በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ምስክሮች የመሰማት ሂደት ላይ ነገ ውሳኔ ሊሰጥ ነው

በሐይማኖት አሸናፊ 

በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ስር በተጠረጠሩ 14 ግለሰቦች ላይ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን እያደመጠ የሚገኘው የፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ይሰማል ተብሎ ከሚጠበቀው 15 ምስክሮች ውስጥ ሶስቱን በሁለት ቀጠሮ ሰምቷል። ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት “በኮሮና ቫይረስ የተያዙት ድነው እስኪመለሱ ይዘግይ ወይም ይቀጥል” በሚለው ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ ነገ ረቡዕ ከሰአት ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የቅድመ ምርመራ ጉዳያቸው እየታየ ካሉ 14 ተጠርጣሪዎች መካከል አምስቱ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡን የተገለጸው ባለፈው ነሐሴ 11፤ 2012 በነበረው ችሎት ነበር። ትላንት ሰኞ ነሐሴ 18 በተካሄደው ችሎት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በማገገም ላይ ያሉት ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በድጋሚ ተነስቷል። 

ዓቃቤ ህግ፤ ቀሪ ምስክሮቹ በኮሮና በመያዛቸው ፍርድ ቤት ባልቀረቡት ተጠርጣሪዎች ላይም ጭምር የሚሰሙ በመሆኑ፤ እነርሱ አገግመው እስኪመጡ ድረስ ሂደቱ ለጊዜው እንዲገታ ጥያቄ አቅርቧል። ይህንን የተቃወሙት የተጠርጣሪ ጠበቆች የዓቃቤ ህግን አስተያየት “indefinite (ባልተወሰነ የግዜ ገደብ የቀረበ ጥያቄ) እና ያልተገባ” ብለውታል። 

“በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ለማገገም የሚወስድባቸው ጊዜ የማይታወቅ እና እግዚያብሔር አያምጣው እና ሞትም ጭምር ሊያስከትል የሚችል ነው” ሲሉ የተጠርጣሪ ጠበቆች የምስክር የመስማት ሂደቱ መቀጠል እንዳለበት አስተያየት ሰጥተዋል።

በልደታ የችሎት አዳራሽ የተሰየመው ችሎትም የሁለቱን ወገን ክርክር አዳምጧል። በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በማገገሚያ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ቅዳሜ ነሐሴ 16 ናሙና መስጠታቸውን ከዓቃቤ ህግ አረጋግጧል። የምርመራ ውጤቱ እስከ ነገ ረቡዕ ነሐሴ 20፤ 2012 እንደሚደርስ ግምት የወሰደው ችሎቱ፤ በሁለቱም ወገን በቀረበው አቤቱታ ላይ ትዕዛዝ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ከሳሽንም ተከሳሽንም በቀጠሮ የመስጠት ሂደት ላይ ያማከሩት ዳኛው፤ የምርመራ ውጤቱን ለመጠባበቅ እና በቀጣይ የምስክር የመስማት ሂደቱ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለነገ ረቡዕ ቀጠሮ ሰጥተዋል። 

ባደሩ አቤቱታዎች ላይ የተሰጡ ትዕዛዞች

ትላንት ሰኞ ነሃሴ 18፤ 2012 የተሰየመው ችሎት፤ ባሳለፍነው ሳምንት ሁለት ምስክሮችን በዝግ ሂደት ካዳመጠ በኋላ ዓቃቤ ህግ እንዲሁም ተጠርጣሪዎች ባቀረቧቸው አቤቱዎች ላይ ትዕዛዞችን በማስተላለፍ ስራውን ጀምሯል።

የመጀመሪያው አቤቱታ ተጠርጣሪዎች መገናኛ ብዙሃን ያለፈቃዳችን ፎቶ እና ቪዲዮ እንዳይቀዱ ይከልከልን ሲሉ ያቀረቡት አቤቱታ ነው። በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 590/2003 መሰረት “መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ የሚያደርሱትን መረጃ በምስል በማስደገፍ የማቅረብ መብት አላቸው” ያለው ችሎቱ ነገር ግን በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 29፤ ንዑስ አንቀፅ ስድስት እና ሰባት መሰረት፤ እነዚህ መብቶች ሊገደቡ እንደሚችሉ ገልጿል። 

