በተስፋለም ወልደየስ
የእነ ጃዋር መሐመድን የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ የሚመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት፤ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የእስረኛ አስተዳደር ኃላፊ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው በፖሊስ ኮሚሽኑ ቁጥጥር ስር ላሉ ሶስት ተጠርጣሪዎች የኮሮና ምርመራ ተደርጎ፣ ውጤት እንዲቀርብ የሰጠው ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ባለመፈጸሙ ነው።
ፍርድ ቤቱ ባለፈው አርብ ባስቻለው ችሎት፤ የፖሊስ ኮሚሽኑ የእስረኛ አስተዳደር ኃላፊ ለዛሬ ታስረው እንዲቀርቡ አዝዞ ነበር። ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 26፤ 2012 ችሎት ፊት የቀረቡት ዋና ኢንስፔክተር አራጌ እሸቴ “በቴሌቪዥን በተላለፈው መሰረት መቅረብ ስላለብኝ ቀርቤያለሁ። ማንም አስሮ ያስገደደኝ አካል የለም” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቁጥጥር ስር ላሉ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በነሐሴ ወር ውስጥ ለሶስት ጊዜያት ያህል ምርመራ እንደተደርገላቸው የተናገሩት የእስረኛ አስተዳደር ኃላፊው፤ ሆኖም የምርመራ ውጤታቸውን ለፍርድ ቤት እንዲቀርብ “ማንም የነገረኝ ወይም የጠየቀኝ የለም” ብለዋል። “እኛ ማቅረብ የምንችለው የራሳችንን እስረኞች ውጤት ነው” ያሉት ዋና ኢንስፔክተር አራጌ “የእነርሱን ማቅረብ ያለባቸው የፌደራል እስረኛ አስተዳደር ኃላፊዎች ነው” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ምላሽ ሰጥተዋል።
ምርመራ ይደረግላቸው ከተባሉት ሶስት ተጠርጣሪዎች አንዱ የሆኑት የOMN ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ፤ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ቀደም ሲል ማድረጋቸውን ሆኖም ውጤቱ እንዳልተነገራቸው ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። ከእነርሱ ጋር አብረው ሲበሉ እና ሲጠጡ የነበሩ ሌሎች ተጠርጣሪዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጠቆመው በእነርሱ ላይም አንዳንድ ምልክቶች በመታየታቸው ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ማቅረባቸውን አስታውሷል። ፍርድ ቤቱ እንዲመረመሩ ትዕዛዝ ካስተላለፈ በኋላ ግን የእነርሱን ናሙና የወሰደ እንደሌለ አብራርቷል።
ጉዳዩን የሚመለከቱት ዳኛ ፍርድ ቤቱ በሶስት የተለያዩ የችሎት ውሎዎች ለሶስቱ ተጠርጣሪዎች ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ ቢሰጥም አለመፈጸሙን ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የእስረኞች አስተዳደር ኃላፊ በቀጣይ ቀጠሮ ትዕዛዙን ፈጽመው እንዲቀርቡ “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ” የሰጡት ዳኛው “በቀጣይ ቀጠሮ ተመርመረው የማይቀርቡ ከሆነ በእርስዎ ላይ እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ፍርድ ቤቱ ከምሳ ሰዓት በፊት በነበረው የችሎት ውሎው፤ አቃቤ ህግ በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ በተካተቱ 14 ተጠርጣሪዎች ላይ ለዛሬ ካቀረበቸው አራት ምስክሮች የአንደኛውን የምስክርነት ቃል አድምጧል። በዛሬው ችሎት፤ በኮሮና በሽታ በመያዛቸው ከዚህ ቀደም በነበሩ ችሎቶች ላይ ያልቀረቡ ስድስት ተጠርጣሪዎች ተገኝተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)