መዓዛ መንግሥቴ ከቡከር ሽልማት የመጨረሻ ስድስት እጩዎች አንዷ ሆና ተመረጠች

The Shadow King, by Maaza Mengiste

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አሜሪካዊት ደራሲ መዓዛ መንግሥቴ ለስመ ጥሩው የቡከር ሽልማት የመጨረሻ ዙር ከታጩ ስድስት ጸሐፍት አንዷ ሆና ተመረጠች። መዓዛ ለሽልማቱ የታጨችው “ዘ ሻዶው ኪንግ” የሚል ርዕስ በተሰጠው እና መቀመጫውን በስኮትላንድ ኤደንብራ ባደረገው ካነንጌት ቡክስ አሳታሚ ለንባብ በበቃው መጽሀፍ ነው።

በስነ ጹሁፍ ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው “ዘ ቡከር ፕራይዝ”፤ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተፅፈው በዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ ለሕትመት የበቁ የልቦለድ ስራዎችን የሚሸልም ነው። መዓዛ  ለሽልማቱ ከታጩ ስድስት የመጨረሻ እጩዎች አንዷ ሆና መመረጧን “የማይታመን ነው” ብላለች። 

“ከሰማሁ ጀምሮ እየተንቀጠቀጥኩ ነው። ልክ እንደ ሰማሁ ለረዥም ጊዜ ጮህኩና እንደገና በዝምታ ተዋጥኩ። በፍጹም ላምን አልቻልኩም። እጅግ ከፍተኛ ክብር ተሰምቶኛል። ይህን በፍጹም አልጠበቅኩም። የምናገረው ሁሉ ጠፍቶኛል” ስትል ሽልማቱ የፈጠረባትን ስሜት ዛሬ ማክሰኞ ምሽት በቪዲዮ ኮንፍረንስ በተደረገ ስነ ስርዓት ላይ ገልጻለች። 

ደራሲዋ ለሽልማት የታጨችበት “ዘ ሻዶው ኪንግ” ጣሊያን ከ85 አመታት በፊት ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ሴት የነጻነት ታጋዮች የነበራቸውን ግዙፍ ግን ደግሞ በታሪክ ፊት ቸል የተባለ ሚና ይተርካል። መዓዛ እንደተናገረችው መጽሐፉን ስትጀምር ኢትዮጵያውያን ከፋሽስት ጣልያን ባደረጉት ተጋድሎ ላይ ልታተኩር ብታቅድም በጥናት እና ምርምር ወቅት ያገኘቻቸው መረጃዎች አስደናቂ ሆነው የትኩረት አቅጣጫዋን አስቀይረዋታል።

“ሴቶች ምግብ እና ውሃ ተሸክመው፣ የቆሰሉትን እያከሙ፣ የሞቱትን እየቀበሩ ወንዶቹን ይከተሉ እንደነበር ሳውቅ ካሰብኩት በላይ በጦርነቱ ተሳትፈው ነበር ማለት ጀመርኩ። ከዚያ በሰራሁት ጥናት ሴቶች በእርግጥም በአውደ ግንባሮች እንደነበሩ ተረዳሁ። ይህ ለእኔ መጽሐፉን ሙሉ በሙሉ ቀየረው። ‘ዘ ሻዶው ኪንግ’ ህይወት የዘራው ከዚያ በኋላ ነበር” ብላለች መዓዛ።

ደራሲዋ በመጽሐፉ ላይ የተጠቀመችው አጻጻፍ እና የቋንቋ ብቃት በሀያሲያን እና ዳኞች አድናቆትን አስገኝቶለታል። የአሜሪካው ፐብሊክ ራዲዮ (NPR) የመጻሕፍት ሐያሲ እና ጸሐፊ ሚካኤል ሻውብ “የልቦለዱ ኮኮብ የመዓዛ መንግሥቴ ድንቅ አጻጻፍ ነው። ይህም ‘ዘ ሻዶው ኪንግ’ን ለማስቀመጥ ፋታ የማይሰጥ አድርጎታል” ሲል አሞካሽቷል።   

“እንደ ጸሀፊ በመዓዛ እንከን የለሽ የታሪክ አወቃቀር ተደምሚያለሁ። እንደ ተራበ አንባቢ በዚያ የታሪክ መዋቅር ውስጥ ግለሰባዊ፣ ለስሜት ቅርብ ግን ደግሞ አሳዛኝ ታሪክ ያላቸው የሚያበሩ፣ የሚተነፍሱ፣ ነዋሪ ገጸ ባሕሪያት ማግኘቷን ወድጄላታለሁ”

ደራሲ ሊ ቻይልድ- ከቡከርስ ሽልማት አምስት ዳኞች መካከል አንዱ 

ከቡከርስ ሽልማት አምስት ዳኞች መካከል አንዱ የሆኑት ደራሲ ሊ ቻይልድ ለመዓዛ የቋንቋ አጠቃቀም አድናቆታቸውን ገልጸው፤ መጽሐፏ ከአመቱ ምርጥ ልብወለዶች አንዱ ሆኖ መመረጡ “ተገቢ ነው” ብለዋል። ደራሲው ይህን የተናገሩት ዛሬ ማክሰኞ ማምሻውን ስድስቱ የመጨረሻ እጩዎች ይፋ መሆናቸውን በማስመልከት ሸላሚው ተቋም ባዘጋጀው የኢንተርኔት መርሐ ግብር ላይ ነው።

“እንደ ጸሀፊ በመዓዛ እንከን የለሽ የታሪክ አወቃቀር ተደምሚያለሁ። እንደ ተራበ አንባቢ በዚያ የታሪክ መዋቅር ውስጥ ግለሰባዊ፣ ለስሜት ቅርብ ግን ደግሞ አሳዛኝ ታሪክ ያላቸው የሚያበሩ፣ የሚተነፍሱ፣ ነዋሪ ገጸ ባሕሪያት ማግኘቷን ወድጄላታለሁ” ብለዋል ሊ ቻይልድ።

