በኦሮሚያ ክልል ዳኞች እስር እና ድብደባ እየደረሰብን ነው አሉ

5391

በሐይማኖት አሸናፊ 

በኦሮሚያ ክልል ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ያጋጠሙ የተለያዩ የጸጥታ ችግሮችን ተከትሎ ዳኞች ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት በፖሊስ ድብደባ እየደረሰባቸው እንደሆነ እና ከሕግ አግባብ ውጪም እስር እየደረሰባቸው እንደሆነ ገለጹ። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በዝርዝር ያጣራቸቸው ሁለት ጉዳዮችም ይህንን አረጋግጠዋል።

ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአዳሚ ቱሉ ወረዳ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት ዳኞች የሆኑት ኑሪ አቢዮ እና አህመድ ሰኢድ በቅድሚያ ለፖሊስ ስራ እንቅፋት እንደሆኑ ተነግሯቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ። ሁለቱም ዳኞች ማክሰኞ ሐምሌ 7፤ 2012 ጠዋት ሶስት ሰዓት ገደማ ከመኖሪያ ቤታቸው ወደ ፍርድ ቤቱ ሲገቡ በር ላይ ተይዘው ወደ ወረዳው ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን ያስረዳሉ።

አቶ ኑሪ የተባሉት ዳኛ  ያለምንም ወከባ በቁጥጥር ስር ሲውሉ አቶ አህመድ ግን በፖሊስ በከባድ ጥፊ ከተመቱ በኋላ ነው የታሰሩት ይላሉ ጓደኞቻችው። አቶ አህመድ “እኔ በሕግ ያለመከሰስ መብት አለኝ፤ ወንጀል ከሰራሁ እንደማንኛውም ሰው መጠየቅ አለብኝ፤ ነገር ግን በቅድሚያ ያለመከሰሰ መብቴን አንሱ” በማለታቸው በፖሊስ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው በቦታው የነበሩ የአይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

ከዳኞቹ እስር አንድ ቀን በፊት፤ ከዞኑ የፖሊስ መምሪያ የተላኩ ሰዎች በፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ውጥረት የተሞላበት ስብሰባ ማካሄዳቸውን  በፍርድ ቤቱ ባልደረባ የሆኑ እና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ ገልጸዋል። የፖሊስ ኃላፊዎቹ “ፖሊስ እየሰራ ላለው ስራ ዳኞች እንቅፋት እየሆናችሁ ስለመጣችሁ ልናስጠነቅቃችሁ ነው የመጣነው” ማለታቸውንም አክለዋል። እንደ ምንጫችን ገለጻ የፖሊስ ኃላፊዎቹን በተለይ ያሳሰባቸው ፖሊስ የሚጠይቀውን የጊዜ ቀጠሮ ዳኞች መከልከላቸው፣ በተለምዶ ከሚፈቀደው 14 ቀን በታች መስጠታቸውን እና ዋስትና መፍቀዳቸው ነው።  

የአዳሚ ቱሉ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ሌሎች ዳኞች፤ አሰራሩ ይሄ እንዳልሆነ እና ፖሊስ በፍርድ ቤቱ ሂደት ቅሬታ ካለው ይግባኝ መጠየቅ እንደሚችል ማስረዳታቸውንም ይገልጻሉ። ይህንን ተከትሎም  እስከ ኃይለ ቃል ልውውጥ የደረሰ ውጥረት በፖሊስ እና በፍርድ ቤት ኃላፊዎቹ መካከል መፈጠሩን በፍርድ ቤቱ የሚሰሩ ሌላ ባልደረባ አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ዳኞች በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከሶስት ቀናት በኋላ በሐምሌ 10፤ 2012 ወደ ሚሰሩበት የአዳሚ ቱሉ ወረዳ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት ቀርበዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ይህንኑ እውነታ በመዝገብ ቁጥር 36552 ከተከፈተ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ግልባጭ ተመልክታለች። 

ተጠርጣሪዎቹ የቀረቡበት ችሎት በሶስት ዳኞች ተሰየመ ሲሆን ችሎቱን በሰብሳቢነት ሲመሩ የነበሩት ደግሞ ሰብሳቢ ዳኛ ምትኩ መኮንን መሆናቸውን ሰነዱ ያሳያል። የግራ እና ቀኝ ዳኞች የነበሩት መርሲሞ በየነ እና ሮባ ንጉሱ እንደነበሩም በሰነዱ ሰፍሯል። ሶስቱ ዳኞቹ በጋራ በሰጡት ውሳኔም መዝገቡን መመልከት እንደማይችሉ በመግለጽ ራሳቸውን ከችሎቱ በማንሳት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት መርተውታል።

