ኢዜማ በኦሮሚያ በደረሱ ጥቃቶች እና ጉዳቶች ላይ ሪፖርት ሊያወጣ ነው

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ፤ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተከሰቱ ጥቃቶችን እና የንብረት ውድመቶችን የዳሰሰ ሪፖርት እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ። ጉዳዩን የሚያጣራ የተወሰነ የፓርቲው ቡድን ተልዕኮውን ፈጽሞ ወደ አዲስ አበባ መመለሱንም ፓርቲው ዛሬ አርብ ነሐሴ 15፤ 2012 በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልጿል።

ሰባት አባላት ያሉበት ፓርቲው ቡድን በሻሸመኔ፣ አርሲ ነገሌ፣ ዝዋይ እና አሳሳ የደረሱ ጉዳቶችን ተዘዋውሮ መመልከቱን የአጣሪ ቡድኑ አባል የሆኑት የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። መንግስት በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰቱ ጥቃቶች ቀድሞ መከላከል ሲገባው አለማድረጉን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ ይህንን አካሄድ ኮንነዋል።  

“ሰዎች ተደራጅተው፣ መኪና ተከራይተው፣ ስንት ኪሎ ሜትር ሄደው ችግር እስከሚፈጥሩ ድረስ የማይሰማ የመንግስት መዋቅር፣ የማይሰማ የመንግስት ደህንነት አካል፤ ክልልም፣ ወረዳም እያስተዳደርኩ ነው ብሎ አፉን ሞልቶ እንደሚናገር ግራ ይገባኛል። ከዚያ አልፎ ደግሞ ይሄ ሁሉ ሲሆን አንድም የወረዳ፣ የዞን፣ የክልል ሃላፊ ‘ይሄ ነገር የተፈጠረው እኔ ወረዳ ላይ፣ እኔ ክልል ላይ ነው’ ብሎ አንድ ሰው እንኳ ልብ ያለው ስራውን የሚለቀቅ አላየነም” ሲሉ አቶ የሺዋስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

ወደ የአካባቢዎቹ የተሰማራው የኢዜማ አጣሪ ቡድን ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዩች አንዱ በክስተቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የማቋቋም እንቅስቃሴን መመልከት እንደሆነ አቶ የሺዋስ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል። ሌላው የቡድኑ ትኩረት “አሁን ያለው የጸጥታ ዋስትና ምን ይመስላል?” የሚለውን መገምገም እንደነበር አስረድተዋል። 

“ማቋቋሙ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንዳልሆነ አይተናል። ዋስትናውም በጣም አስጊ እንደሆነ በጣም በብዙ ቦታዎች ላይ ለማየት ችለናል። ሙሉውን ግን የቀረጻናቸውን ቪዲዮዎች፣ ያነጋገርናቸውን ሰዎች፣ የደረስንበትን በአጠቃላይ የልዑካን ቡድኑ እንደመጣ የሚገለጽ ይሆናል” ብለዋል አቶ የሺዋስ። 

በየአካባቢዎቹ በዜጎች ላይ የተከሰተው ጉዳት “ለሀገሪቱ እና ለሚታሰብው ዲሞክራሲ እንቅፋት ነው” ብለዋል። የተጎዱ ሰዎችን “ማነጋገር፣ ማጽናናት፣ እንዲቋቋሙ ማድረግ፣ ወደፊትም ዋስትና እንዲያገኙ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው” ሲሉ አሳስበዋል። ኢዜማ መንግስት አስቀድሞ መከላከል ላይ እንዲበረታ ጥሪ ያቀርባልም ብለዋል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)