በአዲስ አበባ በበሬ ዋጋ ላይ እስከ 10 ሺህ ብር ጭማሪ ታይቷል ተባለ

በበለጠ ሙሉጌታ

በአዲስ አበባ ከተማ የቁም እንስሳት ገበያዎች በበሬ መሸጫ ዋጋ ላይ ከአምስት ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ ጭማሪ መታየቱን ሸማቾች ገለጹ። በመዲናይቱ ገበያዎች አንድ በሬ ከ20 ሺህ እስከ 55 ሺህ ብር እየተሸጠ ነው።   

ለአዲስ ዓመት በዓል በሬ ለመግዛት በየካ ክፍለ ከተማ ጨፌ ገበያ ዛሬ ሐሙስ በተገኙበት “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አቶ ዓለሙ ተረጋ፤ የመጨሻ ዋጋው በፋሲካ በዓል ከነበረው እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ ጭማሪ እንዳለው ገልጸዋል። ላለፉት ዓመታት ከጎረቤቶቻቸው ጋር በጋራ ገንዘብ በማዋጣት እስከ 20 ሺህ ብር ባለ ዋጋ መካከለኛ በሬ ሲገዙ መቆየታቸውን ገልጸው በዚህ አመት ግን ይህን ማድረግ አለመቻላቸውን አስረድተዋል።  

“ለአዲስ ዓመት አነስተኛ በሬ በ25 ሺህ ብር ለመግዛት ተገድጃለሁ። ተጨማሪ 500 ብርም አውጥቻለሁ” ሲሉ የገበያውን ሁኔታ የሚገልጹት አቶ ዓለሙ “በዓመት በዓል ይህ ወጪ ተጨማሪ እና ከባድ ነው” ይላሉ።

በካራ ገበያ በበሬ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ብርሃኑ ቶላ፤ የበሬ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ይስማማሉ። ሆኖም ጭማሪውን “መጠነኛ ነው” ባይ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለጻ 16ሺህ የነበረው መካከለኛ በሬ አሁን እስከ 25ሺህ ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። የዋጋ ጭማሪው የተከሰተው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚገዛ አይኖርም በሚል ስጋት እና በማጓጓዣ ችግር ምክንያት ከብቶች ከተለያዩ አካባቢዎች በብዛት አለመምጣታቸው መሆኑንም ያብራራሉ። 

በአዲስ አበባ ከተማ ከብት የሚያደልቡትም ቢሆኑ በየጊዜው በሚጨምረው የእንስሳት መኖ ዋጋ እና የሼዶች ኪራይ መወደድ መቸገራቸውን የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ ይህም በበዓል ወቅት ለሚከሰተው የቁም ከብቶች የዋጋ ንረት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ። 

የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተዘዋውሮ በተመለከታቸው አቃቂ፣ ካራ እና ፈረንሳይ ጨፌ በተሰኙ የቁም ከብት መሸጫ ስፍራዎች አነስተኛ በሬ ከ20 እስከ 25ሺህ ብር ሲሸጥ ውሏል። በእነዚህ ገበያዎች መካከለኛ በሬ ከ35 ሺህ እስከ 45ሺህ ብር ባለ ዋጋ የሚገኝ ሲሆን ከፍተኛ ለሚባለው ነጋዴዎች እስከ 55ሺህ ብር ዋጋ ሲጠሩ ተስተውሏል። በአንፃራዊነት የዋጋ ቅናሽ በሚታይበት ባለ በአቃቂ በሰቃ ገበያ በሬ ከ22 ሺህ እስከ 35 ሺህ ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረ ሚካኤል መስሪያ ቤታቸው 60 ሺህ የቁም እንስሳትን ለእርድ ማዘጋጀቱንና ከዚህ ውስጥ ሶስት ሺህ የሚሆኑት በሬዎች መሆናቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የከተማይቱን ነዋሪ የስጋ ፍላጎት ለማሟላት በሶስት ሺፍት፣ ለ24 ሰዓት እየተሰራ መሆኑ የሚናገሩት ኃላፊው፤ ከብቶችን ለሚያመጡ ግለሰቦች በ30 ደቂቃ ውስጥ አርዶ እና አዘጋጅቶ የሚመለስበት መንገድ መመቻቸቱን አስረድተዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ በበዓላት ወቅት የሚከሰት የሸቀጦችን የዋጋ ንረት እና እጥረት ለመቅረፍ ሲሰራ መቆየቱን ሲገልጽ የቆየ ቢሆንም ሸማቾች አሁንም በከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ እየተማረሩ ይገኛሉ። በጉዳዩ ላይ የቢሮውን ኃላፊ አብዱልፈታህ ዮሴፍን በስልክ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብንሞክርም ሳይሳካልን ቀርቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)