የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ መግባባት ላይ ነገ ውይይት ያደርጋሉ

በተስፋለም ወልደየስ

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ መግባባት ላይ ነገ ቅዳሜ ነሐሴ 16፤ 2012 ውይይት ሊያደርጉ ነው። በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በሚካሄደው በዚህ ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ይገኛሉ ተብሏል። 

በነገው ውይይት ሶስት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጥናታዊ ጽሁፍ እንደሚያቀርቡ መርሃ ግብሩን ያሰናዳው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታውቋል። የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት በነገው ውይይት ጥናታዊ ጽሁፍ የሚያቀርቡት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እና የኦሮሞ አቦ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር ሻምበል አማን ኦስማን ናቸው። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፌስ ቡክ ገጽ 

የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ ከ20 ገጽ ያልበለጡ ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን ለመርሃ ግብሩ አዘጋጆች ከቀናት በፊት ማስገባታቸውን ምንጮች ገልጸዋል። የፕሮፌሰር መረራ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ያዘጋጁት “በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሀገር ግንባታ ታሪካዊ ዳራ” በሚል ርዕስ ሲሆን አቶ የሺዋስ በበኩላቸው “ሕገ መንግስት እና ሕገ መንግስታዊነት ለብሔራዊ መግባባት” ያለውን ሚና በጥናታዊ ጽሁፋቸው ዳስሰዋል። የሶስተኛው አቅራቢ ሻምበል አማን ጥናት የሚያጠነጥነው በዘመናዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ላይ ነው። ጥናቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት፣ ችግሮቻቸው እና ለብሔራዊ መግባባት ያላቸው ሚናን ይተነትናል። 

ሶስቱ ጥናት አቅራቢዎቹ የተመረጡት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ባለፈው ሐምሌ 22፤ 2012 ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በጽህፈት ቤታቸው በተወያዩበት መድረክ ነበር። ከብሔራዊ መግባባት ጋር በተያያዙ ርዕሶች ላይ ለውይይት የሚሆኑ የጥናት ጽሁፎች እንዲያዘጋጁ ከተመረጡ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ውስጥ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶ/ር አብዱልቃድር አደም፣ ዶ/ር አለሙ ስሜ እና አቶ ጣሂር መሐመድ ይገኙበታል። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደው ስብሰባ ሌሎች ሶስት አመራሮችም ቀጣይ ውይይቶችን እንዲያስተባብሩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። የማስተባበሩን ኃላፊነት የተረከቡት የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም እና ምክትላቸው አቶ ግርማ በቀለ ናቸው። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፌስ ቡክ ገጽ 

በርከት ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በታሰሩበት እና በኢትዮጵያ ተደራራቢ ችግሮች በሚስተዋሉበት በዚህ ጊዜ፤ እንዲህ አይነት ውይይት ማካሄዱ ለውጥ ያመጣ እንደው የተጠየቁት አቶ ሙሳ “ለውጥ ያመጣል ብለን እናስባለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ደግሞ “አንደኛ ያው በሀገር ላይ አለመግባባቶች ሊኖሩ ይችላሉ ግን ተስፋ አንቆርጥም። ስለዚህ አሁንም የሚጠበቀው አንዱ ተስፋ ነው” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የሚዘጋጁ እንዲህ አይነት መድረኮች ወይ የመንግስት ፍላጎት አሊያም ቁጥጥር የሚንጸባረቅባቸው እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ሙሳ የነገው ውይይት ግን ዋናው ስራ የተሰራው “የሁሉም ውክልና ባለው አካል ነው” ሲሉ የመርሃ ግብሩ ዝግጅት የሚለይበትን ምክንያት ጠቁመዋል። በነገው ውይይት ላይ የተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችን ጨምሮ 150 ገደማ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)