በተስፋለም ወልደየስ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር በሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ የሀገሪቱ ሰላም እና ደህንነት የሚፈለግ ከሆነ እርሳቸው እና አብረዋቸው የተከሰሱ ሰዎች በዋስትና ወጥተው በመጪው ምርጫ ላይ መሳተፍ እንደሚገባቸው ለፍርድ ቤት ተናገሩ። አቶ እስክንድር ይህን ያሉት የዋስትና ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ አቃቤ ህግ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላቀረበው ክርክር በሰጡት ምላሽ ነው።
ዛሬ ሐሙስ መስከረም 7፤ 2013 ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ እስክንድር እና ሌሎች አራት ተከሳሾች በአቃቤ ህግ የቀረበባቸው ክስ ሲነበብ በችሎት ሆነው ተከታትለዋል። በሌሉበት የተከሰሱ ሁለት ተጠርጣሪዎችን ጨምሮ በሰባት ሰዎች ላይ አቃቤ ህግ ክሱን የመሰረተው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ቢሆንም፤ ክሱ በችሎት በንባብ አልቀረበም ነበር።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ የተነበበው 13 ገጾች ያሉት የአቃቤ ህግ ክስ ሰነድ፤ በሁለት ተከፍሎ የቀረበ ነው። “አንዱን ወገን በሌላው ላይ በጦር መሳሪያ እንዲነሳ በማነሳሳት፤ በመንግስት ላይ የሚደረግ ወንጀልን” የሚመለከተው የመጀመሪያው ክስ፤ በአቶ እስክንድር እና በሌሎች አራት ተጠርጣሪዎች ላይ የቀረበ ነው። ሁለተኛው እና “የሽብር ወንጀል ለመፈጸም መሰናዳት” የሚለው ክስ ደግሞ አቶ እስክንድር እና በሌሉበት የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች የተወነጀሉበት ነው።
በሌሉበት ጉዳያቸው እየታየ ካሉት ከእነዚህ ሁለት ግለሰቦች መካከል በክስ ሰነዱ በሰባተኛ ደረጃ በተቀመጡት ግለሰብ ላይ አቶ እስክንድር ያላቸውን ጥርጣሬ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ አንስተዋል። አቃቤ ህግ አቶ ፍትዊ ገብረመድህን የተባሉት እኚህን ተከሳሽ የመረጠው “ፖለቲካዊ ግርታን ለመፍጠር ነው” ብለዋል። አቃቤ ህግ በክስ መመስረቻ ሰነዱ ላይ የጠቀሳቸው እኚህ ተከሳሽ “ህጋዊ ስማቸው” መሆኑን እንዲያረጋግጥም ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱ ይህን ተከትሎ ያደመጠው ለተከሳሾች “የዋስትና መብት ሊፈቀድ ይገባል፤ አይገባም” በሚል አቃቤ ህግ እና የተከሳሽ ጠበቆች ያደረጉትን ክርክር ነው። የዋስትና መብት ህገ መንግስታዊ መርህ መሆኑን የጠቆሙት ጠበቆች፤ መርሁን የሚቃረን ነገር በአቃቤ ህግ በኩል የሚቀርብ ከሆነ መከራከሪያቸውን እንደሚያቀርቡ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
የዋስትና መብት በህገ መንግስቱ መከበሩን የጠቀሰው አቃቤ ህግ፤ ሆኖም በህግ አግባብ ሊገደብ የሚችልባቸውን ምክንያቶች ዘርዝሯል። ክርክሩን በማስረጃ በማስደገፍም የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርዓት ሁለት አንቀጾችን እና ሁለት የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎችን ጠቅሷል።
ተከሳሾች የፈጸሙት ወንጀል ሞት የሚያስፈርድ ከሆነ አሊያም 15 ዓመት እና ከዚያ በላይ በሆነ ጊዜ በጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ከሆነ ዋስትና ሊከለከል እንደሚችል አቃቤ ህግ ለችሎት አስረድቷል። ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ ለ14 ሰዎች ሞት እና ከ187 ሚሊዮን ብር በላይ ለሆነ የንብረት ውደመት ተጠያቂ መሆናቸውን የገለጸው አቃቤ ህግ ይህም እስከ 25 ዓመት ሊያስፈርድባቸው እንደሚችል አብራርቷል። አንደኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ እስክንድር ከዚህ በተጨማሪ የተጠቀሰባቸው የሽብር ወንጀል ክስ 12 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሚያስቀጣ መሆኑም አመልክቷል።