የመዓዛ ሁለተኛ መጽሐፍ የሆነው “ዘ ሻዶው ኪንግ” ለመጨረሻው ዙር የቡከርስ ሽልማት ውድድር ያለፈው ከ162 ልቦለዶች ጋር ተወዳድሮ መሆኑ በዛሬው ስነ ስርዓት ላይ ተገልጿል። መጽሐፉን ለመጨረሻው ዙር ያጨው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ገጣሚ ለምን ሲሳይ የተካተተበት አምስት አባላት ያሉብት የዳኞች ኮሚቴ ነው። 

የአመቱ የዳኞች ሊቀመንበር የሆኑት ማርጋሬት በዝቢ ለውድድር ቀርበው ስለነበሩ መጽሐፍት ሲያስረዱ “አብዛኞቹ ጠቃሚ፣ አንዳንድ ጊዜ እንግዳ፣ ተመሳሳይ እና የሚታወቁ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ናቸው” ብለዋል።  “ምርጦቹ ልብወለዶች ብዙውን ጊዜ ማህበረሰቦቻችንን ስለ ዓለማችን ኢፍትኃዊነት እና መወዛገቧ ብቻ ሳይሆን ስለ ከባቢ አየር ለውጥ፣ ስለተዘነጉ ሕብረተሰቦች ያለፉ ዘመናት፣ ዘረኝነት ወይም ስለ አብዮት አስፈላጊነት ለጠቃሚ ውይይት ይጋብዛሉ” ሲሉ ፋይዳቸውን አስረድተዋል። 

ለቡከርስ ሽልማት የታጩት እነዚህ መጽሐፍት ከመስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ ለሕትመት የበቁ ናቸው። ከመጽሐፍቱ ደራሲያን መካከል በቅርቡ በዚምባብዌ የበረታውን ሙስና በመቃወም ሰልፍ በማድረጓ በአገሪቱ መንግሥት ታስራ የተፈታችው ፂፂ ዳንጋሬምባ ትገኝበታለች። አሜሪካውያኑ ዲያነ ኩክ፣ አቭኒ ዶሺ እና ብራንደን ቴይለርን ሌሎቹ ዕጩ ተሸላሚ ደራሲያን ናቸው።  

በእጩነት ከቀረቡት መካከል የስኮትላንድ እና አሜሪካ ጥምር ዜግነት ያለው ዳግላስ ስቱዋርት ብቻ መገኘቱ አነጋግሯል። የዳኞች ሊቀመንበሯ ማርጋሬት በዝቢ “የሰዎችን ቪዛ ወይም ፓስፖርት አልፈተሽንም። መጻሕፍቱን ብቻ ነው የተመለከትንው” ብለዋል። “እያንዳንዱ መጽሐፍ መስፈርቱን እንዳሟላ እናውቃለን” ሲሉም አክለዋል። 

የቡከርስ ሽልማት በእንግሊዘኛ ተናጋሪው ዓለም ከፍተኛ ተቀባይነት እና ክብር የሚሰጠው ሲሆን ላለፉት 50 አመታት ምርጥ ለተባሉ ልብወለዶች እውቅናን እና ተነባቢነትን እንደሚያጎናጽፍ ይነገርለታል። ባለፈው አመት ካናዳዊቷ ገጣሚ ማርጋሬት አትውድ እና ብሪታኒያዊቷ በርናርዲን ኢቫሪስቶ ሽልማቱን በጥምረት ሲያሸንፉ የመጻሕፍቶቻቸው ሽያጭ በከፍተኛ ብዛት ጨምሯል። 

ሽልማቱ ከሚሰጠው ዓለም አቀፍ እውቅና ባሻገር ለተሸላሚ ደራሲያኑ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ያበረክታል። ውድድሩን በአሸናፊነት የሚያጠናቅቅ ደራሲ 50,000 ፓውንድ የሚሸለም ይሆናል። በእጩነት የተመረጡ ደራሲያን ደግሞ እያንዳንዳቸው 2,500 ፓውንድ ያገኛሉ። የዚህ ዓመት የቡከርስ ሽልማት አሸናፊ በመጪው ሕዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም ይታወቃል። የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ለንደን በሚገኘው ራውንድ ሐውስ የትወና እና የሙዚቃ ድግስ ማቅረቢያ አዳራሽ ከቢቢሲ ጋር በመተባበር ይካሄዳል።

ለስመ ጥር ሽልማት በመታጨት በኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ ታሪክ ደማቅ ስም ያስመዘገበችው መዓዛ ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ ነው። ደራሲዋ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው የኩዊንስ ኮሌጅ የፉልብራይት ስኮላር እንዲሁም የፈጠራ አጻጻፍ (Creative Writing) እና የሥነ ጽሁፍ ትርጉም መርሐ ግብር (Literary Translation programme) ፕሮፌሰር ነች። 

ከዚህ ቀደም ታትሞ ለንባብ የበቃው “ቢኒትዝ ዘ ላየንስ ጌዝ (Beneath the Lion’s Gaze) የተባለ የመዓዛ ልቦለድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን “ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ” ምርጥ ካላቸው አስር የአፍሪካ መጻሕፍት አንዱ ነበር። የመዓዛ ሥራዎች “ዘ ኒው ዮርከር” እና “ግራንታ” በተባሉ መጽሔቶች እንዲሁም በ“ኒውዮርክ ታይምስ” ጋዜጣ ለሕትመት በቅተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)