ዳኛው አቤቱታውን ተንተርሰው ላሳለፉት ውሳኔ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ ሃያ ስድስትን በተጨማሪነት ጠቅሰዋል። የሕገ መንግሰቱ አንቀጽ 26 በሰብአዊ መብቶች ምዕራፍ ስር የተካተተ ሲሆን የግለሰቦች የግል ህይወት የመከበር እና የመጠበቅ መብቶችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች የሰፈሩበት ነው። 

የእዚሁ አንቀጽ፤ ንዑስ አንቀጽ አንድ “ማንኛውም ሰው የግል ህይወቱ፣ ግላዊነቱ የመከበር መብት” እንዳለው ያትታል። በንዑስ አንቀጹ ከተዘረዘሩ መብቶች መካከል፤ ማንኛውም ሰው መኖሪያ ቤቱን፣ ሰውነቱን እና ንብረቱን ከመመርመር የመጠበቅ መብት እንዳለው የሰፈረው ይገኛል። በዚህ መሰረትም ችሎቱ መገናኛ ብዙሃን ያለተጠርጣሪዎች ፈቃድ ፎቶም ሆነ ቪዲዮ እንዳይወስዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

ሁለተኛው አቤቱታ በዓቃቤ ህግ የቀረበ ነበር። ዓቃቤ ህግ ፍርድ ቤቱ ምስክሮችን እየዳመጠ ያለበት የቅድመ ምርመራ ሂደትን የያዘ ሰነድ በማህበራዊ ሚዲያ መውጣቱን እና “ይህም አግባብ አይደለም ይባልልኝ” ሲል ያመለከተው ነው። ምስክሮች የሚሰሙበት የወንጀል ዝርዝር የያዘው ጭብጥ ብሎም የዓቃቤ ህግ ምስክሮች ዝርዝር የያዘ ሰነድ “በማህበራዊ ሚዲያ ይፋ ተደርጎብኛል” ሲል ዓቃቤ ህግ ለችሎቱ በተጨማሪ አቤት ብሏል።  ጉዳዩን የመረመረው ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን ውድቅ አድርጎታል።

ሌላኛው አቤቱታ ከተከሳሾች የቀረበ ሲሆን ሶስት ተከሳሾች የኮሮና ምርመራ አንዲደረግላቸው ጥያቄ ያቀረቡበት ነው። ችሎቱም ተጠርጣሪዎች ምርመራ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

በአራተኝነት የቀረበው አቤቱታ ተከሳሾች የሃይማኖት አባቶቻቸውን ለማኘት ያቀረቡት ጥያቄ ነው። በዚህ መሰረት ተጠርጣሪዎቹ የሃይማኖት አባቶቻቸውን በስልክ ለ40 ደቂቃ ያህል እንዲያናግሩ ችሎቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ሲያሳልፍም የሕገ መንግስቱን አንቀፅ 21 በመጥቀስ በህግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች የሃይማኖት አማካሪዎቻቸውን የማግኘት መብት እንዳላቸው በማስረዳት ነው።

በትላንቱ የችሎት ውሎ በአቶ መለሰ ዲሪብሳ በቀረበ አቤቱታ ላይም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ አቶ መለሰ ቤተሰብ እንዲጠይቃቸው እንዲሁም ምግብ እና ልብስ እንዲገባላቸው ለፖሊስ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡት አቤቱታም ፍርድ ቤቱ በስድስተኛነት የተመለከተው ጉዳይ ነው። ጠበቆች የሞባይል ስልክ ይዘው እንዳይገቡ ቢከለከልም፤ ዓቃቤያን ህግ ግን ስልክ ይዘው መግባታቸው አግባብ አይደለም የሚል አቤቱታ ለችሎቱ ቀርቧል። ፍርድ ቤቱም “ስልክ ወደ ችሎቱ ተይዞ እንዳይገባ የሚደረገው ለደህንነነት ሲባል መሆኑን ጠቅሶ ዓቃቤያን ህጉም “ስልክ ይዘው እንዳይገቡ” ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ችሎቱ ባደሩ አቤቱታዎች ላይ ትዕዛዝ ካሰማ በኋላም ወደ ቅድመ ምርመራ ምስክር የማስማት ሂደቱ ተመልሷል። በዕለቱም ከመጋረጃ ጀርባ የሚያስደምጣቸውን ሁለት ምስክሮችን ለመስማት በማቀድ ሂደቱን ቢጀምርም የመጀመሪያው ምስክር የመስማት ሂደቱ ብቻ ሶስት ሰዓታት ፈጅቶ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ ላይ ተጠናቅቋል። በዚህ ምክንያትም ሁለተኛውን ምስክር የመስማት ሂደቱ በይደር ለቀጣይ ቀጠሮ እንዲተላለፍ አስገድዷል።  