ከመዝገቡ ላይ ራሳቸውን ያነሱበት ምክንያትም፤ የተከሰሱት ዳኞች የስራ ባልደረቦቻቸው እና በግልም ጓደኞቻቸው መሆናቸውን ስለሆኑ ጉዳዩን ገለልተኛ ሆነው መመልከት ስለማይችሉ እንደሆነ ህጉን ጠቅሰው አብራርተዋል። መዝገቡ የተመራላቸው የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ዳኛ አበበ አዱኛም እንዲሁ ተከሳሾች የፍርድ ቤቱ ሰራተኞች በመሆናቸው ምክንያት መዝገቡ በፍርድ ቤቱ መታየቱ ለትክክለኛ የፍትህ አሰጣጥ እንደማይረዳ በመግለጽ መዝገቡን ዘግተዋል።

ፖሊስም በዞን ፍርድ ቤት አዲስ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ በማስከፈት ተጠርጣሪዎችን ሐምሌ 15፤ 2012 ያቀረበ ሲሆን የምስራቅ ሸዋ ዞን ፍርድ ቤት ችሎትም የ12 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ለፖሊስ ፈቅዷል። ከ12 ቀናት በኋላ ማለትም ሐምሌ 27፤ 2012 ዳኞችን ፍርድ ቤት ይዞ የሄደው ፖሊስ፤ ፍርድ ቤቱ በመዘጋቱ ምክንያት የታሰሩትን ዳኞች ወደ መቆያቸው ፖሊስ ጣቢያ ይዞ ተመልሷል። ፍርድ ቤቱ ድንገት አገልግሎት መስጠቱን ያቋረጠው በዚያ የሚሰራ አንድ የፍርድ ኦፊሰር በኮሮና ቫይረስ መያዙን ተከትሎ ነው መባሉ መሆኑን ተመሳሳይ ምንጮች ገልፀዋል።

የፖሊስ የምርመራ ስራ እንቅፋት ሆናችኋል በሚል ወንጀል ተጠርጥረው መያዛቸውን በታሰሩ ወቅት ተገለፆላቸው እንደበር የሚናገሩት ባልደረቦቻው ይህም በቀጥታ ከዳኝነት ስራቸው ጋር የተገናኛ ነው ይላሉ። ነገር ግን በምርመራ መዝገባቸው ላይ የተዘረዘሩት ወንጀሎች “ የሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ውድመት ማድረስ እና ሁከት እንዲሁም ብጥብጥ ላይ በቀጥታ ተሳትፈዋል” የሚሉ ወንጀሎች መዘርዘራቸውን ያስረዳሉ። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የምርመራ መዝገብም ይህንኑ ወንጀላ አረጋግጧል። 

ሁለቱ ዳኞች የዞኑ ፍርድ ቤት ወደ ስራ መመለሱን ተከትሎ ከ16 ቀናት በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ፍርድ ቤቱም እስራቸው ሕገ ወጥ መሆኑን ገልጾ እንዲፈቱ ነሐሴ 11፤ 2012 በዋለው ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷል። ነገር ግን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ዳኞቹ ከእስር ያለመለቀቃቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል። ሁለቱ ዳኞች በዞኑ ፍርድ ቤት “እስራቸው ሕገ ወጥ ነው፤ ይለቀቁ” ከተባለበት ቀን ጀምሮ አምስት ቀን ቢቆጠርም በእስር ቤት ይገኛሉ። በአጠቃላይ 40 ቀናትን በእስር ያሳለፉት ሁለቱ ዳኞች እስካሁንም ያለመከሰስ መብታቸው ያለመነሳቱን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያገኘችው መረጃ ያስረዳል።

ሄበን አርሲ ወረዳ

በተጨማሪ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ከህግ አግባብ ውጪ በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩ ዳኞች ውስጥ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማረጋገጥ የቻለችው የሄበን አርሲ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ናቸው። ከራሳቸው አንደበት እና ከሌሎችም ምንጮች ለመረዳት እንደተቻለው ለአንድ ሳምንት ያክል በቁጥጥር ስር ውለው የተለቀቁት እኚህ ዳኛ ያሲን ጂብኮ ይባላሉ። የመታሰራቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ለእርሳቸውም እንዳልተገለጠላቸው ነገር ግን እርሳቸውን ለማስፈታት ባልደረቦቻቸው በሚሞክሩበት ወቅት የወረዳውን አስተዳዳሪ በዋስ በመልቀቃቸው የተነሳ እንደሆነ መረዳታቸውን ይናገራሉ። 

