አቶ ልደቱ አያሌው ጠበቆቻቸውን አሰናበቱ

በተስፋለም ወልደየስ  

የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው በቢሾፍቱ ከተማ ፍርድ ቤት የወከሏቸውን ጠበቆች አሰናበቱ። አቶ ልደቱ እርምጃውን የወሰዱት ከዚህ በኋላ በከተማው ፍርድ ቤት የህግ ክርክር ማድረግ ባለመፈለጋቸው እንደሆነ ዛሬ ረቡዕ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል። 

ፖሊስ በአቶ ልደቱ ላይ ከፍቶት የነበረውን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጉዳይን ሲመለከት የቆየው የቢሾፍቱ ከተማ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ በሁለት ሳምንት ውስጥ ክስ እንዲመሰረት በማዘዝ መዝገቡን ዘግቶ ነበር። ፍርድ ቤቱ ውሳኔው ካሳለፈ ዛሬ አስራ ሰባተኛ ቀኑ መሆኑን የሚጠቅሱት የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ፤ ይህን መሰረት አድርገው ዛሬ ለችሎቱ ማመልከቻ ማስገባታቸውን ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የማመልከቻው ይዘት “አቃቤ ህግ በተሰጠው ጊዜ ክስ መመስረት ስላልቻለ አቶ ልደቱ በነጻ ሊለቀቁ ይገባል” የሚል እንደሆነ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ገልጸዋል። የፍርድ ቤቱ ዳኞች በዘጉት መዝገብ ላይ የቀረበውን ማመልከቻ ለመመልከት አንገራግረው እንደነበር የሚናገሩት አቶ አዳነ፤ በስተመጨረሻ በጽህፈት ቤት በኩል ማመልከቻውን መርምረው ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን አብራርተዋል። ፖሊስ እና አቃቤ ህግ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ምላሽ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ የሰጠው ፍርድ ቤቱ፤ ይህንኑ ለመመልከት ለመጪው ሰኞ መስከረም 11፤ 2013 ቀጠሮ መስጠቱንም ጠቁመዋል። 

እርሳቸው በሌሉበት በጠበቆቻቸው በኩል ለቀረበው ማመልከቻ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ የሰሙት አቶ ልደቱ፤ ከዚህ በኋላ በከተማው ፍርድ ቤት በሚካሄድ የህግ ክርክር መቀጠል እንደማይፈልጉ ማስታወቃቸውን አቶ አዳነ ገልጸዋል። ይህንኑ ሀሳባቸውን በጹሁፍ አስፍረው እንደሰጧቸውም የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል። 

በኢዴፓ በኩል የተሰራጨው የአቶ ልደቱ ደብዳቤ፤ እውቁ ፖለቲከኛ በነጻ የጥብቅና አገልግሎት ሲሰጧቸው የነበሩ የህግ ባለሙያዎችን ያሰናበቱበትን ምክንያት በዝርዝር ያስረዳል። ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም በቀረቡባቸው ስምንት የችሎት ውሎዎች “ተገቢ ያልሆኑ” ሲሉ የጠሯቸው የፖሊስ እና የአቃቤ ህግ ጥያቄዎች “ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት” ማግኘታቸውን በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል። ሆኖም እርሳቸው ያቀረቧቸው ህጋዊ የመብት ጥያቄዎች “አንድም ጊዜ” ተቀባይነት አለማግኘታቸውን በንጽጽር አንስተዋል። 

“የምርመራ ፋይሌ በፍርድ ቤቱ በተዘጋበት እና ምንም አይነት የጊዜ ቀጠሮ ባልተሰጠኝ ሁኔታ የዋስ መብት እንዳይኖረኝ ተከልክያለሁ” በማለት ደረሰብኝ ያሉትን የመብት ጥሰት በደብዳቤያቸው ያሰፈሩት አቶ ልደቱ፤ “በዚህም ምክንያት በፖለቲካ አመለካከቴ እንድታሰር የወሰኑብኝ የፖለቲካ ሰዎች፤ ስለወደፊቱ ዕድሌም የሚወስኑትን የፖለቲካ ውሳኔ በእስር ላይ ሆኜ እየተጠባበቅኩ እገኛለሁ” ብለዋል። 

የእርሳቸውን የዋስትና መብት ለማስከልከል የቀረበባቸው ዋና ማስረጃ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ያቀረቡት ሰነድ እና ታትሞ ያልተሰራጨው መጽሀፋቸው ረቂቅ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ልደቱ፤ “ይህ የሚያሳየውም የህግ ሳይሆን የፖለቲካ እስረኛ መሆኔን ነው” ሲሉ በደብዳቤያቸው ሞግተዋል። “በአጭሩ እኔ የታሰርኩት ለምን ወንጀል ፈጸምክ ተብዬ ሳይሆን ለምን አሰብክ ተብዬ ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

በአቶ ልደቱ ላይ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ የቆየው የኦሮሚያ ፖሊስ፤ ፖለቲከኛውን የጠረጠራቸው የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ሰኔ 23 እና 24፤ 2012 በቢሾፍቱ ከተማ የተቀሰቀሰውን ሁከት በማስተባበር እና በገንዘብ በመደገፍ መሆኑን በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤት ሲገልጽ ቆይቷል። ያለፉትን ስምንት የችሎት ሂደቶች በዛሬው ደብዳቤያቸው መለስ ብለው የቃኙት ተጠርጣሪው፤ በሂደቱ የታዘቡት “በፖለቲካ እና በህግ መካከል ክርክር እየተካሄደ መሆኑን” እንደነበር ጠቁመዋል። በሂደቱም “ሁልጊዜም አሸናፊ እየሆነ ያለው ህግ ሳይሆን ፖለቲካ ነው” ሲሉም በፍትህ ሂደቱ ላይ ያላቸው ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል። 

ከዚህ በኋላ የሚካሄደውን ክርክር “ትርጉም የሌለው” ሲሉ የጠሩት አቶ ልደቱ፤ “ህግ የፖለቲካ መሳሪያ በሆነበት ሁኔታ በህግ ክርክር መብትን ማስከበር ስለማይቻል ከአሁን በኋላ ግዴታዬን ለመወጣት ቀጠሮ ሲሰጠኝ በችሎት ፊት ከመገኘት ባለፈ የህግ ክርክር የማድረግ ፍላጎት የለኝም” ሲሉ በፓርቲያቸው በኩል ባሰራጩት ደብዳቤያቸው አስታውቀዋል። ለአቶ ልደቱ በነጻ ጥብቅና ሲቆሙላቸው የነበሩ ሶስት የህግ ባለሙያዎች እንደነበሩ የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አስታውሰዋል። 

በፌደራል ፖሊስ አባላት ሐምሌ 17፤ 2012 በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ልደቱ የዚያኑ ዕለት ወደ ቢሾፍቱ ተወስደዋል። ለሁለት ጊዜ ያህል ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ በፍርድ ቤት ውድቅ የተደረገባቸው ተቃዋሚ ፖለቲከኛው፤ የጊዜ ቀጠሮ ችሎቶቻቸውን በእስር ሆነው ሲከታተሉ ቆይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)