በአዲስ አበባ ከባድ ተሽከርካሪዎችን በተከለከለ ሰዓት በሚያንቀሳቀሱ ላይ እስከ 6 ሺህ ብር ቅጣት ተጣለ

በበለጠ ሙሉጌታ 

በአዲስ አበባ ከተማ ከቀኑ 10 እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት ድረስ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ሲያንቀሳቅሱ የሚገኙ አሽከርካሪዎች ከ500 እስከ ስድስት ሺህ ብር እንደሚቀጡ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው የቅጣት መጠኑን ተግባራዊ ያደረገው በከተማይቱ በስራ መውጫ ሰዓታት ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅና አደጋ ለመቀነስ ባወጣው አዲስ መመሪያ ነው።

የከባድ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመወሰን በወጣው በዚሁ መመሪያ መሰረት፤ የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ሳያወጡ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በተከለከለው ሰዓት ወደ ከተማዋ ማስገባት እና ማንቀሳቀስ በአሽከርካሪዎች ላይ ቅጣት ያስከትላል። በዋና መንገድ ላይ ጭነት መጫንና ማውረድ ተግባር በሚፈጽሙ ላይም ቅጣቱ ተግባራዊ እንደሚደረግ መመሪያው ያስቀምጣል። 

የመጫን አቅማቸው 2.5 ቶን እና ከዚያ በላይ በሆኑ ተሽከርካሪዎችን ይመለከታል የተባለውን ይህን መመሪያ የሚጥሱ አሽከርካሪዎች እንደ ጥፋታቸው ክብደት እና ድግግሞሽ ከ500 እስከ ስድስት ሺህ ብር እንደሚቀጡ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 6፤ 2013 ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። ጥፋተኛ አሽከርካሪዎች ከሚጣልባቸው የገንዘብ ቅጣት በተደራቢነት፤ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዳቸው ከአንድ እስከ ሶስት ወር እንደሚታገድባቸው ቢሮው ገልጿል።

አዲሱን መመሪያ ተላልፈው የሚገኙ አሽከርካሪዎች ጥፋቱን ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጸሙ እንደሆነ አንድ ሺህ ብር እንደሚቀጡ በመመሪያው ተቀምጧል። ጥፋቱ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ የቅጣት መጠኑ ወደ ሁለት ሺህ ብር ከፍ እንደሚልም መመሪያው ያሳያል። አንድ አሽከርካሪ የተከለከለውን ድርጊት ከሁለት ጊዜ በላይ ፈጽሞ የሚገኝ ከሆነ ከሚጣልበት ሶስት ሺህ ብር ቅጣት በተጨማሪ፤ የመንጃ ፈቃዱም ለአንድ ወር እንደሚታገድ መመሪያው ያስጠንቅቃል።

ጊዜው ያለፈበት የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ተጠቅመው ከባድ ተሽከርካሪዎችን ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ እና የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎችም ከቅጣት እንደማያመልጡ የትራስንፖርት ቢሮው አስጠንቅቋል። ይህን ጥፋት ለመጀመሪያ ጊዜ ፈጽመው የተገኙ አሽከርካሪዎች አምስት ብር እንደሚቀጡ በመመሪያው መስፈሩን የገለጸው ቢሮው ድርጊቱ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ የቅጣት መጠኑ በእጥፍ እንደሚጨምር ጠቁሟል። ጊዜው ያለፈበት ፍቃድ ይዘው ለሶስተኛ ጊዜ የተገኙ አሽከርካሪዎች ከሚደርስባቸው የአራት ሺህ ብር ቅጣት በተጨማሪ የመንጃ ፈቃዳቸው ለሁለት ወራት ይታገዳሉ ተብሏል።

የተሰረዘ፣ የተደለዘ ወይም አስመስሎ የተሰራ የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ይዞ መገኘት እንደሚያስቀጣ ያስገነዘበው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የመንቀሳቀሻ ፈቃዱን ለሌላ አካል አሳልፎ መስጠትም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚያስከትል አስታውቋል። በዚህ ሁኔታ የተገኘ አሽከርካሪ ላይ የሚጣለው ቅጣት ስድስት ሺህ ብር እንደሆነም ቢሮው ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)