ኢሰመኮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ ግድያዎች ተፈጽመዋል አለ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጸሙ ጥቃቶች፤ ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ ግድያዎች ተፈጽመዋል አለ። ቢያንስ በሁለት ዙር ተፈጽመዋል በተባሉ በእነዚህ ጥቃቶችም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን ኮሚሽኑ አረጋግጬያለሁ ብሏል። 

ኢሰመኮ ይህን ያለው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተከሰተውን ግድያ እና መፈናቀል አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 7፤ 2013 ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ነው። በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ መደፍረሶች መታየታቸውን የጠቆመው የኮሚሽኑ መግለጫ ይህን ተከትሎም ያጋጠሙ ክስተቶች እጅግ እንዳሳሰቡት አስታውቋል። 

ጥቃት የተፈጸመባቸው የክልሉ አካባቢዎች በመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ የሚገኘው አጳር ቀበሌ እና በወንበራ ወረዳ መልካ ቀበሌ መሆናቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አመልክቷል። ከእነዚህ አካባቢዎች “እጅግ አሳሳቢ መረጃዎች” እየደረሱት መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ በቦታዎቹ ላይ ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግስት ማረጋገጡንም ጠቅሷል። ጥቃቶቹ የተፈጸሙት ከሳምንት በፊት ጳጉሜ 1 እና 2፤ 2012 እንደዚሁም ባለፈው እሁድ መስከረም 3፤ 2013 መሆናቸውንም አክሏል።

“ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ገለልተኛ፣ ፈጣን እና ውጤታማ ምርመራዎችን በማካሄድ፤ ግድያው በተከሰተባቸው ሁኔታዎች ላይ የጥፋተኞችን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጡ [እናሳስባለን]”

– የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

በክልሉ “ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ የደረሱትን ጥቃቶች፣ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ሙሉ በሙሉ አወግዛለሁ” ያለው ኮሚሽኑ፤ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት እና ሀገሪቱ በተቀበለቻቸው ሌሎችም ሰብአዊ መብት ሰነዶች የተደነገጉት በሕይወት የመኖር መብቶች እንዲከበሩ ጠይቋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ማጋጠማቸውን የጠቀሰው መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተቋም፤ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ “ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ገለልተኛ፣ ፈጣን እና ውጤታማ ምርመራዎችን በማካሄድ፤ ግድያው በተከሰተባቸው ሁኔታዎች ላይ የጥፋተኞችን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጡ” አሳስቧል። 

ኢሰመኮ በክልሉ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በመከላከያ ሰራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በክልል የጸጥታ ኃይሎች እየተደረገ ያለውን ጥረት በመግለጫው በአዎንታዊነት ጠቅሷል። አካባቢውን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት በጥቃቶቹ ከተፈናቀሉ ሰዎች መካከል 300 ያህል የሚሆኑት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የክልሉ መንግስት ዋቢ ያደረገው መግለጫው፤ የሚመለከታቸው የክልሉ መንግስት አካላት ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ወደ ቀደመ ህይወታቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ጥሪ አቅርቧል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)