በቁጥጥር ስር የነበሩትን የወረዳው አስተዳዳሪ እርሳቸው ወደሚያስችሉት ችሎት መቅረባቸውን የሚናገሩት ዳኛው የዋስትና መብታቸውን እንዴት እንደፈቀዱ እንደሚከተለው አብራርተዋል።

“የዋስትና መብት ቢፈቀድ አቃቤ ህግ ተቃውሞ ካለው ጠየቅኩ። ዓቃቤ ሕግም ሰውዬው በምን ወንጀል ተጠርጥረው እንደቀረቡ ራሱ እንደማያውቁ እና ዋስትና ይሰጥ ወይም ይከልከል ለማለት እንደሚቸገሩ ገለጹልኝ። የተከሰሱበት አንቀፅ እንኳን ቢገለጽ ዋስትና ለመከልከል ወይም ለመፍቀድ ያግዛል፤ ነገር ግን ያም አልተገለጸም። በዚህ ሁኔታ እኔ እንዴት ዋስትና ልከለክል እችላለሁ?” ሲሉ ዳኛው ይጠይቃሉ።

በዋስ እንዲፈቱ ትዕዛዝ የሰጡት ሳይፈጸም እና የወረዳ አስተዳዳሪውም ከእስር ሳይፈታ እርሳቸውም ከሚኖሩበት ነጌሌ ከተማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ ያሲን ይናገራሉ።

“እንደ ዳኛ ውሳኔዬ ተከብሮ ከዚያ ታስሬ ቢሆን መልካም ነበር። ያም አልሆነም። ያሰሩኝም እንደሽፍታ ነው። በሞተር ሳይክል እየሄድኩ ልዩ ኃይሎች በፓትሮል ከበቡኝ። በግራ እና በቀኝ ጠመንጃ ደቀኑብኝ። እኔ በወቅቱ እስክርቢቶ እንጂ ሌላ ምንም አልያዝኩም”

ዳኛ ያሲን ጂብኮ

“እንደ ዳኛ ውሳኔዬ ተከብሮ ከዚያ ታስሬ ቢሆን መልካም ነበር። ያም አልሆነም። ያሰሩኝም እንደሽፍታ ነው። በሞተር ሳይክል እየሄድኩ ልዩ ኃይሎች በፓትሮል ከበቡኝ። በግራ እና በቀኝ ጠመንጃ ደቀኑብኝ። እኔ በወቅቱ እስክርቢቶ እንጂ ሌላ ምንም አልያዝኩም” ሲሉ ለሰባት ዓመታት በፍርድ ቤቶች ውስጥ ያገለገሉት ዳኛ በቁጥጥር ስር የዋሉበትን ሁኔታ ያስረዳሉ። 

በአዳሚ ቱሉ በእስር ላይ እንዳሉት ሁለት ዳኞቹ ሁሉ አቶ ያሲንም ከተያዙ በኋላ ያለመከሰስ መብታቸው አልተነሳም። ከእስር የተፈቱትም ቢሆን በዞን ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጥረት እና ልመና መሆኑንም ይገልጻሉ። እስሩን ማን እንዳዘዘ እንደማይታወቅ እና የታሰሩትም፤ የተፈቱትም በስልክ “ከበላይ አካል የመጣ ነው” በተባለ ትዕዛዝ ነው ይላሉ። ከእስር ከወጡ በኋላም ቢሆን የእስራቸው ምክንያት እስካሁንም በግልጽ አለመታወቁን ያክላሉ።

“ይህንን የሚያይ ሌላ ዳኛ እንዴት በነፃነት ይሰራል? እኔ እንኳን አንድ ሰው ነኝ ግን የፍትህ ስርአቱ በጣም ያሳስበኛል” ሲሉ አቶ ያሲን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ማንም ሰው ከሕግ በታች ነው። ወንጀል ካለብኝ አልያዝ አይደለም። ነገር ግን የተያዝኩበት እስከተፈታሁበት ያለው ሂደት ትክክል አይደለም። እኔ ፍርድ ቤት ቀርቤ የዋስ መብት መጠየቅ አልፈልግም ነበር፤ ምክንያቱም በእኔ ምክንያት ሌላ ዳኛ ማሳሰር አልፈልግም” ሲሉ በዳኞች አካባቢ ያለውን ስጋት አጋርተዋል።  

