የእነ እስክንድር ነጋ “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ ከተከሰሱ በኋላ በስር ፍርድ ቤት ተቀባይነት አገኘ

በተስፋለም ወልደየስ 

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ረፋዱን ክስ የተመሰረተባቸው እነ እስክንድር ነጋ፤ በስር ፍርድ ቤት አቅርበውት በነበረ አቤቱታ ከሰዓታት በኋላ ከእስር እንዲፈቱ ተወሰነላቸው። እነ እስክንድር እንዲለቀቁ ውሳኔ የሰጠው ቀደም ሲል ያቀረቡትን አካልን ነጻ የማውጣት (Habeas Corpus) አቤቱታ ሲመለከት የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፍትሃብሔር ተረኛ ችሎት ነው።

የእነ እስክንድር ጠበቆች አካልን ነጻ የማውጣት አቤቱታ ያቀረቡት፤ አቃቤ ህግ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰረት የተሰጠው የፍርድ ቤት ውሳኔ ባለመፈጸሙ “ደንበኞቻችን በፖሊስ በህገ ወጥ መንገድ ታስረው ቆይተዋል” በሚል ነበር። የተጠርጣሪዎቹን የቀዳሚ ምርመራ የምስክሮች መስማት ሂደት ይመለከት የነበረው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መዝገቡን የዘጋው ነሐሴ 12፤ 2012 ሲሆን፤ “ክስ መቼ መመስረት አለበት?” የሚለው ጉዳይ ሲያከራክር ቆይቷል። 

አቤቱታው የቀረበለት የፍትሃብሔር ተረኛ ችሎት ቀደም ሲል በነበረው ውሎው የፖሊስ እና አቃቤ ህግን ምላሽ አድምጦ ነበር። በወቅቱም አቃቤ ህግ የምስክሮች ቃል ግልባጭ የደረሰው ከውሳኔው 10 ቀናት በኋላ መሆኑን ገልጾ ክስ የመመስረቻ ጊዜው ከዚያን ቀን ጀምሮ የሚቆጠር መሆኑን በማንሳት ተከራክሯል። በጊዜ ገደቡ መሰረትም እስከ መስከረም አንድ ድረስ ክስ የመመስረቻ ጊዜ እንዳለው ጠቅሶ፤ በእነ እስክንድር ላይ “ህገ ወጥ እስር አልተፈጸመም” ብሎ ነበር።     

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው አቃቤ ህግ የቀዳሚ ምርመራ ሂደቱን ግልባጭ በቶሎ አግኝቶ ክስ መመስረት ሲገባው፣ ለ10 ቀናት ሆን ብሎ ያጓተተው፤ “እነ እስክንድርን በእስር ለማቆየት ነው” ሲሉ ተሟግተዋል። እንደተባለውም ግልባጩ ከ10 ቀናት በኋላ ለአቃቤ ህግ ደርሶት ከሆነ፤ “ሊቆጠር የሚገባው በአቃቤ ህግ ላይ እንጂ በእስር ላይ ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ መሆን የለበትም” የሚል ተጨማሪ መከራከሪያም አቅርበዋል። 

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፍትሃብሔር ተረኛ ችሎት ጉዳዩን መመርመር ያስችለው ዘንድ የቀዳሚ ምርመራ መዝገቡ እንዲቀርብለት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። የቀዳሚ ምርመራ መዝገቡን የተመለከተው ችሎቱ ዛሬ ሐሙስ ጳጉሜ 5፤ 2012 ከሰዓት የተጠርጣሪ ጠበቆች ባልተገኙበት በጽህፈት ቤት በኩል ውሳኔ ሰጥቷል። 

የቀዳሚ ምርመራውን ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ የመረመረው ችሎቱ፤ አቃቤ ህግ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰረት የታዘዘው መዝገቡ ከተዘጋበት ቀን ጀምሮ ሳይሆን ግልባጩን ከተቀበለበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑን መረዳቱን ገልጿል። በመቅረጸ ድምጽ የተቀረጸው የምስክሮች ቃል ተገልብጦ ያለቀው ውሳኔ ከተሰጠ ከሰባት ቀናት በኋላ መሆኑንም አረጋግጧል።

አቃቤ ህግ ግልባጩ ይደርሰዋል ተብሎ ከታሰበበት ከነሐሴ 20 ጊዜ ጀምሮ ያሉትን አስራ አምስት ቀናት ከግምት ውስጥ ያስገባው የፍትሃብሔር ችሎቱ፤ የአቃቤ ህግ እስከ የክስ መመስረቻ ጊዜ እስከ ትላንት ጳጉሜ 4፤ 2012 ድረስ እንደነበር ገልጿል። ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት ተጠርጣሪዎችን በእስር ማቆየቱ “ህገወጥ የሚያስብል ነው” ሲል ችሎቱ በዛሬው ውሳኔ ላይ አትቷል። በዚህም መሰረት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከዛሬ ጀምሮ አመልካቾችን ከእስር እንዲለቀቅ የፍትሃብሔር ችሎቱ ውሳኔ አሳልፏል። 

በዛሬውን የፍትሃብሔር ችሎት ቀጠሮ ያልተገኙት የእነ እስክንድር ነጋ ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ የችሎቱን ውሳኔው “ረብ የለሽ” ብለውታል። በደንበኞቻቸው ላይ ጠዋት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ፤ የከሰዓቱን ውሳኔ “ባዶ” እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።  

“የጠዋቱን ጉዳይ ያየው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የበላይ ነው። የከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ ነው በታችኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ገዢ የሚሆነው። የበላዩ ፍርድ ቤት አቶ እስክንድር በቀረበባቸው በዚህ አዲስ ምክንያት በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን ይከታተሉ እያለ፤ የታችኛው ፍርድ ቤት ግን ‘ፖሊስ የያዛቸው በህገወጥ መንገድ ስለሆነ ይለቀቁ ቢልም ትርጉም የለሽ ድካም ነው የሚሆነው” ሲሉ ጠበቃው አብራርተዋል። 

እነርሱ በፍትሃብሔር ችሎት አቤቱታ ያቀረቡት በፌደራል ፖሊስ ላይ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሄኖክ፤ ከዛሬ ጀምሮ ፌደራል ፖሊስ ኃላፊነቱን ለማረሚያ ቤት የሚያስረክብ በመሆኑ፣ የችሎቱ ‘የይለቀቁ ውሳኔ’ በፖሊስ ተፈጻሚ መሆን እንደማይችልም ያክላሉ። በዛሬው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሎ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ትዕዛዝ የተሰጠባቸው እነ እስክንድር ነጋ፤ ለመጪው ሐሙስ መስከረም 7፤ 2012 ችሎት ፊት እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ በእነ እስክንድር ላይ የመሰረተው ክስ፤ “የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በመሰናዳት እና አንዱን ወገን በሌላው ላይ በጦር መሳሪያ እንዲነሳ አነሳስተዋል” የሚል ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)