር ከተካተቱ አስር ባለስልጣናት አንዱ ሆነዋል። አቶ እንዳወቅ የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)