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የተለያዩ የፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም ዳኞች፤ የፍትህ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ፍርሃት መንገሱን እና ያጠፋውን ካላጠፋው በሕግ ለመለየትም እየቻሉ እንዳልሆነ ገልጸዋል። “ከ14 ቀን በታች ጊዜ ቀጠሮ መስጠት አስጊ እየሆነ ነው” የሚሉት ዳኞች የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ዳኞች ከእስር እስከ ድብደባ የተለያዩ ጉዳት እያጋጠማቸው በመሆኑ ነው ሲሉ በፍትህ ተቋማት ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ አስረድተዋል።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጎንፋ አቶማ ዳኞች ላይ ያለ አግባብ እስር እየደረሰ መሆኑን እንደሚያውቁ እና ይህም ከየትኛውም ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ። “የፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አመራር ያለአግባብ የታሰሩ ዳኞችን እያስፈታ ሲሆን አዳሚ ቱሉ እና ባሌ ታስረው የሚገኙ ዳኞች ብቻ ናቸው የቀሩን። እሱን ጉዳይ ለመፍታት እየሞከርን ነው። የተያዙበት አካሄድ አግባብ ስላልሆነ እንዲለቀቁም የዞን ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል” ሲሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለ“ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዳኞች የሚሰጡትን ትዕዛዝ ፖሊስ እንደማይፈጽም፤ በአዳሚ ቱሉ ለ40 ቀናት በእስር ላይ ያሉ ዳኞችን በማሳያነት በመጥቀስ የተጠየቁት አቶ ጎንፋ “ይህ የችሎቱ ሕገ መንግስታዊ ስልጣን ነው። የፍርድ ቤት ትዕዛዝን መፈፀም ግዴታ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

“ፍርድ ቤት ሌላ አላማ አለው፤ ሌላው የጸጥታ አካል ደግሞ ከዚያ የተለየ አላማ አለው ማለት አይቻልም። ችግሩን በተለይም በፍትህ አካላት ፎረም ለመፍታት እየተሞከረ ነው። ይህ ፎረም ፖሊስ እና አቃቤ ህግ የሚገኙበት ሲሆን የተለያዩ ችግሮችን ሲፈቱ ነበር፤ አሁንም ይፈታሉ” ሲሉም አብራርተዋል። 

በዳኞች ዘንድ በተደጋጋሚ የቀድሞው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ደሳ ቡልቻ ስም ይነሳል። “እርሳቸው ፍርድ ቤቶቹን በመሩበት ወቅት ዳኞች ላይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የሚሰጡት ፈጣን ምላሽ አሁን ቀርቷል፤ ዳኞች ከእስር በተጨማሪ ድብደባም እያጋጠማቸው ነው” የሚለውን ቅሬታም ለአቶ ጎንፋ አቅርበናል። ይህንን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ኃላፊው ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ችግር ሲፈጠር ፍርድ ቤቱ መግለጫ ይሰጥ እንደበር ይናገራሉ። ነገር ግን አሁን ላይ ክልሉ ካለበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ መግለጫ መስጠት ማቆማቸውን ገልጸዋል።

ዳኞችን ለመከላከል ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ከዚህ በኋላ እንደዚህ አይነት ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ከክልሉ አመራሮች ጋር ሰፊ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህም ባሻገር ዳኞች ላይ ህገ ወጥ ድርጊት የፈጸሙ አመራሮች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አመልክተዋል። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር እና አንጋፋ የወንጀል ሕጎች ባለሞያ የሆኑት ስሜነህ ኪሮስ ዳኞች ያለመከሰስ መብታቸው ስለሚነሳበት ሂደት ያብራራሉ። አንድ ዳኛ በእጅ ከፍንጅ ወንጀል ካልተያዘ በቀር ያለመከከስ መብት እንዳለው ያብራራሉ። በቅድሚያ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰብሳቢነት የሚመራው የዳኞች አስተዳደር ገባኤ ጉዳዩን በዲሲፕሊን ሂደት መርምሮ ውሳኔ ላይ መድረስ እንደሚገባ አቶ ስሜነህ ገልጸዋል።

ከዚያም ፕሬዝዳንቱ ይህንን ውሳኔ ዳኞቹን ለሾመው ምክር ቤት በመላክ፤ ምክር ቤቱ ድምፅ ከሰጠበት በኋላ ያለከመከሰስ መብት ተነስቶ ዳኛው በመደበኛው የፍትህ ሂደት ውስጥ ያልፋል፤ እንደ ስሜነህ ገለፃ። በቅርቡም አንድ የፌደራል ዳኛ እንዲነሳ ጥያቄ ቀርቦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድቅ ያደረገበትን ሂደት ለማሳየት አቅርበዋል።