አዳዲሶቹ አቤቱታዎች 

ችሎቱ የምስከር የመስማት ሂደቱን ካጠናቀቀም በኋላ የተጠርጣሪዎችን እና የዓቃቤ ህግ አዳዲስ አቤቱታ አዳምጧል። በቅድሚያ አቤቱታቸውን ያሰሙት አንደኛ ተጠርጣሪ አቶ ጃዋር ናቸው። ምስከሮች እየመሰከሩ ባሉበት ዕለት በቦታውም በሰዓቱም እንዳልነበሩ ለችሎቱ በመግለጽ ለዚህም “መረጃም ማስረጃም አለን። የት ነው ፍትህ የሚጠየቀው? ዓቃቤ ህግ የሚያቀርበው ምስክርነት እውነተኛ ከሆነም የመስካሪዎች ማንነት ማረጋገጥ አለበት ብዬ እገምታለሁ” ሲሉ አመልክተዋል።

ሌላው አቶ ጃዋር ያቀረቡት አቤቱታ የባንክ አካውንታቸው እና ንብረቶታቸው እንዳይንቀሳቀሱ መታገዱን ገልጸው፤ ፖሊስ ምርመራዬን ጨርሻለሁ ስላለ “ይለቀቅልኝ” ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል። አያይዘውም “ስማቸው ሲራጅ ብቻ ስለሆነ (በስም መመሳሰል) በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የባንክ አካውንታቸው ታግዶ ይገኛል” ያሉት አቶ ጃዋር ይህም አግባብነት የለውም ችሎቱም ይህ እንዲቆም ትዕዛዝ እንዲሰጥ ያድርግልኝ ብለዋል።

በተጨማሪም በትውልድ አካባቢያቸው ምዕራብ ሐረርጌ ዞን በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች  የሚገኙ ግለሰቦች ከእርሳቸው ጋር በተያያዘ እንግልት ደርሶባቸዋል ብለዋል። የወረዳዎቹን ስም በመዘርዘር ጭምር አንደኛ ተከሳሽ በጠቀሷቸው በእነዚህ ወረዳዎች “የመንግስት ኃላፊዎች መኪና ይዘው በየሱቁ እየዞሩ በጃዋር ገንዘብ ነው የምትነግዱት እያሉ ሸቀጣሸቀጥ እና ቡና ይጭናሉ” በማለት ድርጊቱ እንዲቆም ሲሉ ለችሎቱ አመልክተዋል።

በመቀጠልም አቶ በቀለ ገርባ ለችሎቱ ባቀረቡት አቤቱታ “ይህ ክርክር በመንግስት እና በተቃዋሚ መካከል የሚደረግ show trial  ነው” ሲሉ አቤቱታቸውን ጀምረዋል። “መንግስት ፍርድ ቤቶችን ተጠቅሞ ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት እና መጪው ምርጫን ታሳቢ ያደረገ ሂደት ነው” ሲሉም ለችሎቱ ገልጸዋል። በአንድ ወገን “ከፍተኛ የሚዲያ ዘመቻ ተከፍቷል” የሚል አቤቱታ ያሰሙት አቶ በቀለ በማህበራዊ ገጾችም የሚሰራጩ መረጃዎች ቤተሰቦቻቸውን አደጋ ውስጥ የሚከት እንደሆነም ተናግረዋል። አክለውም ለምስክሮች የሚደረገው ጥበቃ ለቤተሰቦቻቸውም እንዲደረግ ጠይቀዋል።

“የድሮ ጄነራሎችን በመገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ ዛቻ እያደረሱብን ነው” የሚለውን አቤቱታ በመንግስት ላይ ያቀረቡት አቶ በቀለ የክልል አመራሮችም በዚሁ ዘመቻ ተሳትፈዋል ሲሉ በጥቅሉ ገልፀዋል። አክለውም “የአማራ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ በመገናኛ ብዙሃን በመቅረብ ሁላችንንም ጠቅሰው ተናግረዋል” ሲሉም ለችሎቱ አመልክተዋል።

