የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይሎች ነገ በይፋ ሊመረቁ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

ከደቡብ ክልል ተነጥሎ ባለፈው ሰኔ ወር በይፋ የተቋቋመው የሲዳማ ክልል፤ የራሱን ልዩ ኃይል አባላት በነገው ዕለት ሊያስመርቅ ነው። ተመራቂዎቹ ቀደም ሲል በደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ሲያገልግሉ የነበሩ የሲዳማ ተወላጆች ናቸው ተብሏል። 

ቅዳሜ ነሐሴ 16፤ 2012 የምረቃ ስነ ስርዓታቸው የሚከናወነው የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በቁጥር አንድ ሺህ እንደሚጠጉ የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ፊሊጶስ ኖሆም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የመጀመሪያው የሲዳማ ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ደስታ ሌዳሞ በሚገኙበት በነገው ስነ ስርዓት ላይ፤ ለልዩ ኃይል አባላቱ የተሰራላቸው አዲስ የደንብ ልብስ በይፋ ይመረቃል ብለዋል። 

ተመራቂዎቹ የልዩ ኃይል አባላት ለ12 ቀናት የተሰጣቸውን ስልጠና ተከታትለው ማጠናቀቃቸውንም የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል። ስልጠናው ቴክኒካዊ ጉዳዩችን ያካተተ አለመሆኑንም አክለዋል። ይልቁንም ስልጠናው በተለያዩ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ተመድበው ሲሰሩ የቆዩት የልዩ ኃይል አባላት፤ በሲዳማ ክልል ካለው ህብረተሰብ ሲቀላቀሉ በሚኖራቸው መስተጋብር ላይ ያተኮረ እንደሆነ አብራርተዋል።     

“የልዩ ኃይል አባላቱ ከዚህ በፊት በደቡብ ክልል ውስጥ ስር ነው ሲሰሩ የነበሩት። አሁን የወሰዱት ስልጠና ሲዳማ ተወላጆች ሆነው ወደ ሲዳማ ሲመጡ ሲዳማ ተወላጅነታቸውን ብቻ ይዘው እንዳይመጡ፣ የተለየ መዋቅር እንደሆነ እና በህዝቦች አንድነት ላይ እና በአመለካከት ላይ ነው ስልጠና የወሰዱት” ሲሉ ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። 

የሲዳማ ክልል አሁን ከሚመረቁት በተጨማሪ አዲስ የልዩ ኃይል አባላት ለመመልመል እንቅስቃሴ አለመጀመሩን የሚገልጹት አቶ ፊሊጶስ ያንን ለማድረግ ክልሉ የራሱ የሆነ ማሰልጠኛ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል። አሁን በክልሉ እየተደረገ ያለው ምልመላ ለመከላከያ ሰራዊት እና ለፌደራል ፖሊስ አባልነት እንደሆነም አመልክተዋል።  

ነገ በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ በሚካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የካቢኔ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው የሀገር ሽማግሌዎች ይገኛሉ ተብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)