በተስፋለም ወልደየስ
በኦሮሚያ ክልል በ13 ከተሞች በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ቁጥራቸው በወል ያልታወቀ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። ኮሚሽኑ የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ጥሪውን አቅርቧል።
ኮሚሽኑ ይህን ያለው በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ቀናት በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ስለደረሱ የሞት እና እና የአካል ጉዳቶች በተመለከተ ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 14፤ 2102 ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ኮሚሽኑ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የደረሱትን መረጃዎች በመጥቀስ እንዳስታወቀው በክልሉ 13 ከተሞች ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ላይ “የሞት ጉዳት” ደርሷል። ከከተሞቹ መካከል የምስራቅ ሀረርጌዎቹ አወዳይ፣ ሀሮማያ፣ ደንገጎ እና በምዕራብ ሀረርጌ ስር የሚገኙት ሂርና፣ ገለምሶ፣ ጭሮ፣ አሰቦት ይገኙበታል።
የሞቱት ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ ስለመገደላቸው በግልጽ ያላስቀመጠው መግለጫው፤ በተቃውሞ ሰልፎቹ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱም እንዲሁ በቁጥር ከመግለጽ ተቆጥቧል። በመገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ የትስስር ገጾች የወጡ መረጃዎች የተለያዩ አሀዞችን ማስቀመጣቸውን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ በራሱ በኩል ማጣራት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
“ሰኞ እና ማክሰኞ በነበሩ ሰልፎች ቆስለው በሐረር ሕይወት ፋና ሆስፒታል ህክምና እያገኙ ያሉ ሰዎች ብዛት 26 ነው”
በሕይወት ፋና ሆስፒታል የሚሰሩ የህክምና ባለሙያ
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው በሐረር ሕይወት ፋና ሆስፒታል የሚሰሩ የህክምና ባለሙያ፤ ሰኞ እና ማክሰኞ በነበሩ ሰልፎች ቆስለው በሆስፒታላቸው ህክምና እያገኙ ያሉ ሰዎች ብዛት 26 ነው ብለዋል። በጥይት እና በዱላ ድብደባ ቆስለው ወደ ሆስፒታላቸው ከመጡ ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ አራቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል። በጥይት የተመቱ ሁለት ሰዎች ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ወደ ሆስፒታል ይዘዋቸው እንደመጡም አክለዋል።
ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው ህግ አስከባሪዎች ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ አሳስቧል። የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ እና ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ “የመንግስት አካላት የዜጎችን በሰላማዊ መልኩ ተቃውሞ የማሰማት መብት ማረጋገጥ እንዳለባቸው እና ሕግ የማስከበር ስራ ተመጣጣኝነት እንዲጠብቅ ማድረግ ኧእንደሚጠበቅባቸው” አስገንዝበዋል።
“የኦሮሚያ ክልል በዚህ አመት የተከሰቱ አሳዛኝ ግድያዎች ከፈጠሩት ሰቆቃ አሁንም ፈጽሞ አላገገመም” ያሉት ቃል አቃባዩ “እነዚህ ከፍተኛ የመብት ጥሰት አዝማሚያዎች እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው አይገባም” ሲሉ የኮሚሽኑን አቋም አስታውቀዋል።
የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ በተጠሩ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን ለማጣራት የፌዴራል እና የክልል መንግስታት “በአፋጣኝ ምርመራ እንዲጀምሩ” ኢሰመኮ ጠይቋል። ኮሚሽኑ የደረሰውን የሞት እና የአካል ጉዳት መጠን ለማጣራት ከተለያዩ አካላት መረጃ እያሰባሰበ እንደሆነ በመግለጫው ጠቅሷል። የመረጃ ማሰባሰቡ ከየአካባቢውን ነዋሪዎች፣ የአይን ምስክሮች፣ ሆስፒታሎች እና የአስተዳደር አካላትን ያካተተ እንደሆነም አመልክቷል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በኮሚዩኒኬሽን ቢሮው በኩል ምሽቱን ባወጣው መግለጫ ግን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን “በማህበራዊ ሚዲያ የሚነዙ የፕሮፓጋንዳ መልዕክቶችን እንደ መረጃ ምንጭ ተጠቅሟል” ሲል ወንጅሏል። ይህ አይነቱ አካሄድም “የተሳሳተና መታረም ያለበት ጉዳይ ነው” ሲል ክልሉ አቋሙን ግልጽ አድርጓል።
ኮሚሽኑ “ትልቅ ሀገራዊ ተቋም እንደመሆኑ እውነተኛ እና የተጣራ መረጃ ማቅረብ ይገባው ነበር” ያለው የክልሉ መንግስት፤ ይህንንም ለማድረግ “ችግር ተከስቶባቸዉ በነበረባቸው አካባቢዎች በአካል ተገኝቶ ተጨባጭ መረጃዎቸን በማሰባሰብ፣ በየደረጃዉ ያለውን የመንግስት አመራር መጠየቅ” ይችል እንደነበር ጠቁሟል። ሆኖም ተቋሙ ዛሬ ያወጣው መግለጫ “የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸዉ የነበሩ አካባቢዎችን እውነታ ያላገነዘበ እና ከእውነት የራቀ ነው” በማለት ተችቶታል።
“የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጸጥታ አስከባሪ አካላት የህግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ የሚኮንን፣ ሚዛናዊ ያልሆነ እና ከእውነታ የራቀ፣ በወቀሳ የተሞላ መግለጫ ማውጣቱ ተገቢነት የሌለውና ካንድ ኃላፊነት ከሚሰማው ተቋም የሚጠበቅ አይደለም” ብሏል የኦሮሚያ ክልል መንግስት።
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል “12/12/12” በሚል መለያ ስያሜ በአክቲቪስቶች የተጠራውን ተቃውሞ ክልሉ መንግስት “የጥፋት ድግስ” ሲል በመግለጫው ጠርቶታል። ተቃውሞውም “ሰላማዊ ሰልፍ ሳይሆን የሁከት እና የብጥብጥ ሰልፍ ነበር” ሲል ወንጅሏል። የጸጥታ አካላት የወሰዷቸው እርምጃዎች “ህዝቡን የማዳን፣ ሕገ መንግስቱን የመከላከል፣ የህግ የበላይነት የማስከበር ኃላፊነት” እንደሆኑም መግለጫው አትቷል። የጸጥታ ኃይሎች እርምጃዎችን ሲወስዱ “ከተጠያቂነት ማዕቀፍ ጋር በማገናዘብ” እንደሆነም አመልክቷል።
የክልሉ መንግስት የደረሰዉን ጉዳት መነሻና መድረሻ ለማረጋገጥ ለፈለገ ማንኛዉም ኃላፊነት ለሚሰማው አካል የተሟላ መረጃ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል። ጉዳዩን በገለልተኝነት ለማጣራት ለሚፈልግ ለእንዲህ አይነት አካልም ሂደቱን ለመደገፍ ቃል ገብቷል። የአሮሚያ ክልል መንግስት “የተፈጠሩ ስህተቶች ካሉ ለማረም ዝግጁ” መሆኑንም አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[ይህ ዘገባ ከተጠናቀረ በኋላ የወጣው የኦሮሚያ ክልል መንግስት መግለጫ በስተኋላ ላይ ተጨምሮበታል]