የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የጋዜጠኞች የጉዞ ክልከላን በተመለከተ “መረጃ አልነበረኝም” አለ

በተስፋለም ወልደየስ

ከነገ በስቲያ በትግራይ የሚካሄደውን ምርጫን ለመዘገብ፤ ዛሬ ወደ መቀሌ ሊጓዙ የነበሩ ጋዜጠኞች ከአውሮፕላን ጣቢያ እንዲመለሱ መደረጉን በተመለከተ ቅድሚያ መረጃ እንዳልነበረው እና ጉዳዩን እንደሚያጣራ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጸ። የጉዞ እገዳ የተደረገባቸው ጋዜጠኞች መታወቂያቸው፣ የተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው፣ ላፕቶፖቻቸው፣ ካሜራዎች እና ሌሎች የስራ ዕቃዎቻቸው በጸጥታ ኃይሎች እንደተወሰዱባቸው ተናግረዋል።

ጋዜጠኞቹ እና ሌሎች መንገደኞች ወደ መቀሌ ሊጓዙ የነበረው ዛሬ ከቀኑ አምስት ሰዓት ላይ ነበር። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ መንገደኛ እንደተናገሩት የአየር ማረፊያ የጸጥታ ሰዎች ከወትሮው በተለየ ለውጭ ሀገር ዜጎች ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር። በኢትዮጵያ የኒውዮርክ ታይምስ ዘጋቢ የሆነው ሳይመን ማርክስ በተለይ በርካታ ጥያቄዎች ሲቀርቡለት እንደነበር ማየታቸውን ተናግረዋል።

በአየር ማረፊያው የጸጥታ ሰዎች ከተጠየቁት መካከል የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ከፍተኛ ተንታኝ የሆነው ዊሊያም ዴቪድሰን እንደሚገኙበት የአይን እማኙ ገልጸዋል። ከእነርሱ በተጨማሪ ሶስት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችም በተመሳሳይ ወደ መቀሌ የሚጓዙበትን ምክንያት እንደተጠየቁ ጠቁመዋል።

ሶስቱ ጋዜጠኞች የአውሎ ሚዲያ ሰራተኞች እንደሆኑ የመገናኛ ብዙሃኑ ዋና አዘጋጅ በቃሉ አላምረው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። ወደ መቀሌ ሊጓዙ የነበሩት ጋዜጠኞች በዘጋቢነት የሚሰራው ሀገር ተክለብርሃን፣ የካሜራ ባለሙያው ሙሴ ሀድራ እና የቪዲዮ አርታኢው መልካምፍሬ ይማም እንደሆኑ ገልጿል።    

ጋዜጠኞቹ ወደ ስፍራው ሊያመሩ የነበረው ከትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን በደረሳቸው ግብዣ እንደነበር የሚናገረው በቃሉ ሆኖም አንድ የኤርፖርት የጸጥታ ሰው “ህገወጥ ምርጫ ለማድረግ፤ ወንጀል ለመስራት ነው እየሄዳችሁ ያላቸሁት” በሚል ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር ለብቻ ተለይተው እንዲቀመጡ ማደረጉን ገልጿል። በዚያን ወቅት ከጋዜጠኞቹ ጋር መረጃ ይለዋወጥ እንደነበር የሚያስረዳው በቃሉ በስተኋላ ላይ ስልካቸውን እና ሌሎችም ኤሌክትሮኒክስ የስራ መገልገያዎቻቸው እንደተወሰዱባቸው ገልጿል። 

“አንድ ካሜራ ከእነ ሙሉ አክሰሰሪው፣ ሶስት አራት ሌንስ፣ ሁለት ላፕቶፕ፣ ሶስት ስልክ፣ አንድ ፕሌይ ስቴሽን እና የልጆቹን መታወቂያ ነጥቀው መልሰዋቸዋል” ሲል ዋና አዘጋጁ ከስራ ባልደረቦቹ የተወሰዱ ንብረቶችን ዘርዝሯል።  

