የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ እና ምክትላቸው ከኃላፊነታቸው ተነሱ

በተስፋለም ወልደየስ

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በቀለ ሙለታ እና ምክትላቸው አቶ ብሩክ ከበደ ከትላንት ሰኞ ነሐሴ 18፤ 2012 ጀምሮ ከስልጣናቸው መነሳታቸውን የተቋሙ ምንጮች ገለጹ። በምትካቸው የቀድሞው የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና አቶ ሰጠኝ እንግዳው በኃላፊነት መመደባቸውን የተቋሙ ቦርድ ሊቀመንበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።   

እንደ ምንጮች ገለጻ ትላንት ለሁለቱም የፋና ኃላፊዎች የስንብት ደብዳቤ ደርሷቸዋል። የዋና ስራ አስፈጻሚው እና ምክትላቸው ከኃላፊነታቸው መነሳት ለሁሉም የተቋሙ ሰራተኞች በይፋ ባይገለጽም የኤዲቶሪያል ቡድን አባላት ለሆኑ የፋና የስራ ኃላፊዎች ግን ጉዳዩ እንደተገለጸላቸው ምንጮች ጠቁመዋል። የሁለቱን ኃላፊዎች ከቦታቸው መነሳት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ንጉሱ ጥላሁንም ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

በሁለቱ ኃላፊዎች ላይ እርምጃው የተወሰደው በመካከላቸው ያለውን የመሪነት ሽኩቻ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ሳይተገብሩት በመቅረታቸው እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል። የሁለቱ የፋና ከፍተኛ ኃላፊዎች ሽኩቻ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ እንደሆ የገለጹት ምንጮች ጉዳዩ ከተቋሙ ቦርድ እስከ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ የደረሰ እንደነበር ያስረዳሉ። 

ፎቶ፦ ከፋና ቴሌቪዥን የተወሰደ 

ቀደም ሲል ከኢህአዴግ በስተኋላ ደግሞ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቦርድ አመራሮች የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ናቸው። በአሁኑ ወቅት የፋና ቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሪቴያት ኃላፊነታቸው ተነስተው የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ናቸው። በአቶ በቀለ እና አቶ ብሩክ መካከል “እኔ ነኝ ተቋሙን መምራት ያለብኝ” የሚል ግልጽ ሽኩቻ ነበር” ያሉት አንድ የፋና ሰራተኛ፤ ቦርዱም ይህንን ችግር ለመፍታት ሙከራ አድርጎ ነበር ይላሉ።

“አቶ በቀለ በተቋሙ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ በሁለቱ መካከል ከፍተኛ የጥቅም ግጭት ነበር። ሁለቱም የየራሳቸውን ቡድን ማደራጀት ውስጥ ገብተው ነበር። በዚህ መሃል የተቋሙ ስራ በጣም ተጎድቷል” ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳየጠቀስ የጠየቁ የተቋሙ ሰራተኛ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በሁለቱ የፋና ኃላፊዎች መካካል “የጥቅም ግጭት” ነበር የሚለውን መረጃ አቶ ንጉሱ አስተባብለዋል። የተቋሙ ቦርድ ከውሳኔ ላይ የደረሰው “ግምገማ አድርጎ” እንደሆነ የገለጹት ሊቀመንበሩ “ነገር ግን የጥቅም ግጭት ስለመኖሩ አልገመገምንም” ብለዋል። ኃላፊዎቹ የተነሱበትን ምክንያት የተጠየቁት አቶ ንጉሱ ምክንያቱን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። 

በፋና ውስጥ የሚሰሩ በኃላፊነት ደረጃ ያሉ አንድ ሰራተኛ ግን የአቶ ንጉሱን ማስተባበያ አልተቀበሉም። “ፋና ታች ባሉት ሰራተኞች ጥንካሬ እንጂ በአመራሮቹ ጥሩ ለውጥ እንዳላመጣ በቦርዱ ጭምር ይታወቃል” ሲሉ ይሟገታሉ።፡

ፎቶ፦ ከፋና ቴሌቪዥን የተወሰደ 

በጥቂት የሰው ኃይል እና በኋላ ቀር መሳሪያዎች በ1987 ዓ.ም. መቋቋሙን የሚገልጸው ፋና ከአጭር ሞገድ ራዲዮ ስርጭት ተነስቶ፣ በ11 የክልል ከተሞች የኤፍ. ኤም. ራዲዮ ጣቢያዎችን እስከ መክፈት ተጉዟል። የራሱ የሆነ ባለ 11 ፎቅ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ህንጻ ባለቤት የሆነው ፋና፤ በጥር 2010 ዓ.ም. የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ጣቢያ መደበኛ ስርጭት ጀምሯል። 

በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ፣ አፋርኛ፣ እንግሊዘኛ ቋንቋዎች የሚዘጋጅ ድረ ገጽ እና የማህበራዊ ትስስር ገጾች ያሉት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፤ ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ በአረብኛ ቋንቋ የዲጂታል ይዘቶችን ማቅረብ ጀምሯል። በጽሁፍ፣ በፎቶግራፍ፣ በቪዲዮ እና በድምጽ የሚቀርቡት የፋና የዲጂታል ይዘቶች፤ በሳምንት በአማካይ በስድስት ሚሊየን ገደማ ጎብኚዎች እንደሚታዩ ከተቋሙ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። 

ለፋና አብዛኞቹ ስኬቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሆነው ስማቸው የሚነሳው የቀድሞ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወልዱ ይመስል ናቸው። በ1993 ዓ.ም. በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ለሁለት መከፈሉን ተከትሎ ከሬድዮ ፋና ኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉት አቶ ሙሉጌታ ገሰሰን ተክተው ራዲዮ ጣቢያውን የማስተዳደሩን ስራ የተረከቡት አቶ ወልዱ እስከ ነሐሴ 2011 ዓ.ም. ድረስ በዋና ስራ አስፈጻሚነታቸው ቆይተዋል።

እስከ ትላንት ድረስ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ብሩክ ከበደ በተቋሙ ውስጥ ለረጅም ዘመን አገልግለዋል – ፎቶ፦ ከፋና ቴሌቪዥን የተወሰደ 

ከአቶ ወልዱ ጋር ለበርካታ ዓመታት የሰሩት አቶ ብሩክ ከበደ፤ ከጋዜጠኝነት ተነስተው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚነት ደረጃ የደረሱት በእርሳቸው አስተዳደር ዘመን ነው። የቀድሞው ዋና ስራ አስፈጻሚ በግል ምክንያት ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸው ሲገለጽ አቶ ብሩክ “ቦታውን እረከባለሁ የሚል ተስፋ ነበራቸው” ይላሉ ምንጮች። 

ሆኖም ለሁለት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ፋናን ሲያስተዳድሩ የቆዩት አቶ ወልዱን የተኩት አቶ በቀለ ሙለታ ናቸው። አቶ በቀለ መንግስታዊውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተቋምን ለስድስት ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል። የእርሳቸው ከሌላ ቦታ ወደ ፋና መምጣት ለአቶ ብሩክ “አልተዋጠላቸውም ነበር” የሚሉት ምንጮች፤ ይህም በሁለቱ ግለሰቦች መካከል ለተፈጠረው የስልጣን ሽኩቻ “ዋነኛው መንስኤ ነው” ባይ ናቸው።  

አቶ በቀለ ሙለታ የፋና ዋና ስራ አስፈጻሚ ከመሆናቸ በፊት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ለስድስት ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል- ፎቶ፦ ከፋና ቴሌቪዥን የተወሰደ 

ትላንት ከዋና ስራ አስፈጻሚነት በተነሱት አቶ በቀለ ምትክ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን እንዲመሩ የተመደቡት አቶ አድማሱ ዳምጠው መሆናቸውን የተቋሙ ሊቀመንበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከአንድ ዓመት ከ10 ወር በፊት የኦሮሚያ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ነበሩት አቶ አድማሱ በመስከረም 2011 ዓ.ም. የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በነበሩት አቶ ለማ መገርሳ ከተሾሙ 17 የክልሉ የካቢኔ አባላት አንዱ ነበሩ። 

ለሰባት ወራት ብቻ በኦሮሚያ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊነት የቆዩት አቶ አድማሱ፤ በፌደራል ደረጃ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትን በሚኒስትር ማዕረግ ሲያገለግሉ በቆዩት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ተተክተዋል። ላለፈው አንድ  ዓመት ግድም በቻይና በትምህርት ላይ የቆዩት አቶ አድማሱ ከወር በፊት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ምንጮች አመልክተዋል። 

አዲሱ የፋና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በራዲዮ ፋና ከሪፖርተርነት እስከ ዜና ኃላፊነት የደረሰ የቀደመ አገልግሎት አላቸው – ፎቶ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት

አቶ አድማሱ በራዲዮ ፋና ከሪፖርተርነት እስከ ዜና ኃላፊነት የደረሰ የቀደመ አገልግሎት አላቸው። ተቋሙን ከበታች ጀምሮ ማወቃቸው በዋና ስራ አስፈጻሚነት ለመመደብ ካስቻላቸው ምክንያቶች አንዱ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮች ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)