ነገር ግን ከዚህ ውጪ ዳኞች የታሰሩባቸው ክስተቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መታየቱን የሚያስረዱት ስሜነህ ይህ የሕግ ተርጓሚውን ሚና አደጋ ውስጥ የሚከት እና ኢ-ሕገ መንግስታዊ ሂደት ነውም ሲሉ ያብራራሉ። የሕግ የበላይነት የሚመሰረተውም በዳኞች ነፃነት ላይ ነውም ሲሉ ይገልፃሉ። በአማራ ክልል ከሕግ ውጪ የታሰረ ዳኛን ፕሬዘዳንቱ እንደማንኛውም እስረኛ ጠይቀው የተመለሱበትን ክስተት የሚያስታውሱት ስሜነህ መንግስት ከአምባገነን ስርአት ለመውጣት ሙከራ ላይ ስለነበረ እንደሚሻሻል ተስፋ በማድረግ ሲታለፍ እንደነበርም ይገልጻሉ።

“በደርግ ጊዜ ዳኛ በህገ ወጥ መንገድ መታሰሩን የሚያስረዳ መረጃ ባይኖረኝም፤ በኢሕአዴግ ዘመነ መንግስት ግን ዳኞች ሲታሰሩም ሲደበደቡም ተመልክተናል። አሁን ያ ጊዜ አለፈ በምንለበት ጊዜ ይህ ድርጊት በድጋሚ መፈጸሙ ለማንኛውም ባለሞያ ያንገበግባል።

ስሜነህ ኪሮስ – በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር

“በደርግ ጊዜ ዳኛ በህገ ወጥ መንገድ መታሰሩን የሚያስረዳ መረጃ ባይኖረኝም፤ በኢሕአዴግ ዘመነ መንግስት ግን ዳኞች ሲታሰሩም ሲደበደቡም ተመልክተናል። አሁን ያ ጊዜ አለፈ በምንለበት ጊዜ ይህ ድርጊት በድጋሚ መፈጸሙ ለማንኛውም ባለሙያ ያንገበግባል። በርግጥ በፍርድ ቤቶች ዙሪያ የተሰራ የሪፎርም ስራ ስለሌለ አስገራሚ አይደለም። ከላይ ያሉ የተወሰኑ ሰዎች ስለተሾሙ ብቻ ፍርድ ቤቶች ሪፎረም ሂደት ውስጥ አልፈዋል ማለት አይቻልም። የፍርድ ቤት ሪፎርም ማለት genuine የዳኞች ነፃነት ሲኖር ነው” ሲሉም ስሜነህ የጉዳዩን አሳሳቢነት ያስረዳሉ።

አንድ ዳኛ ፍርድ ሰጥቶ ሲወርድ የሚታሰር ከሆነ ይህ በቀጥታ የፍርድ ቤቱን ነጻነት ይጋፋል የሚሉት ባለሞያው ዳኛው ተከሶ የሚሄድበት ችሎትም በምንም መመዘኛ ነፃ ሆኖ ይሰራል ማለት አይቻልም ይላሉ። ይህም በቀጥታ የዴሞክራሲዊ ሂደቱን የሚጻረር እና ዳኝነት ዋጋ የለውም ወይም ሁለቱ የመንግስት ክፍሎች ህግ አውጪው ላይ በሚያደርጉት ጫና በተለይ የህግ አስፈጻሚው በህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ ውስጥ እንዳልገቡ ማሳያ ነውም ሲሉ ስሜነህ ገልጸዋል።

“ዳኛ ከሕግ ውጪ ታሰረ ማለት እኛ ሁላችንም ታሰርን ማለት ነው። እነሱ በዚህ ሁኔታ ሆነው መናገር ስማለይችሉ ሌላው ባለሙያ ሊናገርላቸው ይገባል” ሲሉም ስሜነህ ገልጸዋል። “መንግስት መጀመሪያ የታሰሩትን መፍታት፤ በድጋሚም እንዳይታሰሩ መወሰን አለባቸው። ይህ የአገሪቱን የህግ የበላይነት የሚወስን ድርጊት ነው። እኛም ለምንድንነው የምንሰራው? የሚል ጥያቄ ያመጣል። ተስፋ ያስቆርጣል፤ በአፋጣኝ መታረም ይገባዋል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስተያየታቸውን አካፍለዋል።

በጉዳዩ ላይ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር በስልክ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)