በስፍራው የነበሩት የአይን እማኝም በጋዜጠኞቹ ላይ የደረሰውን የንብረት ነጠቃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ጋዜጠኞቹ ብቻ ሳይሆን እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች መንገደኞችም የያዟቸውን ተንቀሳቃሽ ስልኮች እና ላፕቶፖች እንዲያስረክቡ መገደዳቸውን ተናግረዋል። ከዚያ በኋላ ለአምስት ሰዓት ታቅዶ የነበረው በረራ መሰረዙንም አስረድተዋል። 

በእርግጥም በረራው ተሰርዞ እንደው የተጠየቁት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መረጃዎች ባለሙያ በሲስተማቸው ላይ ግልጽ መረጃ ማግኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀሌ በቀን ሶስት በረራዎችን የሚያደርግ ሲሆን ከእነርሱ ውስጥ ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ እና ከሰዓት ስምንት ሰዓት ላይ የነበሩ በረራዎች ያለምንም እክል መከናወናቸውን ባለሙያዋ ገልጸዋል።  

ጋዜጠኞቹ ወደ መቀሌ እንዳይጓዙ መከልከላቸውን በተመለከተ መስሪያ ቤታቸው የቀደመ መረጃ ደርሶት እንደው በ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ድንቁ ስለ ጉዳዩ እንደማያውቁ ምላሽ ሰጥተዋል። ጉዳዩን መጀመሪያ ራሱ የተረዱት ጥያቄው ሲቀርብላቸው እንደሆነ እና ከጋዜጠኞቹም የደረሳቸው አቤቱታ አለመኖሩን ተናግረዋል። 

“የጉዞ እገዳው ለምን ተደረገ?” የሚለውን ማብራሪያ መስጠት ያለበት እርምጃውን የወሰደው አካል እንደሆነ የጠቆሙት ዶ/ር ጌታቸው ሆኖም ከትግራይ ምርጫ “ህገወጥነት ጋር በተያያዘ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ከቀናት በፊት በእርሳቸው መስሪያ ቤት በኩል የትግራይ ምርጫ ሽፋንን በተመለከተ ለውጭ ሀገር ጋዜጠኞች ምክር ተሰጥቶ እንደነበርም አስታውሰዋል። 

ለውጭ ሚዲያ ወኪሎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክር እንደሚሰጡ የሚያስረዱት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር፤ ለዚህም በምሳሌነት ወደ ህዳሴው ግድብ አሊያም ግጭት ወዳለባቸው አካባቢዎች መቼ መሄድ እንዳለባቸው እና እንደሌለባቸው ምክር እንደሚለግሷቸው አመልክተዋል። የውጭ ሚዲያ ወኪሎች ወደተለያየ ቦታ ሲጓዙ የትብብር ደብዳቤ እንደሚጠይቋቸው የሚናገሩት ዶ/ር ጌታቸው በእነርሱ በኩልም ለየአካባቢዎቹ አስተዳደር በመደወል ስፍራዎቹ ለጋዜጠኞች ደህንነት የተመቸ መሆኑን የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራ አብራርተዋል። ይህ የሚደረገውም የውጭ ሚዲያ ወኪሎቹ የሀገሪቱን “dynamics አያውቁም” በሚል እሳቤ እንደሆነም ጠቁመዋል።       

ፎቶ፦ ኑቢያ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን

“በዚያው አይነት ሰሞኑን የውጭ ሚዲያ ወኪሎችን ወደ ትግራይ ሄዶ መዘገብ የሚመከር አይደለም ብለናቸዋል። ምክንያቱም የፌደራል መንግስቱ ህገ ወጥ ነው ያለው ምርጫ ነው። ምርጫ ቦርድም፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም [ጭምር]። ስለዚህ እንደ እኛ ‘ባትዘግቡት ይመረጣል፤ Editorial ውሳኔው ግን የእናንተ ነው፤ እኛ ምክር ነው የምንሰጠው’ ብለናቸዋል” ሲሉ በመስሪያ ቤታቸው በኩል ሰሞኑን ለጋዜጠኞች የተላለፈውን መልዕክት አስረድተዋል። 

በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በኩል ለጋዜጠኞች በስልክ እየተደወለ የተነገረው ይህ መልዕክት “የፕሬስ ነጻነትን ይጋፋል” በሚል በባለሙያዎቹ ዘንድ ትችት ሲቀርብበት ነበር። እንዲህ አይነት ማሳሰቢያ ለመገናኛ ብዙሃናቸው እንዳልደረሰ የሚናገረው የአውሎ ሚዲያ  ዋና አዘጋጅ በቃሉ አላምረው፤ በሙያው አካሄድ ጦርነትም ቢሆን እንደሚዘገብ ይከራከራል። የፌደራል መንግስትም ቢሆን “የትግራይ ምርጫ መካሄድ የለበትም” አለማለቱን በመጥቀስም ለዘገባ ወደ መቀሌ ለመሄድ መወሰናቸው ትክክል እንደነበር ይሟገታል። 

“ጉዳዩ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲቀርብ ይህንን መዘገብ በህግ መከልከል ነበረበት። በእኛ እይታ ምርጫው አልተከለከለም፤ ‘እንደተደረገ አይቆጠርም’ ነው የተባለው። እርሱ ሌላ የህግ ትርጓሜ ስለሆነ ሃሳባችን እርሱን ለማስተናገድ ነበር” ሲል ከውሳኔያቸው ጀርባ ያለውን አመክንዮ ገልጿል።   

የትግራይ ምርጫን መዘገብ፤ አለመዘገብ እና የፕሬስ ነጻነት “የንድፈ ሀሳብ ጉዳይ አይደለም” የሚሉት ዶ/ር ጌታቸው “በተግባር ችግር ስላለ” መንግስት ውሳኔ ማሳለፉን ይናገራሉ። “መንግስት የጸጥታ ስጋት ሊኖረው ይችላል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን በዝርዝር ሊያውቁ የሚችሉት ከእርሳቸው መስሪያ ቤት ውጭ ያሉ አካላት መሆናቸውን ያብራራሉ። የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የፕሬስ ፍቃድ ለሰጣቸው ጋዜጠኞች ተገቢውን ምክር መስጠቱንም በአጽንኦት አንስተዋል።       

“እኛ የፕሬስ ፍቃድ የሰጣቸውን በተመለከተ ‘ተንቀሳቅሳችሁ የመስራት መብት አላችሁ’ ብለናቸዋል። ስለዚህ የእኛን ምክር ሰጥተን ስናበቃ በዚያ በተቃራኒ ሄደው ‘እንሰራለን፤ ሪስኩን እንወስዳለን’ ካሉ ኃላፊነቱ የእነሱ ነው”

ዶ/ር ጌታቸው ድንቁ – የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር

“እኛ የፕሬስ ፍቃድ የሰጣቸውን በተመለከተ ‘ተንቀሳቅሳችሁ የመስራት መብት አላችሁ’ ብለናቸዋል። ስለዚህ የእኛን ምክር ሰጥተን ስናበቃ በዚያ በተቃራኒ ሄደው ‘እንሰራለን፤ ሪስኩን እንወስዳለን’ ካሉ ኃላፊነቱ የነሱ ነው” ሲሉ  ዶ/ር ጌታቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፕሬስ ፍቃዳቸው እና የስራ መሳሪያዎች የተወሰደባቸው ጋዜጠኞችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ማጣራት እንደሚያደርግም አክለዋል። 

የትግራይ ክልል ምርጫ ከነገ በስቲያ ረቡዕ ጳጉሜ 4፤ 2012 እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለታል። የምርጫው ውጤት መስከረም 3፤ 2013 ይፋ እንደሚደረግ የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን ያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ያመለክታል። 

ከፌደራል መንግስት ተቋማት ውሳኔ በተቃራኒ በትግራይ ክልል የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከትላንት በስቲያ ነሐሴ 30፤ 2012 አስቸኳይ ስብሰባ አካሄዶ ውሳኔ አሳልፏል። ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል የሚደረገው ምርጫ “እንዳልተደረገ የማይቆጠር፣ የማይጸና እና ተፈጻሚነት የሌለው ነው” ሲል ወስኗል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)