ወላጆች በግል ትምህርት ቤቶች እስከ ሶስት ወር የሚደርስ ክፍያ እየተጠየቅን ነው ሲሉ አማረሩ

በበለጠ ሙሉጌታ 

መንግስት የ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ እንዲጀመር መፍቀዱን ተከትሎ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች እስከ ሶስት ወራት የሚደርስ ክፍያ መቀበል መጀመራቸው “አግባብነት የለውም” ሲሉ የተማሪ ወላጆች ቅሬታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ትምህርት መቼ እንደሚጀመር በይፋ ሳይታወቅ በአንድ ጊዜ ከፍ ያለ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲከፍሉ መገደዳቸው ጫና እንደፈጠረባቸውም ገልጸዋል። 

በአዲስ አበባ ከሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች አንዱ በሆነው ለምለም አካዳሚ በተባለ ትምህርት ቤት ሁለት ልጆቻቸውን ያስመዘገቡት ሰብለ አሰፋ፤ “አማራጭ በማጣት እና የልጆች የምዝገባ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ቦታ ለመያዝ” በሚል የተጠየቁትን ከፍተኛ ዋጋ መክፈላቸውን ይናገራሉ። የአምስተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ለሆኑ ልጆቻቸው በአጠቃላይ 3,095 ብር መክፈላቸውን የሚያስረዱት ሰብለ “በዚህ በበዓል ወቅት የዚህን ያህል ገንዘብ መክፈል አግባብነት የሌለው ነው” ብለዋል። ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ ሳይወሰን የወር ክፍያ እንዲከፍሉ መገደዳቸውንም ተችተዋል። 

በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የሃ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አካዳሚ ልጃቸውን የሚያስተምሩ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሌላ ወላጅም በተመሳሳይ የወር ክፍያ መፈጸማቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “መንግስት የግል ትምህርት ቤቶችን የወርሃዊ ክፍያ ጣሪያን በትኩረት ሊመለከተው ይገባል” የሚሉት እኚሁ ወላጅ በትምህርት ቤቱ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ለሆነች ልጃቸው፤ የትምህርት ክፍያ ብቻ 2,800 ብር ማውጣታቸውን ይገልጻሉ። ከዚህ በተጨማሪም ለመመዝገቢያ እና ለትምህርት መሳሪያዎች አንድ ሺህ ብር መክፈላቸውንም ያስረዳሉ። 

መቅደስ አሞኜ የተባሉ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ልጃቸውን ከአጸደ ህጻናት ጀምሮ አሁን አስከደረሰበት አምስተኛ ክፍል ድረስ ያስተማሩት በአንድ ትምህርት ቤት መሆኑን ጠቁመው በየጊዜው የሚጨመረው የትምህርት ክፍያ በኑሯቸው ላይ ጫና ማሳደሩን አስታውቀዋል። የትምህርት ቤት ወርሃዊ ክፍያ የልጆቹን ከክፍል ክፍል መሸጋገር መሰረት አድርጎ በየዓመቱ ከ100 እስከ 250 ብር እንደሚጨምር የሚጠቆሙት መቅደስ፤ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ልጃቸውን ከግል ትምህርት ቤት ለማስወጣት እንደሚገደዱ አመልክተዋል። 

ሳሪስ አካባቢ በሚገኘው ዮዝ ስኮላርስ በተሰኘ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማረው ልጃቸው፤ አንደኛ ክፍልን ሲቀላቀል 300 ብር ወርሃዊ ክፍያ ብቻ መክፈላቸውን መለስ ብለው የሚያስታውሱት መቅደስ፤ ከአራት ዓመት በኋላ ወርሃዊ ክፍያው በሶስት እጥፍ መጨመሩን ያብራራሉ። ለ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ባለፈው ሳምንት ክፍያ በፈጸሙበት ወቅት፤ 950 ብር ወርሃዊ ክፍያ እና የመመዝገቢያ 500 ብር መክፈላቸውንም በምሳሌነት ያነሳሉ።  

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተዘዋውራ በተመለከተቻቸው ትምህርት ቤቶችም ወላጆች የጠቀሱት የክፍያ አካሄድ በትክክልም እየተተገበረ እንዳለ አረጋግጣለች። ከአምስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሃ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አካዳሚ እና ፋልከን አካዳሚ  የሶስት ወር ክፍያ ከመመዝገቢያ እና ከሌሎች የትምህርት  ቁሳቁስ ክፍያዎች ጋር በማስከፈል ላይ ሲገኙ፤  በየካ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ለምለም አካዳሚ እንደዚሁም በአራዳ ክፍለ ከተማ ሱኘር ሆሊሴቨር አካዳሚ  እና  ኖላዊ አካዳሚ በአቃቂ  ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአንድ ወር የትምህርት ክፍያ የሚጠይቁ ናቸው። 

