በተስፋለም ወልደየስ
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 12፤ 2012 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ አዳነች አቤቤን ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾመ። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ስልጣናቸውን ዛሬ የለቀቁት አዳነች፤ የአዲስ አበባ ከተማን ለመምራት ቃለ መኃላ ፈጽመዋል።
በዛሬው የከተማይቱ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ከተገኙ 85 የምክር ቤት አባላት መካከል 77 አባላት አዳነች አቤቤ ምክትል ከንቲባ ሆነው እንዲሾሙ ድጋፍ ሲሰጡ፤ 6 አባላት ተቃውመዋል። ሁለት አባላት ደግሞ ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል።
አዳነች ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳሪነት የመጡት ለሁለት ዓመታት ከተማይቱን በምክትል ከንቲባነት ሲመሩ የቆዩት ታከለ ኡማ ዛሬ ረፋዱን ከስልጣናቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ነው። ታከለ የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስትር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሾማቸው የተገለጸው ዛሬ ረፋዱን ነበር።
ከቀኑ አስር ሰዓት ገደማ በተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ፤ ተሰናባቹ ምክትል ከንቲባ ታከለ የከተማይቱን ቁልፍ ለአዲሲቷ ተሿሚ አስረክበዋል። አዳነች የርክክብ ስነ ስርዓቱን ተከትሎ ለምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር፤ የትኩረት አቅጣጫዎቻቸውን ይፋ አድርገዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በጅምር ላይ ያሉ ስራዎች ብዙ መሆናቸውን የጠቆሙት ምክትል ከንቲባዋ “እነዚህን ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ማጠናቀቅ እና ከግብ ማድረስ አንዱ እና ዋነኛው ትኩረታችን ይሆናል” ብለዋል። በመዲናይቱ ባሉ የመሰረተ ልማት፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የመጠጥ ውሃ፣ ጽዳት እና ደህንነት ዘርፎች “እመርታዊ ለውጥ” እንዲመጣ ተግተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚማረሩበትን የአገልግሎት አቅርቦት ጉዳይን በንግግራቸው ያነሱት ምክትል ከንቲባዋ “በአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና እና ፍትሃዊነት ዋና መርሆአችን አድርገን የምንሰራ ይሆናል” ብለዋል። “በአገልግሎት አሰጣጥም ሆነ የከተማዋን እና የሀገርን ሀብት ማስተዳደር ግልጽ የሆነ አሰራር፣ ከሀብት ብክነት የጸዳ፣ ምዝበራን ያስወገደ፣ በታማኝነት እና በቅንነት ላይ የተመረኮዘ እንዲሆንም ተግተን የምንሰራ ይሆናል” ሲሉ ለከተማይቱ ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።
አዳነች በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩባቸው በንግግራቸው ከዘረዘሯቸው ጉዳዩች መካከል “የከተማ ድህነት ማስወገድ፣ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር፣ የከተማዋን ማህበራዊ ዋስትና ማዕቀፎች ማስፋፋት እና ማጠናከር እንደዚሁም በከተማዋ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት መፍታት” የሚሉ ይገኙበታል።
ምክትል ከንቲባዋ በዛሬው የምክር ቤት ስብሰባ፤ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ሲሰሩ በቆዩት እንዳወቅ አብቴ ምትክ አዲስ ተሿሚ አቅርበው በሙሉ ድምጽ አጸድቀዋል። እንዳወቅን ተክተው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ሆነው የተሾሙት ዣንጥራር አባይ ናቸው።
አዲሱ ተሿሚ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካሪም ነበሩ። ከአዲስ አበባ ከተማ ስልጣናቸው የተነሱት አቶ እንዳወቅ፤ የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መሾማቸውን ጽህፈት ቤታቸው ዛሬ ረፋዱን አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[ይህ ዘገባ ዘግየት ብሎ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]