አቃቤ ህግ ተከሳሾቹ ዋስትና ቢፈቀድላቸው ሌላ ወንጀል ሊፈጽሙ እንደሚችሉም በማንሳት ተከራክሯል። ተከሳሾቹ ስልጣን እንያዛለን በማለት ስስ የሆኑ እና የሰዎችን ስሜት የሚቀሰቅሱ፣ ብሔርን እና ሃይማኖትን የሚያጋጩ ቅሰቀሳዎችን ያደርጉ እንደነበር ጠቅሷል። “ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም” በማለትም አባሎቻቸው ራሳቸውን ለተልዕኮ እንዲያዘጋጁ ጥሪ ማድረጋቸውንም ተናግሯል። ተከሳሾቹ “ሌላ ትልቅ ወንጀል ለመፈጸም በዝግጅት ላይ ነበሩ” ያለው አቃቤ ህግ፤ “በዚህም ምክንያት ሌላ ወንጀል አይፈጽሙም ለማለት አይቻልም” ሲል ዋስትና ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ ተሟግቷል።
“የዋስትና ጉዳይ መተርጎም ያለበት ከወንጀል ህጉ ዓላማ አንጻር ነው” ያለው አቃቤ ህግ፤ የወንጀል ህጉ ዓላማም የሰዎችን ሰላም እና የሀገርን ደህንነት ማስጠበቅ እንደሆነ ገልጿል። “ተከሳሾቹ የፈጽሙት ድርጊት በሰው ሰላም እና በሀገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚያመጣ ነው” ሲል ለፍርድ ቤቱ የተናገረው ከሳሽ አቃቤ ህግ፤ “ለተከሳሾቹ ዋስትና መፍቀድ የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ እንደመጣል ነው” ሲል ተከራክሯል። በእነዚህ ምክንያቶች ዋስትና ጥያቄውን የተቃወመው አቃቤ ህግ፤ ተከሳሾች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ ጠበቆች በአቃቤ ህግ መከራከሪያ ላይ ምላሽቸውን እንዲያቀርቡ በተከታይነት እድል ሰጥቷል። አቶ እስክንድርን እና አብረዋቸው የተከሰሱ ሶስት ተጠርጣሪዎችን የወከሉት አቶ ጌታነህ ኃይለማርያም እና አቶ ሄኖክ አክሊሉ የአቃቤ ህግን ማብራሪያ በመቃወም መከራከሪያቸውን አቅርበዋል።
ጠበቃ ጌታነህ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት ለማክበር መነሻ ማድረግ ያለበት በሕግ መንግስቱ አንቀጽ 19 (6) የተቀመጠውን መርህ መሆኑን ጠቅሰዋል። አቃቤ ህግ የጠቀሰው የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግ አንቀጽ 63 (1) ትርጉም ሊሰጥበት የሚገባው፤ ከሕገ መንግስቱ አንጻር መሆኑንም አስረድተዋል። የእነርሱ ግንዛቤ ሕገ መንግስቱ ይህንን የስነ ስርዓት ህግ አንቀጽ “በዝምታ እንዳለፈው አሊያም እንደሻረው” መሆኑንም የገለጹት ጠበቃው ከዚህ አንቀጽ ይልቅ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት እና የፖለቲካ ስምምነቶች ከግንዛቤ ውስጥ ሊገቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አቃቤ ህግ ከስነ ስርዓት ህጉ የጠቀሰው ሌላው አንቀጽ 67ም ቢሆን ከደንበኞቻቸው ማንነት ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑን ጠበቃው አመልክተዋል። ተከሳሾቹ ቋሚ አድራሻ ያላቸው እና በህጋዊ መንገድ የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው ሀገር እና ህዝብን ለማገልገል እየሰሩ ያሉ መሆናቸውንም አንስተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደንበኞቻቸው ደረቅ ወንጀል በመፈጸም የሚታወቁ እንዳይደሉ ጠቅሰዋል። በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ ከስነ ስርዓት ህጉ የቀረቡ ሁለት አንቀጾችን እንዲያልፋቸው ጠይቀዋል።
ተከሳሾቹ “ሌላ ወንጀል ለመፈጸም ይችላሉ” በሚል በአቃቤ ህግ በኩል ለቀረበው መከራከሪያም ጠበቃው ምላሽ ሰጥተዋል። “ወንጀል አይፈጽሙም ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው” ተብሎ በቀረበ ምክንያት፤ “አንድ ሰው የዋስትና መብቱን ሊያጣ አይገባም” ያሉት አቶ ጌታነህ፤ ይህን በተመለከተ በስነ ስርዓት ህጉ ላይ የተቀመጠውም ቢሆን መተረጎም ያለበት “በጠባቡ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል። በአቃቤ ህግ የተጠቀሱ የሰበር ችሎት ውሳኔዎችም አሁን ከቀረበው ክስ ጋር “ጨርሶ የተያያዘ አይደለም” ሲሉ ሞግተዋል።
