ኦፌኮ መንግስት የኃይል እርምጃዎቹን በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠየቀ

ተቃዋሚው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ መንግስት የኃይል እርምጃዎቹን በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠየቀ። ሀገሪቱ ትረጋጋ ዘንድም መንግስት በእስር ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን እንዲፈታ አሳስቧል። 

ፓርቲው ጥሪውን ያቀረበው “በኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰተው ወቅታዊ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ ያሻል” በሚል ርዕስ ስር ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 16፤ 2012 ባወጣው መግለጫ ነው። “በሺህዎች የሚቆጠሩ የቄሮዎች ሕይወት ተገብሮበት የመጣው እና ተስፋ ሰጪ የተባለው ለውጥ አጣብቂኝ ውስጥ ከገባ ውሎ አድሯል” ያለው ኦፌኮ “ሞት፣ እስር፣ ድብደባ ተመልሶ መጥቶብናል” ሲል በመግለጫው አስፍሯል። 

በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ “አደገኛ መስቀለኛ መንገድ ላይ ይገኛል” የሚለው ተቃዋሚ ፓርቲው ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል በኋላ በተለይ “ሁኔታዎች የበለጠ እየተወሳሰቡ መጥተዋል” ብሏል። ፓርቲው ክስተቱን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን “ውስብስብ ሁኔታ በመገመት የድምጻዊውን ግድያ በነጻና ገለልተኛ አካል እንዲጣራ እና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቆ እንደነበር አስታውሷል።     

“ግድያውን ተከትሎ የመጣው እስራትም እንደማይጠቅምና ይልቁንም የታሰሩት አባሎቻችን ተፈትተው ሀገርን የማረጋጋቱ ስራ ላይ እንዲሳተፉ ቢደረግ የተሻለ ምርጫ መሆኑን በመግለጽ ጠይቀናል” ሲልም ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል። 

ኦፌኮ፤ የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች እና በአዲስ አበባ ከተቀሰቀሰው ሁከት ጋር በተያያዘ  በርካታ አመራሮቹ እና አባላቱ ታስረውበታል። በእስር ላይ ካሉት የፓርቲው ተጠቃሽ ሰዎች መካከል ምክትል ሊቀመንበሩ በቀለ ገርባ፣ የአመራር አባሉ አቶ ደጀኔ ጣፋ እና የፓርቲው አባል ጃዋር መሐመድ ይገኙበታል። ፓርቲው አባላቱ እንዲፈቱ ላቀረበው ጥያቄ “አዎንታዊ ምላሽ” ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ባለበት ጊዜ ውስጥ እስሩ መቀጠሉን አመልክቷል። 

“በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅበት ሁኔታ መደበኛ ማቆያዎች በመሙላታቸው የትምህርት ቤት መማሪያ ክፍሎች ለኮሮና ቫይረስ በሽታ በሚያጋልጥ ሁኔታ እስር ቤቶች ሆነዋል” ሲል ኦፌኮ በመግለጫው አትቷል። 

በእስር ቤቶች ያሉ ተጠርጣሪዎችም በፍርድ ቤት ውሎዎቻቸው ይህንኑ የፓርቲውን ስጋት ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል። ከተጠርጣሪዎች ውስጥ የተወሰኑት በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በመረጋገጡ ፍርድ ቤት የማይቀርቡበት ጊዜም ተስተውሏል። ከእነዚህ መካከል የሆኑት የኦፌኮው አመራር ደጀኔ ጣፋ በኮሮና ተይዘው ወደ ሆስፒታል በመወሰዳቸው ከአንድም ሁለት ጊዜ በችሎት መገኘት አልቻሉም።     

ኦፌኮ በዛሬው መግለጫው በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረው እንደሚገኙ ጠቁሟል። ፓርቲው በግንኙነት መስመሮቹ አገኘሁት ያለውን መረጃ ጠቅሶ እንደገለጸው በክልሉ ያለው ወጣት ሲያነሳው የቆየውን “የሃጫሉ ገዳዮች ለፍርድ ይቅረቡ” የሚለውን ጥያቄውን ወደ “የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ሊዛወር እንደሚችልም አውቀናል” ብሏል። የኢትዮጵያ አብዛኞቹ ችግሮች “ፖለቲካዊ ናቸው” የሚለው ኦፌኮ “መፍትሄውም ፖለቲካዊ መሆን አለበት” ሲሉ የጸና አቋሙን በመግለጫው አንጸባርቋል። 

“ከዓለምም ሆነ ከራሳችን ተሞክሮ እንደምንረዳው የፖለቲካ ችግር በዋናነት የሚፈታው በእስር እና በጠመንጃ ሳይሆን በራሱ በፖለቲካ ነው” ሲል በመግለጫው የጠቀሰው ፓርቲው “ስለሆነም የኢፌዲሪ መንግስት የኃይል እርምጃዎቹን በአስቸኳይ አቁሞ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ከእስር በመፍታት ሀገሪቷ እንድትረጋጋ እንዲያደርግና ሀገሪቷን ሕዝቦቿን ወደ ብሔራዊ መግባባት እንዲመራ በአጽንኦት እንመክራለን” ብሏል።   

“ከዓለምም ሆነ ከራሳችን ተሞክሮ እንደምንረዳው የፖለቲካ ችግር በዋናነት የሚፈታው በእስር እና በጠመንጃ ሳይሆን በራሱ በፖለቲካ ነው”

የአፌኮ መግለጫ

መንግስታዊ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል በ13 ከተሞች በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ቁጥራቸው በወል ያልታወቀ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ማስታወቁ ይታወሳል። ኮሚሽኑ የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ተመሳሳይ ጥሪ አቅርቦም ነበር። 

የኢሰመኮን መግለጫ ክፉኛ የተቸው የኦሮሚያ ክልል መንግስት፤ የጸጥታ አካላት የወሰዷቸው እርምጃዎች “ህዝቡን የማዳን፣ ሕገ መንግስቱን የመከላከል፣ የህግ የበላይነት የማስከበር ኃላፊነት” እንደሆኑ የዕለቱ ዕለት ለኮሚሽኑ መግለጫ ባወጣው ምላሽ ገልጿል። የጸጥታ ኃይሎች እርምጃዎችን ሲወስዱ “ከተጠያቂነት ማዕቀፍ ጋር በማገናዘብ” እንደሆነም ክልሉ በምላሹ አጽንኦት ሰጥቶ ነበር። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)