“እነዚህ የመንግስት ኃላፊዎች ምንም በማይመለከታቸው ጉዳይ እየገቡ ነው” ያሉት አቶ በቀለ “ይህ እየሆነ ያለውም በሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ነው፤ ችሎቱ ይህ አግባብ ነው ካለም እኛም የራሳችንን ሃሳብ የማቅረብ እድል ሊሰጠን ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል። ዓቃቤ ህግም “አረጋግጫለሁ” እያለ በመገናኛ ብዙሃን የሚያቀርባቸው መረጃዎች ሊከለከሉ የሚገቡ ናቸውም ሲሉ አመልክተዋል።

“በአዲስ አበባ የህዳሴውን ግድብ መሞላት ተከትሎ በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ‘ሃጫሉ ሞቷል፤ ጃዋር ይቀራል’ ተብሎ እዚሁ ከተማ ውስጥ ሲዘፈን ነበር። ይህንንም ወታደር ከበብ አድርጎ መጠየቅ ነበረበት” ሲሉ በቀለ አንስተዋል። “እኛ የምናምነው ከሳሽም፣ ምስክርም ሆነ የሚያዘፍነው አካል አንድ መሆኑን ነው” ሲሉም በችሎቱ ገልፀዋል። በጥቅሉም “ችሎቱ ይከላከልልን እኛን አንዲሁም ቤተሰቦቻችን የሚመለከት ማንኛውም ነገር እንዲቆም ይደረግልን። ይህ ካልሆነ ግን በዚህ ሂደት የመቀጠል ፍለጎት የለንም›› ሲሉ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ደንበኞቻቸውን በተመለከተ በመገናኛ ብዙሃን “የጦር መሳሪያዎች ፈቃድ እንደሌላቸው ተረጋገጠ” የሚሉ መግለጫዎችን ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎችን ዓቃቤ ህግ ማቅረቡ አግባብ አይደለም ሲሉ አመልክተዋል። “አብዛኛው ሕብረተሰብ የሕግ እውቀት እንደሌለው እየታወቀ ዓቃቤ ሕግ የሚያወጣቸው መግለጫዎች አግባብነት የላቸውም፤ አሁን በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ መረጃዎችን ለሚመለከቱ እና የቤተሰብ አባላቸውን ላጡ ሰዎች ይህ ከፍተኛ የጠላትነት ስሜት የሚያመጣ ነው” ሲሉም ጠበቆች ገልጸዋል።

አክለውም በሳተላይት መሳሪያ ላይ የቀረበውም፣ “በርግጥ የሳተላይት መሳሪያ ነው ወይ? ስንት ነው? ፈቃድ አለው፤ የለውም? እና የመሳሰሉት በተመለከተ እኛ የምናቀርበው ማስረጃ ይኖራል” ሲሉ ጠበቆች ገልጸዋል። ዓቃቤ ሕግ ግን በመገናኛ ብዙሃን እያቀረበ ያለው መረጃ “በሌሎች መዝገቦች ላይ ያልተለመዱ ናቸው፣ ይህም ነው ሂደቱን ፖለቲካዊ የሚያስመስለው” ሲሉ ለችሎቱ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡

በጉዳዮቹ ላይ አስተያየቱንን የሰጠው ዓቃቤ ህግ “ማን የት እንደነበር ባለቤቱ የሚያውቀው ነገር ነው” ሲል “በቦታው አልነበርኩም” በሚል ከአንደኛ ተጠርጣሪ ለቀረበው አቤቱታ መልስ ሰጥተዋል። ምስክሮችም እንደዚህ ቀደሙ ፖሊስ ያቀረባቸውን ምስክሮች በቀጥታ ለችሎቱ አለማቅረቡን ገልጾ “ዓቃቤ ህግ screen አድርጎ ያቀረባቸው ናቸው” ሲሉም ገልጸዋል።

“ተጠየቂ የሚያደርገን የማያስተኛ ህሊና አለን” ያሉት መዝገቡ ላይ የተሰየሙት ዓቃቤ ህግ “ያስቆምናቸው ዶክመንተሪዎችም አሉ” በማለት በመገናኛ ብዙሃን “ዘመቻ ተከፍቶብናል” በሚል በተጠርጣሪዎች ለቀረበው አቤቱታ መልስ ሰጥተዋል። መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚቀርበውን አቤቱታም፤ በስም በመጥቀስ ቢቀርብ ትዕዛዙ እንዲፈፀም ለማድረግ እንደሚያስችለውም ዓቃቤ ህግ ምላሽ ሰጥቷል። ዓቃቤ ህግ በመገናኛ ብዙሃን መግለጫዎችን በሚሰጥበት ወቅትም ከቃላት አጠቃቀም ጀምሮ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ መሻሻሎች መኖራቸውንም ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)