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ፋልከን አካዳሚ ትምህርት ቤት፤ ወላጆች የሶስት ወራት ክፍያን እንዲከፍሉ በግልጽ ባወጣው ማስታወቂያ ይፋ ያደረገ ሲሆን የተከፈለው ክፍያ በምንም አይነት አግባብ ተመላሽ እንደማይሆንም ማሳሳቢያ ጭምር አክሏል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የትምህርት ቤቱ ማስታወቂያ “ክፍያ ተመላሽ ይደረግልኝ የሚል ጥያቄ አሳማኝ ምክንያት ቢኖረው እንኳን ለሌላ አገልግሎት ታሳቢ ይደረግለታል እንጂ ተመላሽ አይደረግለትም” ይላል። 

ፋልከን አካዳሚ ለአፀደ ህፃናት ተማሪዎች ለምዝገባ እና ለሩብ ዓመት ክፍያ በአጠቃላይ የሚጠይቀው 3,000 ብር ነው። ትምህርት ቤቱ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ላሉ ተማሪዎች የሚጠይቀው አጠቃላይ ክፍያ ከአፀደ ህፃናቱ መጠን በ575 ብር ከፍ ይላል። የ11ኛ እና ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለመመዝገቢያ እና ለሶስት ወራት ትምህርት እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸው 4,015 ብር መሆኑን የትምህርት ቤቱ ክፍያ ዝርዝር ያመለክታል።  

የሃ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አካዳሚ የተባለው ትምህርት ቤትም እንዲሁ በአንድ ጊዜ የሶስት ወር ክፍያ በማስከፈል ላይ እንደሚገኝ ታዝበናል። ትምህርት ቤቱ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ለመመዝገቢያ 500 ብር፣ ለትምህርት መሳሪያ 850 ብር፣  ለሶስት ወራት የትምህርት ክፍያ ደግሞ 3,500 ብር ይጠይቃል። በትምህርት ቤቱ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ የሚማሩ ተማሪዎችም ተመሳሳይ መጠን ያለው የሶስት ወራት የትምህርት ክፍያም እንዲከፍሉ ይጠበቅባቸዋል።

በግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ መጠን ላይ ቅሬታ የሚያቀርቡ ወላጆች፤ ትምህርት ቤቶቹ በኮሮና ወቅት ያለውን የኢኮኖሚ ሁኔታ እና በወላጆች ላይ ያለውን ጫና ታሳቢ ማድረግ ነበረባቸው ይላሉ። የትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ያወጣውን የትምህርት ቤት ምዝገባ መመሪያን ተላልፈው ምዝገባ እያከናወኑ ያሉ ትምህርት ቤቶች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቆ ነበር። ትምህርት ቤቶቹ ከመመሪያ ውጪ የሰበሰቡትን ገንዘብ ለወላጆች ተመላሽ እንዲያደርጉም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አሳስቧል።

ማንኛቸውም የግል ትምህርት ቤቶች ከዚህ በፊት ሲጠቀሙበት የነበረውን የክፍያ ዘዴ፤ በ2013 የትምህርት ዘመን መቀየር እንደማይችሉ የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ ከመመዝገቢያ ክፍያ ውጪ ሌሎች ተጨማሪ ክፍያዎችን ማስከፈል እንደሚያስጠይቅም አስገንዝቧል። ሚኒስቴሩ ከዚህ በተጨማሪም መንግስት የ2013 የትምህርት ዘመን መቼ እንደሚጀመር ሳያሳውቅ ማንኛቸውም ትምህርት ቤቶች ትምህርት መጀመር እንደማይችሉም አስታውቋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ማሳሰቢያን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው በየሃ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አካዳሚ የተማሪዎች ምዝገባ ሰራተኛ “መንግስት ትምህርት የሚጀመርበትን ወቅት አሳውቃለሁ አለ እንጂ ትምህርት መጀመሩ የማይቀር ነው። ወላጆች የከፈሉት ገንዘብ አንድ ጊዜ ደረሰኝ ተቆርጦበት ገቢ ሆኗል፤ መመለስ አንችልም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

የሆኑ ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት እኚሁ የምዝገባ ሰራተኛ ለትምህርት ቁሳቁስ ተብሎ የተከፈለው ክፍያ በቀጣዩ ተርም ላይ ለተማሪዎች ተቀናሽ እንደሚደረግ ገልጸው፤ ከዚያ ውጪ ያሉ ክፍያዎችን ግን ትምህርት የሚጀመርበትን ጊዜ መንግስት እስኪያሳውቅ ተዘጋጅቶ ለመጠበቅ የተደረጉ በመሆናቸው እንደማይመለሱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በወላጆች ቅሬታ የቀረበባቸውን ሌሎች ትምህርት ቤቶችን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)