የንግድ ትርኢቶች አለመኖር ያደበዘዘው እንቁጣጣሽ

በበለጠ ሙሉጌታ 

የሁለት ልጆች እናት የሆኑት የአዲስ አበባዋ ነዋሪ ወ/ሮ ብርቄ ገብረወልድ፤ በዓላት በመጡ ቁጥር የማያስታጉሉት አንድ ልማድ አላቸው። በበዓላት መዳረሻዎች በመዲናይቱ የሚዘጋጁ ባዛሮች እና የንግድ ትርኢቶችን አያመልጧቸውም።  ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እንደውም ልጆቻቸውን በመያዝ ጭምር ነበር እነዚህ ዝግጅቶች ወደሚደረጉባቸው ቦታዎች የሚሄዱት።

በንግድ ትርኢቶች እርሳቸው ለበዓል የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች እና ለልጆቿ ትምህርት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ሲገዙ፤ ልጆቻችው ደግሞ የሚያደንቋቸውን አርቲስቶች በአካል የመመልከት እድል የሚያገኙበት እንደነበር ይናገራሉ። በቴሌቪዥን እና በራዲዮ የሚተላለፉ የባዛር እና የንግድ ትርኢቶች ማስታወቂያዎች ዓመት በዓል መድረሱን ከማብሰራቸውም በላይ የበዓል ድባብ እና ድምቀት የመፍጠር አቅም እንዳላቸው ይገልጻሉ። 

ወ/ሮ ብርቄ እኒህን በመሰሉ ዝግጅቶች ሸቀጦች በተለያዩ የጥራት እና የዋጋ አማራጮች የሚገኙበት መሆኑ እንደ “ሰፊ ዕድል” ይወስዱታል። በዚህ አመት በፋሲካ እና በአዲስ ዓመት በዓል ተመሳሳይ ዝግጅቶች አለመኖራቸው ግን “የገበያ ዕድሎችን እና የዋጋ አማራጮችን አጥብቧል” ይላሉ። በበዓሎቹ ድምቀት ላይም የራሱን ጥላ አጥልቷል ይላሉ። 

ፎቶዎች፦ ፎርቹን ጋዜጣ

“በዓል የደረሰም አልመስል ብሎኛል። ከዚህ በፊት የምናውቃቸው በርካታ ነገሮች አሁን የሉም” የሚሉት ወ/ሮ ብርቄ ለዘመን መለወጫ ለመግዛት አቅደው የነበረውን የልብስ ማጠቢያ ማሽን መተዋቸውን ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ መካሄድ ያቆሙት የንግድ ትርኢቶች እና ባዛሮች፤ እንደ ወ/ሮ ብርቄ ያሉ ሸማቾችን ብቻ ሳይሆን ምርቶቻቸውን በእነዚህ ዝግጅቶች የሚሸጡ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ያገኟቸው የነበሩ መልካም አጋጣሚዎችን ያሳጣ ነው። 

በቢቢዜድ ምግብ ማምረቻ ኃላፊቱ የተወሰነ አክሲዮን ማህበር፤ በሽያጭ ተቆጣጣሪነት የሚሰሩት አቶ ኤልያስ እጅጉ ይህንን ሀሳብ ይጋራሉ። ለበዓል በሚዘጋጁ የንግድ ትርኢቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች እንደሚመጡ የሚጠቅሱት አቶ ኤልያስ፤ የዝግጅቶቹ መሰረዝ ድርጅታቸው በሽያጭም ሆነ እና ከማስታወቂያ ጋር በተያያዙ ሊያገኛቸው የሚችሉ ጥቅሞችን እንዳሳጣው ይናገራሉ። የአዲስ ዓመት በዓል በተለይ “ገበያው የሚደራበት ነው” የሚሉት የሽያጭ ተቆጣጣሪው፤ እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ የበሰሉ ምግቦችን የሚያቀርበው ድርጅታቸውን ለማስተዋወቅ ተመራጭ እንደነበር ያስረዳሉ። 

ድርጅታቸው በአንድ የንግድ ትርኢት ወይም ባዛር ላይ ሲሳተፍ እስከ 110ሺህ ብር ለቦታ ኪራይ ከመክፈሉም በላይ 100 ለሚደርሱ ሰዎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል ይፈጠር እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ኤልያስ ዘንድሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ይህ መቅረቱን ይገልጻሉ። ወረርሽኙ በክልሎች የሚካሄዱ የንግድ ትርኢት እና ባዛር ላይ እንዳይሳተፉ እንዳገዳቸውም ጭምር ያነሳሉ።

