በተስፋለም ወልደየስ
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ፤ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ እና አብረዋቸው በአንድ መዝገብ ችሎት የቀረቡ ሁለት ተጠርጣሪዎች በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ዛሬ ብይን ቢሰጠም “ፖሊስ ይግባኝ ጠይቋል” በመባሉ ሳይፈቱ መቅረታቸው ፓርቲው አስታወቀ። በሌላ መዝገብ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 18፤ 2012 ችሎት ፊት የቀረበው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ጋዜጠኛ ጉዮ ዋሪዮም በተመሳሳይ የዋስትና የገንዘብ መጠን ከእስር እንዲወጣ ፍርድ ቤቱ ቢበይንም በተመሳሳይ ምክንያት አለመፈታቱ ተገልጿል።
የኦፌኮ የወጣት ሊግ ሊቀመንበር አቶ ደስታ ዲንቃ ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት ለአራቱ ተጠርጣሪዎች የተጠየቀው የ40 ሺህ ብር ዋስትና ክፍያ ቢፈጸምም “ፖሊስ ይግባኝ ለመጠየቅ መዝገቡን ወስዶታል” በመባሉ ምክንያት የፍቺ ሂደታቸው ሳይፈጸም ቀርቷል። የይግባኝ ጉዳዩን የሚመለከት ዳኛ ከሰዓት ባለው ጊዜ ባለመኖሩም ጉዳዩ ለነገ እንዳደረ ጨምረው ገልጸዋል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዛሬው ውሎው፤ ከኦፌኮው ፖለቲከኛ አቶ ደጀኔ ጋር በተመሳሳይ መዝገብ የተካተቱ ሶስት ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ተመልክቶ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው የወሰነው የፖሊስን ጥያቄ ውድቅ አድርጎ እንደነበር ጠበቃ ከዲር ቡሎ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሶስቱ ተጠርጣሪዎች የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በአዲስ አበባ፣ ቡራዮ እና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ሁከት፤ “ተሳትፎ አላቸው” በሚል በፖሊስ ተጠርጥረው የተያዙ ናቸው።
ፖሊስ በሶስቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመስረት የ15 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ለፍርድ ቤቱ አመልክቶ እንደነበር ጠበቃ ከዲር ገልጸዋል። የፖሊስን ጥያቄ የተቃወሙት የእነ አቶ ደጀኔ ጠበቃ “ተጠርጣሪዎቹ የቀረበባቸው የወንጀል ዝርዝር ዋስትና አያስከለክልም” በማለት ተከራክረዋል። ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹን ለተጨማሪ 15 ቀናት የማቆየት ስልጣን የለውም ሲሉም ተሟግተዋል።
የግራ ቀኙን አስተያየት የተመለከተው ፍርድ ቤቱ በሁለት ምክንያቶች የፖሊስን የተጨማሪ ቀናት ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ጠበቃ ኪዲር ተናግረዋል። ዋስትና የሚከለከለው ተጠርጣሪዎች ላይ የቀረበው ወንጀል 15 ዓመትና ከዚያ በላይ የሚያስቀጣ ሲሆን አሊያም ወንጀሉ ሞት ሲያስከትል እንደሆነ ፍርድ ቤቱ መጥቀሱንም አስረድተዋል።
የፖሊስ የምርመራ ውጤት፤ ተጠርጣሪዎቹ የተጠቀሰባቸው ወንጀል ሞት ያስከተለ መሆኑን በግልጽ ያላሳየ መሆኑን ያመለከተው ፍርድ ቤቱ፤ የፖሊስን “የተጨማሪ ጊዜ ይፈቀድልኝ” ጥያቄ አለመቀበሉን ጠበቃው አመልክተዋል። በዚህም መሰረት ሶስቱ ተጠርጣሪዎች እያንዳንዳቸው የአስር ሺህ ብር ዋስትና በማቅረብ ከእስር እንዲለቀቁ ብይን ሰጥቷል ብለዋል።
ዛሬ በዋስትና እንዲፈቱ በፍርድ ቤት የተወሰነላቸው አቶ ደጀኔ እና አቶ ኮርሳ በእስር ላይ ባሉበት በኮሮና በሽታ በመያዛቸው በሆስፒታል በህክምና ላይ የቆዩ ናቸው። በበሽታው በመያዛቸው ምክንያት ከዚህ ቀደም በነበሩ ሁለት የችሎት ውሎዎች ሳይቀርቡ የቀሩት የኦፌኮ ምክትል ጸሀፊ አቶ ደጀኔ እና አቶ ኮርሳ ዛሬ ፍርድ ቤት ተገኝተው ነው።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በዛሬ ረፋድ ውሎው፤ ከእነ አቶ ደጀኔ ጉዳይ በተጨማሪ የOMN ጋዜጠኛ ጉዮ ዋሪዮን ጉዳይም ተመልክቷል። ጋዜጠኛ ጉዮ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ከመገደሉ ከአንድ ሳምንት በፊት ከOMN የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠየቅ ያካሄደ ነው።
ጉዮ ላይ ፖሊስ ያቀረባቸው የወንጀል ዝርዝሮች “በOMN ላይ ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት፣ ብሔርን ከብሔር ጋር የሚያጋጭ ዘገባ በማዘጋጀት እና በማሰራጨት እና በዚያ ምክንያት ሁከት እና ግርግር እንዲፈጠር፣ ያንን ተከትሎም ህይወት እንዲጠፋ እና ንብረት እንዲወድም አስተዋጽኦ አድርጓል” የሚል ነበር። ጉዩ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበው ሐምሌ 11፤ 2012 ነበር።
ፖሊስ በጋዜጠኛ ጉዮ ላይ ክስ ለመመስረት ተጨማሪ ቀናት መጠየቁን የገለጹት ጠበቃ ከዲር፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤ ፍርድ ቤቱ ይህንንም ጥያቄ ሳይቀበለው መቅረቱን ጠቁመዋል። የአራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ጋዜጠኛው በ10 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈታም መበየኑን አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)