ለአፋር እርዳታ ለማድረስ በሄዱ የድሬዳዋ አመራሮች ላይ ጥቃት ተሰነዘረ

በተስፋለም ወልደየስ 

በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች እርዳታ ለመለገስ ወደ ሰመራ ተጉዞ የነበረው የድሬዳዋ አስተዳደር ልዑክ በመልስ ጉዞ ላይ እያለ ማንነታቸው ባልታወቀ ኃይሎች ጥቃት ደረሰበት። በጥቃቱ ሁለት የፖሊስ አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ልዑክ ወደ አፋር ያቀናው በጎርፍ ለተፈናቀሉ ሰዎች የሚውል 1.2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያዩ የምግብ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለመለገስ እንደነበር የከተማይቱ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያሳያል። ልዑኩ የተመራው በከተማይቱ አስተዳደር የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልዬ ነበር። 

በልዑካን ቡድኑ ውስጥ የድሬዳዋ የከንቲባ ጽህፈት ቤት እና የካቢኔ ጉዳዩች ኃላፊ፣ የአደጋ ስጋት አመራር ቢሮ ኃላፊ እና ሌሎችም የከተማይቱ አመራሮች ነበሩበት ተብሏል። ልዑኩ የአፋር ክልል መንግስት መቀመጫ በሆነችው ሰመራ ከተማ በመገኘት እርዳታውን ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለአቶ አወል አርባ በሰላም ቢያስረክብም፤ በመልስ ጉዞው ግን ለጊዜው ትክክለኛ ስፍራው ባልተገለጸ ቦታ ያልተጠበቀ ጥቃት ገጥሞታል። 

“በዛሬው ዕለት ሌሎች ክልሎች እና ተቋማት እንደሚያደርጉት፤ በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጎዱ ሰዎች ድጋፍ ለማድረስ ሄደው ድጋፉን አስረክበው እየተመለሱ ባለበት ሰዓት ላይ ነው ጥቃት የደረሰባቸው” ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የልዑካን ቡድኑን አጅበው ከነበሩ የድሬዳዋ ፖሊስ አባላት መካከል በሁለቱ ላይ ጉዳት መድረሱን ማረጋገጣቸውን አቶ ሚካኤል ገልጸዋል። ፖሊሶች በአሁኑ ወቅት የህክምና እርዳታ እያገኙ እንደሆነም አስረድተዋል። ወደ ቦታው የተጓዙ አመራሮች እና ሌሎች የልዑካን ቡድን አባላት ላይ ጉዳት አለመድረሱንም አክለዋል። 

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በፍጥነት በቦታው ተገኝተው ጉዳዩን መቆጣጠር እንደቻሉ አቶ ሚካኤል ጠቁመዋል። ጥቃቱ በማን እና እንዴት ተፈጸመ የሚለው “በቀጣይ ተጣርቶ የሚገለጽ ይሆናል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)