የኮሮና ወረርሽኝ የንግድ ትርኢት እና ባዛር የሚያዘጋጁ ድርጅቶችንም ክፉኛ ደቁሷል። ጆርካ ኢቨንትስ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሚሊኒየም አዳራሽ አምስት የንግድ ትርኢቶችን አዘጋጅቷል። የንግድ ትርኢቶቹ የአዲስ ዓመት፣ ገና እና ፋሲካ በዓላትን ተንተርሰው የሚዘጋጁ ነበሩ። እየተገባደደ ባለው አመት ግን ድርጅቱ ማካሄድ የቻለው በገና በዓል የነበረውን የንግድ ትርኢት ነው።   

የጆርካ ኢቨንትስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አጋ አባተ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በርካታ ዕቅዶቻቸውን እንዳበላሸባቸው ይናገራሉ። የፋሲካ እና የአዲስ ዓመት የንግድ ትርኢቶች ባለመከናወናቸው ብቻ እስከ 20 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ ማጣታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ድርጅታቸው እስካሁን ባዘጋጃቸው ዝግጅቶች ላይ “እስከ 400 ሚሊዮን ብር የሚደርስ የገንዘብ ዝውውር” እንደነበር በማስረጃነት የሚጠቅሱት አቶ አጋ፤ እነዚህ የንግድ ትርኢቶች “አራት ሺህ ለሚደርሱ ሰዎች የሰራ ዕድልን ሲፈጥሩ የቆዩ ነበሩ” ይላሉ። 

የጆርካ የንግድ ትርኢቶች በተለምዶ ከ300 እስከ 400 የሚደርስ አቅራቢዎች ይሳተፉ እንደነበር የሚያስታውሱት ስራ አስኪያጁ፤ ለአሁኑ አዲስ አመትም ከ200 በላይ የሚሆኑ የአገር ውስጥ አቅራቢዎችን ለማሳተፍ ታቅዶ እንደነበር ያስረዳሉ። ለ22 ቀናት እንዲቆይ ታስቦ በነበረው የአዲስ አመት የንግድ ትርኢት ላይ ከቻይና፣ ህንድ እና ሌሎች አገራት የሚመጡ በርካታ ተሳታፊዎች የማስመጣት እቅድ እንደነበራቸውም ይገልጻሉ። 

“በዓመት ውስጥ እንድ ወይም ሁለት ኤግዚቢሽን ላይ በመሳተፍ የዓመት ገቢያቸውን የሚሰሩ ከእኛ ጋር የቆዩ አቅራቢዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ለመመልከት ችያለሁ” ሲሉ አቶ አጋ የኮሮና ቫይረስ ወርርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  ጆርካ ኢቨንትስ ከንግድ ትርኢቶች በተጨማሪ በሚሰራቸው ሌሎች የመዝናኛ እና መሰል ስራዎች የሰራተኞችን ደሞዝ በመክፈል ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ እየሞከረ እንደሚገኝም አክለዋል።

ፎቶ፦ ፎርቹን ጋዜጣ

ሳይካሄድ በቀረው የአዲስ አመቱ የንግድ ትርኢት ላይ ከአቅራቢዎች ባለፈ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ማህበራት እራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት ዕድል አመቻችተው እንደነበር አቶ አጋ አመልክተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከመንግስት አካላት ጋር በመተባበር ጥቃቅን እና አነስተኛ አምራቾች ድጋፍ ተደርጎላቸው “ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ዕድልም ይፈጠር ነበር” ይላሉ።

በወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መንግስት ያወጀው አዋጅ “የንግድ ትርኢቶችን እንድናከናውን አይፈቅድም” የሚሉት አቶ አጋ “እኛ ኮሮና ቫይረስን ተከላክለን የንግድ ትርኢት ለማዘጋጀት የሚያስችል አቅም መፍጠር ብንችልም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ሊሳካልን አልቻለም” ብለዋል። “መንግስት ወትሮውንም ቢሆን ለዘርፉ በቂ ትኩረት አልሰጠውም። እንደ መርካቶ ያሉ ሰፊ ገበያዎች ላይ የገበያ ስርአቱ በተለመደው መንገድ ቀጥሎ የእኛ የንግድ ትር ኢቶች መከልከላቸው አግባብ አይደለም” ብለዋል፡፡

መንግስት በአማካኝ ከእያንዳንዱ የንግድ ትርኢት በአማካኝ እስከ 30 ሚሊዮን ብር ገቢ የሚያገኝ ሲሆን ዘርፉን ከዚህም በላይ በማሳደግ እና ትኩረት እንዲያገኝ በማድረግ በግሉ ዘርፍ የተሰመራውን የንግድ ማህበረሰብም ይሁን እራሱን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባው አበክረው ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)