በተስፋለም ወልደየስ
የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወላይታ ዞን አመራሮችን ጨምሮ ለ20 ተጠርጣሪዎች በተፈቀደው ዋስትና ላይ ፖሊስ ያቀረበውን ይግባኝ ለመመልከት ለሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 20፤ 2012 በሐዋሳ ከተማ ባስቻለው ችሎት ተጠርጣሪዎቹ ሳይቀርቡ በመቅረታቸው ሌላ ቀጠሮ መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል።
ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ የአራቱ ጠበቃ የሆኑት አቶ ተመስገን ዋጃና ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት አስራ አንድ ተጠርጣሪዎች ብቻ መጥሪያ የደረሳቸው በመሆናቸው ተሟልተው መቅረብ አልቻሉም። በሀዋሳው ችሎት አስር ተጠርጣሪዎችን ወክለው የቀረቡት ሁለት ጠበቆች “መጥሪያው የደረሰበት አግባብ የስነ ስርዓት ህጉን የተከተለ አይደለም” በማለት ተቃውሞ ማቅረባቸውንም ገልጸዋል።
“በወላይታ ያለው የጸጥታ ሁኔታ መጥሪያውን ለማድረስ አያስችልም የተባለው አግባብ አይደለም ብለናል። በአካባቢው የነበረው ሁኔታ ሰላማዊ ነው። ህዝቡ የተለመደውን ስራ እየሰራ ነው። የመንግስት መስሪያ ቤቶችም መደበኛ አገልግሎታቸውን እየሰጡ ነው”
ጠበቃ ተመስገን ዋጃና
በስነ ስርዓት ህጉ መሰረት ፖሊስ የፍርድ ቤት መጥሪያን በአካል በመገኘት ለተጠርጣሪዎች ማድረስ እንደሚገባው የጠቀሱት ጠበቃው ሆኖም ፖሊስ ይህን ሳያደርግ መቅረቱን ገልጸዋል። ፖሊስ መጥሪያዎቹን በወላይታ ዞን ለሚገኘው ኮማንድ ፖስት ማድረሱን እና ይህ አካልም ለሀገር ሽማግሌዎች መስጠቱን አብራርተዋል። የሀገር ሽማግሌዎቹ በተሟላ መልኩ መጥሪያውን ማድረስ ባለመቻላቸው ተጠርጣሪዎቹ በችሎት ሳይገኙ መቅረታቸውን ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱም ጠቅሰዋል።
ፍርድ ቤቱ ባዘዘው መሰረት ለምን መጥሪያውን እንዳልደረሰ ለፖሊስ ጥያቄ ማቅረቡን አቶ ተመስገን ተናግረዋል። ፖሊስ “በአካባቢው የነበረው ረብሻ መጥሪያውን በአካል ለማድረስ አያስችልም ነበር” የሚል ምላሽ መስጠቱንም ገልጸዋል። ይህን የፖሊስ ምክንያት ጠበቆች በችሎት መቃወማቸውን አክለዋል።
“በወላይታ ያለው የጸጥታ ሁኔታ መጥሪያውን ለማድረስ አያስችልም የተባለው አግባብ አይደለም ብለናል። በአካባቢው የነበረው ሁኔታ ሰላማዊ ነው። ህዝቡ የተለመደውን ስራ እየሰራ ነው። የመንግስት መስሪያ ቤቶችም መደበኛ አገልግሎታቸውን እየሰጡ ነው። በዚህ ሁኔታ መጥሪያ ማድረስ አልችልም ማለት የሚከብድ ስለሆነ ፖሊስ በቸልተኝነት መጥሪያውን ማድረስ አልቻለም ስንል ለችሎቱ አስረግጠን አስረድተናል” ሲሉ አቶ ተመስገን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሀገር ሽማግሌዎች በኩል ለተጠርጣሪዎች እንዲደርስ የተደረገው መጥሪያ፤ በኮማንድ ፖስት ትዕዛዝ ተመልሶ እንዲሰበሰብ ከተደረገ በኋላ በድጋሚ እንዲሰጣቸው መደረጉን ለችሎቱ ማንሳታቸውን ጠበቃው ገልጸዋል። መጥሪያው እንዲሰበሰብ ተደርጎ የነበረው “ጉዳዩ በፖለቲካ እየታየ ነው” በሚል እንደነበርም ጠቅሰዋል። ይህ ሁኔታ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የፈጠረው መደናገር ዛሬ ፍርድ ቤት ላለመቅረባቸው በተጨማሪ ምክንያትነት ተነስቷል ብለዋል።

የጠበቆችን አቤቱታ ያደመጠው የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለመጪው ረቡዕ ነሐሴ 27፤ 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ ተመስገን ገልጸዋል። በመጪው ቀጠሮም ፖሊስ ባቀረበው የዋስትና መቃወሚያ ላይ ተጠርጣሪዎች ያላቸውን ምላሽ በጹሁፍ እንዲያቀርቡም ትዕዛዝ መስጠቱንም አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱ የጹሁፍ ምላሽ እንዲቀርብ ያዘዘው አሁን ባለው ወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ስጋት ምክንያት የቃል ክርክር ለማድረግ አመቺ ባለመሆኑ ምክንያት እንደሆነም ጠቁመዋል።
ፖሊስ የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤን ጨምሮ በ20 ተጠርጣሪዎች ላይ ይግባኝ የጠየቀው፤ የወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እያንዳንዳቸው በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ማድረጉን ተከትሎ ነው። ፖሊስ ከነሐሴ 3፤ 2012 ጀምሮ ለአራት ቀናት በእስር አቆይቷቸው የነበሩ ግለሰቦች 26 የነበሩ ቢሆንም ይግባኝ የጠየቀው በ20ዎቹ ላይ ብቻ መሆኑ ታውቋል። በፖሊስ ይግባኝ ያልተካቱቱት ስድስት ግለሰቦች የሀገር ሽማግሌዎች ናቸው ተብሏል።
የሀገር ሽማግሌዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው የነበረው ከወላይታ ዞን አመራሮች፣ ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ ከአክቲቪስቶች እና ሌሎች ግለሰቦች ጋር በወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምስረታ ላይ ለመምከር በሶዶ ከተማ ጉተራ አዳራሽ ለስብሰባ በተቀመጡበት እንደነበር ከስፍራው የወጡ መረጃዎች በወቅቱ አመልክተው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)