ኢትዮ ቴሌኮም በጥቅል አገልግሎቱ ላይ የታሪፍ ማሻሻያ አደረገ

– ከነገ ጀምሮ ለ3 ቀናት የሚቆይ ስጦታም ማዘጋጀቱን አስታውቋል

ኢትዮ ቴሌኮም በጥቅል አገልግሎቱ ላይ የታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ። ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ በሚደረገው የጥቅል አግልግሎት ማሻሻያ በሞባይል ዳታ ፓኬጅ ላይ 35 በመቶ እና በሞባይል ድምጽ አገልግሎቱ 29 በመቶ ቅናሽ እንደተደረገ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 20፤ 2012 በሰጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል። 

ኢትዮ ቴሌኮም ከነገ ሐሙስ ነሐሴ 21 ጀምሮ ለ3 ቀናት የሚቆይ የምስጋና ስጦታ ማዘጋጀቱን በዛሬው መግለጫው ጠቅሷል። የድርጅቱ ደንበኞች 1GB የኢንተርኔት ዳታ፣ 40 ደቂቃ የድምጽ አገልግሎት፣ 100 አጭር የጽሁፍ መልዕክቶች ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት በነጻ እንደሚያገኙ አስታውቋል። 

በኢትዮጵያ ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም በስራ ላይ ያለው ኔትወርኩን ለ5G የሞባይል አገልግሎት ዝግጁ ማድረጉንም በዛሬ መግለጫው ጠቁሟል። ኢትዮ ቴሌኮም በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ኔትወርኩን ለ5G ቢያዘጋጅም አገልግሎቱን ግን በቅርቡ እንደማይጀምር ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

መንግስታዊው ድርጅት በ2013 በጀት ዓመት 55.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማስገባት ማቀዱንም ገልጿል። የደንበኞቹን ቁጥርም አሁን ካለው በ13 በመቶ በማሳደግ 52.1 ሚሊዮን ለማድረስ በእቅዱ አስቀምጧል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)