የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዶ/ር እንድርያስ ጌታን የዞኑ አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመ

በተስፋለም ወልደየስ

የወላይታ ዞን ምክር ቤት ዛሬ አርብ ነሐሴ 22 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ፤ ባለፈው ሳምንት በብልጽግና ፓርቲ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ በተደረጉት አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ምትክ ዶ/ር እንድርያስ ጌታን የዞኑ አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመ። ምክር ቤቱ የዶ/ር እንድርያስን ሹመት በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ስብሰባውን የታደሙ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አበበች እራሾ በተመራው በዛሬው አስቸኳይ ጉባኤ፤ 14 አባላት በተለያዩ ምክንያቶች አለመገኘታቸውን ምንጮች ገልጸዋል። በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚገኘው ጉተራ አዳራሽ በተካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ዶ/ር እንድርያስ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

በዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አበበች እራሾ በተመራው በዛሬው አስቸኳይ ጉባኤ፤ 14 አባላት በተለያዩ ምክንያቶች አለመገኘታቸውን ምንጮች ገልጸዋል

አዲሱ ተሿሚ የደቡብ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው። ዶ/ር እንድርያስ ወደ ክልል ከመዛወራቸው በፊት የወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ ዲን እና የአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል። 

ዶ/ር እንድርያስ በዛሬው የምክር ቤት ጉባኤ ባሰሙት ንግግር፤ የወላይታ ዞን በክልል ለመደራጀት ያቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ ያነሱ ሲሆን “የተጀመሩ ስራዎችን ከህዝብ ጋር በመመካከር እሰራለሁ” ማለታቸውን ምንጮች አስረድተዋል። በዞኑ ደፍርሶ የነበረውን ሰላም እና ጸጥታ ወደነበረበት እንዲመለስ እና በዚህ ምክንያት የተቀዛቀዘው ኢኮኖሚ እንዲያድግ የሚያስችሉ ስራዎችን እንደሚያከናውኑም አዲሱ አስተዳዳሪ ቃል ገብተዋል ተብሏል። 

በነሐሴ ወር መጀመሪያ በወላይታ ሶዶ በስብሰባ ላይ የነበሩ የዞኑ አመራሮች እና ሌሎች ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ተቃውሞ መቀስቀሱ ይታወሳል። ለአራት ቀናት በእስር ቆይተው ከተፈቱት 26 ግለሰቦች ውስጥ የዞኑ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እና የዞኑ የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ዮሃንስ ይገኙበታል። 

የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፤ በወላይታ ዞን በአመራርነት የተቀመጡ ኃላፊዎች ከነሐሴ 14፤ 2012 ጀምሮ ከስልጣናቸው እንዲነሱ መወሰኑን አስታውቆ ነበር። የዞኑ አመራሮች “ለውጡን በጉልበት ለመቀልበስ የተለያዩ ታክቲኮችን በመንደፍ፥ በክልል የመደራጀት ጥያቄ አመላለስ ለማወሳሰብ አቅደው በመፈፀም፣ በዞኑ ያለመረጋጋትና የንጹሃን ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆነዋል” ሲል አስተባባሪ ኮሚቴው መወንጀሉም አይዘነጋም። 

ለአራት ቀናት በእስር ቆይተው ከተፈቱት 26 ግለሰቦች ውስጥ የዞኑ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እና የዞኑ የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ዮሃንስ ይገኙበታል

የኮሚቴውን መግለጫ ተከትሎ ከፌደራል እና ከደቡብ ክልል የተውጣጡ የወላይታ ተወላጅ ባለስልጣናት ባለፈው እሁድ በዞኑ ካሉ የወረዳ አመራሮች ጋር በሶዶ ከተማ ስብሰባ አድርገው እንደነበር ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከዚያም በኋላ የተለያዩ ስብሰባዎች መካሄዳቸው ቢነገርም በስብሰባዎቹ ስለተደረሰባቸው ውሳኔዎች ከዞኑ አስተዳደርም ሆነ ከደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ በኩል በግልጽ የወጡ መረጃዎች የሉም።

በስብሰባዎቹ ላይ በተሳታፊዎች ከተነሱ አጀንዳዎች ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ የወላይታ ዞን አመራሮች እና ሌሎች ግለሰቦች ክስ መቋረጥ አንዱ እንደነበር ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ይናገራሉ። ሆኖም የክስ ሂደቱ መቀጠሉ በዚህ ሳምንት ተረጋግጧል። የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ20 ተጠርጣሪዎች ዋስትና መፈቀድ ላይ የቀረበለትን ይግባኝ ለመመልከት፤ ከትላንት በስቲያ በስቲያ ረቡዕ ነሐሴ 20፤ 2012 ያስቻለ ቢሆንም ተጠርጣሪዎቹ በአካል ባለመቅረባቸው ለሚቀጥለው ሳምንት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)