ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነገ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ሊወያዩ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በነገው ዕለት ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ሊወያዩ ነው። የነገው ውይይት ባለፈው ሐምሌ ወር ከተደረገው ተመሳሳይ ስብሰባ ወዲህ የነበሩ ሂደቶች የሚገመገሙበት ነው ተብሏል። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ነገ ማክሰኞ መስከረም 5፤ 2013 ረፋዱን ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ለዚሁ ስብሰባ፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ዛሬ ጥሪ ተደርጎላቸዋል። ጥሪው የደረሳቸው አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር፤ ስብሰባው በወቅታዊ ጉዳዩች ላይ ለመወያየት መጠራቱን እንደተገለጸላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር በበኩላቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስብሰባ እንዳለ ቢነገራቸውም፤ አጀንዳው በግልጽ እንዳልተነገራቸው ገልጸዋል።  

እኚሁ አመራር፤ ስብሰባው ላለፉት ሁለት ወራት ሲካሄድ የቆየው እና በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳተፈው ውይይት ማጠቃለያ ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ባለፈው ነሐሴ ወር በብሔራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩ ሁለት ውይይቶች ያዘጋጀው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ግን የነገው ስብሰባ ማጠቃለያ ሳይሆን ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ የመገምገሚያ መድረክ እንደሆነ አስታውቋል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም የፓርቲዎች ውይይት በአጭር ጊዜ የሚጠቃለል ሳይሆን ቀጣይ እና ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ እንደሆነ ተናግረዋል | ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

የነገው ስብሰባ “እስካሁን የመጣንበት መንገድ ምን ይመስላል? ክፍተቶች ምን ነበሩ? ምን ምን እርማቶች ያስፈልጋሉ? የሚሉትን ነገሮች ለማየት [የተዘጋጀ] ነው” ሲሉ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሂደቱም በአጭር ጊዜ የሚጠቃለል ሳይሆን ቀጣይ እና ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አነሳሽነት የተጀመረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስብሰባነት ወጥቶ ጥናታዊ ጽሁፎች በቀረቡባቸው ሁለት የአዳራሽ ውይይቶች ቀጥሎ ቆይቷል። ባለፈው ነሐሴ ወር በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተካሄዱ ሁለት ውይይቶችም ሰባት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። 

በውይይቶቹ ላይ የቀረቡት ሁሉም ጥናታዊ ጽሁፎች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቅድሚያ የሰጡትን የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ያነሱ ነበር። ነሐሴ 16፤ 2012 በተካሄደው የመጀመሪያው መድረክ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እና የኦሮሞ አቦ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር ሻምበል አማን ኦስማን ይህንኑ የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ የተመለከቱ ጽሁፎችን አቅርበዋል።

“በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የታሪክ ዳራ” በሚል ርዕስ የቀረበው የፕሮፌሰር መረራ ጥናታዊ ጽሁፍ በመጀመሪያ የውይይት መድረክ ከፍተኛ ክርክር ማስነሳቱ ይታወሳል። የኦፌኮው ሊቀመንበር በዚህ ጥናታዊ ጽሁፋቸው “በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ሀገር ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎችን” የዳሰሱ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ያጋጠሟቸውን “የታሪክ ፈተናዎች እና ያመለጧቸውን ዕድሎች” በብሔራዊ መግባባት መነጽር ለመፈተሽ ጥረት አድርገዋል። ይህ ጽሁፍ በመገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ትሥሥር ገጾች አነጋጋሪ ሆኖ ነበር።  

“በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የታሪክ ዳራ” በሚል ርዕስ የቀረበው የፕሮፌሰር መረራ ጥናታዊ ጽሁፍ በመጀመሪያ የውይይት መድረክ ከፍተኛ ክርክር አስነስቶ ነበር | ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ከአንድ ሳምንት በፊት በተካሄደው ሁለተኛው የውይይት መድረክ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ወገን የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ በብሔራዊ መግባባት ላይ የሚያጠነጥኑ ጥናታዊ ጽሁፎችን ለታዳሚያን አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የብልጽግና ፓርቲን የወከሉት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊው ዶ/ር አለሙ ስሜ “ገዢው ፓርቲ በብሔራዊ መግባባት ላይ ያለው ሚና”ን የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ በዚሁ መድረክ ላይ አቅርበዋል። 

በሁለተኛው መድረክ የነበሩ ውይይቶች “የሰከኑ” እንደነበሩ የሚናገሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ፤ በዕለቱ የነበረው ሂደት ተመሳሳይ ውይይቶችን በመጪው ጊዜያት ለማካሄድ የሚያበረታቱ አካሄዶች የታዩበት እንደነበር ይገልጻሉ። “የመጨረሻው ዙር ላይ ከመጀመሪያው በጣም በተለየ መንገድ ተስፋ የሚጣልበት ነበር። የመጀመሪያው እንደ መጀመሪያነቱ መጠን ተስፋ የሚያቆርጡ ነገሮች ነበሩ። እውነቶቹ ሳይቀበሩ፣ መቅረብ የነበረባቸው ነገሮች ቀርበው ተወያይተናል” ሲሉ አቶ ሙሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

በነገው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስብሰባ ቀጣይ ውይይቶችን ማድረግ በሚቻልበት አኳኋን ላይ ሀሳቦች እንደሚነሱ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተናግረዋል። በስብሰባው ተሳታፊዎች የሚመረጡ አዳዲስ አጀንዳዎችን ተቀብለው ጥናታዊ ጽሁፎችን የሚያቀርቡ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ሊሰየሙ እንደሚችሉም አመልክተዋል።

“ዋናው ብሔራዊ መግባባት ሁሉን አቀፍ ነው። በፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ተጀምሮ በእነርሱ የሚያልቅ አይደለም”

አቶ ሙሳ አደም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ

የብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ ቀደም ባሉ ውይይቶች በተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች በሰነድ መልክ ለማዘጋጀት መታሰቡን አቶ ሙሳ ገልጸዋል። እስካሁን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲያደርጉት የቆዩት “የፖለቲካ ውይይት ብቻ ነው” የሚሉት ሰብሳቢው፤ ይህ ማለት “ዋናው የብሔራዊ መግባባት ውይይት ተጀምሯል” ማለት እንዳልሆነ አብራርተዋል። 

“ዋናው ብሔራዊ መግባባት ሁሉን አቀፍ ነው። በፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ተጀምሮ በእነርሱ የሚያልቅ አይደለም። ነገር ግን ይሄ ለዋናው ብሔራዊ መግባባት እንደ ግብዓት እና መነሻ የሚሆን ነው” ሲሉ በመጪዎቹ ጊዜያት ባለ ድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ትልቅ የብሔራዊ መግባባት ጉባኤ እንደሚኖር አቶ ሙሳ ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)