ደንበኞቻቸው የቀረበባቸው ክስ “በከፍተኛ ሁኔታ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው” ያሉት ጠበቃ ጌታነህ፤ ፍርድ ቤት ይህን ከግምት ማስገባት እንዳለበት አስረድተዋል። “ክሱ ደንበኞቻችንን ከፖለቲካዊ መድረክ ገለል ለማድረግ ተያይዞ የመጣ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ጠበቃ ሄኖክ በበኩላቸው ተከሳሾች “ነጻ ሆነው የመገመት መብት” እንዳላቸው አስታውሰው፤ በአቃቤ ህግ መከራከሪያ ሲቀርብ የነበረው ግን ከዚህ በተቃራኒ እንደነበር ለችሎቱ ገልጸዋል። አቃቤ ህግ ሲጠቀምባቸው የነበሩ አገላለጾች “የፍትህ ስርዓቱን ጫና ውስጥ የመክተት” እንደነበርም ተናግረዋል።
አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ “ወንጀል ለመፈጸም መሰናዳት” መሆኑ የጠቀሱት ጠበቃው፤ በዝግጅት ላይ ባለ ነገር “በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ምንም የደረሰ ነገር የለም” ማለት መሆኑን አብራርተዋል። በዝግጅት ደረጃ ነው በተባለ ወንጀል “መሰረታዊ መብት ሊገደብ አይገባም” ብለዋል።
ጠበቃው የሀገር ሰላምን እና ደህንነት በተመለከተ አቃቤ ህግ ያነሳውን ሀሳብም የተቃረነ አስተያየት ሰጥተዋል። “ተከሳሾቹ ብዙ ደጋፊ ያላቸው ናቸው” ያሉት አቶ ሄኖክ “እንደውም ተከሳሾቹ በመታሰራቸው ሀገር አትረጋጋም” ሲሉ ለችሎቱ ተናግረዋል። በሀገሪቱ በየቀኑ ሰው እየሞተ መሆኑን ያስታወሱት ጠበቃው፤ ይህ እየሆነ ያለው ተከሳሾቹ ባለመታሰራቸው አለመሆኑን ጠቁመዋል። አቶ ሄኖክ በመጨረሻም ደንበኞቻቸው ቋሚ አድራሻ እና ልጆች ያሏቸው፣ የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው እንደዚሁም ሰላማዊ እና ህጋዊ ትግል የሚያካሄዱ መሆናቸውን በመጥቀስ የዋስትና መብት ለመከልከል የቀረበው ክርክር ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ጠበቆቻቸው ካቀረቧቸው መከራከሪያዎች በተጨማሪ ማከል የሚፈልጉት ነገር እንዳለ ለፍርድ ቤቱ የገለጹት አቶ እስክንድር ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ በዳኞቹ ተፈቅዶላቸዋል። የዋስትና ጥያቄን አስመልክቶ አቃቤ ህግ ሲናገር ዋነኛ ፍላጎቱ የህዝብ ሰላም እና ደህንነት መሆኑን መጥቀሱን ገልጸው፤ ይህ እንዲከበር ደግሞ የሚቀጥለው ምርጫ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
“እኛ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት ላይ የነበርን ነን። በዝግጅታችን ለህዝባችን የፖለቲካ የበላይነት እንዳለን በማሳየታችን፤ በዚህ ምክንያት ገዢው ፓርቲ አስሮ ያመጣን መሆኑን እንድታውቁልን ያስፈልጋል”
እስክንድር ነጋ – የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር
“እኛ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት ላይ የነበርን ነን። በዝግጅታችን ለህዝባችን የፖለቲካ የበላይነት እንዳለን በማሳየታችን፤ በዚህ ምክንያት ገዢው ፓርቲ አስሮ ያመጣን መሆኑን እንድታውቁልን ያስፈልጋል” ሲሉ አቶ እስክንድር ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። “እኛ ታስረን የሚደረግ ምርጫ፤ አቃቤ ህግ የሚፈልገውን የሀገሪቱን ሰላም እና ደህንነት አያመጣም። በሀገሪቱ ሰላም እና ደህንነት እንዲመጣ ከተፈለገ በዋስትና ወጥተን በምርጫ መሳተፍ አለብን” ብለዋል። እነርሱ በሌሉበት የሚካሄድ ምርጫ ተቀባይነትም ሆነ ቅቡልነት እንደማይኖረውም አክለዋል።
ከአቶ እስክንድር በተጨማሪ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አባላት አመራሮች የሆኑት አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሴ “የዋስትና መብት ሊከለከል አይገባም” ሲሉ አስተያየቶቻቸውን በችሎት አሰምተዋል። የአምስተኛ ተከሳሽ ጌትነት በቀለ ሁለት ጠበቆችም የአቃቤ ህግን ማብራሪያ በመቃወም ሰፋ ያለ መከራከሪያ አቅርበዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት፤ በተከሳሾች የዋስትና መብት ላይ የቀረበውን ክርክር መርምሮ ብይን ለመስጠት ለመጪው ማክሰኞ መስከረም 12፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። በመጪው ችሎት ጠበቆች በአቃቤ ህግ ክስ ላይ የሚያቀርቡትን የክስ መቃወሚያ እንዲያቀርቡም ትዕዛዝ አስተላልፏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)