አቃቤ ህግ የታገደው የእነ ጃዋር መሐመድ ንብረት ሊመለስላቸው አይገባም አለ

በተስፋለም ወልደየስ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከጃዋር መሐመድ ቤት በብርበራ የተወሰዱ ገንዘቦች እና ዕቃዎች ፖሊስ በኢግዚቢትነት የያዛቸው ስለሆነ ልጠየቅበት አይገባም አለ። አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በሶስት ተጠርጣሪዎች እና በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ስም የተመዘገቡ እና በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ስድስት መኪኖችም በወንጀል ድርጊት የተገኙ ንብረቶች ስለሆኑ ሊመለሱ እንደማይገባ ተከራክሯል።  

አቃቤ ህግ ክርክሩን ያቀረበው አቶ ጃዋርን ጨምሮ 15 ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን የንብረት እገዳ ይነሳልን አቤቱታ በመቃወም ዛሬ አርብ መስከረም 8፤ 2013 ለፍርድ ቤት በጹሁፍ በሰጠው ምላሽ ነው። አስራ አምስቱ ተጠርጣሪዎች የታገዱ እና የተያዙ ንብረቶቻቸው እንዲለቀቁላቸው፤ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት አቤቱታ ያቀረቡት ከሳምንት በፊት ጳጉሜ 3፤ 2012 ነበር። 

ተጠርጣሪዎቹ ሰኔ 23፤ 2012 በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተነሳው ሁከት እና ብጥብጥ “ተሳትፎ አላቸው” በሚል ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር እንዳሉ አቃቤ ህግ በዛሬው ምላሹ አስታውሷል። በዚህ መሰረትም በተጠርጣሪዎቹ እና በቤተሰቦቻቸው ስም የሚገኙ የተለያዩ የባንክ አካውንቶች፣ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ላይ እገዳ እንዲደረግ በሐምሌ 11፤ 2012 ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ማመልከቻ ማስገባቱን ጠቅሷል። 

ማመልከቻውን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት የእግድ ትዕዛዝ መስጠቱን ተከትሎም የተጠርጣሪዎቹ እና የቤተሰቦቻቸው የባንክ አካውንት እና ንብረት መታገዱንም አቃቤ ህግ በምላሹ አትቷል። ይህ የንብረት እገዳ ጉዳይ እነ ጃዋር መሐመድ በጊዜ ቀጠሮ እና በቀዳሚ ምርመራ የችሎት ውሎዎቻቸው ወቅት በጠበቆቻቸው በኩል በተደጋጋሚ አቤቱታ ሲያቀርቡበት እንደነበር ይታወሳል።

የንብረት እገዳው የተከናወነው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በነሐሴ ወር መጨረሻ በነበረ የቀዳሚ ምርመራ ችሎት ላይ መግለጹን ተከትሎ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች አቤቱታቸውን የእገዳውን ትዕዛዝ ለሰጠው ችሎት አቅርበዋል። አቃቤ ህግ ጠበቆች ላቀረቡት አቤቱታ ዛሬ በጽህፈት ቤት በኩል በጹሁፍ በሰጠው ምላሽ አራት ጉዳዮችን አንስቷል። 

የመጀመሪያው አቶ ጃዋር መሐመድ “ለግል ፍጆታዬ ቤት ያስቀመጥኩት ጥሬ ገንዘብ እና ውድ ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች ከቤቴ ተወስደውብኛል” በማለት በማመልከቻው የጠቀሱት ነው። አቃቤ ህግ ለዚህ አቤቱታ በሰጠው ምላሽ “የፌደራል ፖሊስ ለወንጀል ምርመራው ይጠቅመኛል በማለት በብርበራ ከቤቱ ውስጥ በኢግዚቢትነት የተወሰደ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይ የፌደራል አቃቤ ህግ ምላሽ ሊሰጥ አይገባም” ብሏል።

ሁለተኛው የአቃቤ ህግ ምላሽ የተመለከተው በአቶ በቀለ ገርባ፣ ሀምዛ አዳነ፣ ቦና ትቢሌ በተባሉ ሶስት ተጠርጣሪዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ስም የተመዘገቡ ስድስት መኪኖች ላይ የቀረበ አቤቱታን ነው። አምስቱ መኪኖች የወንጀል ድርጊት የተገኙ እና ለወንጀል መፈጸሚያ የዋሉ በመሆናቸው የተያዘው ንብረት ይመለስልኝ በሚል የቀረበው አቤቱታ “ውድቅ ሊሆን ይገባል” ሲል አቃቤ ህግ ምላሽ ሰጥቷል። 

አቶ ሀምዛ በስሜ የተመዘገበ ነው በሚል ያቀረቡት ተሽከርካሪ “በማንም ስም ያልተመዘገበ” መሆኑን በምላሹ የጠቀሰው አቃቤ ህግ፤ ከዚህ በተጨማሪም የኮንትሮባንድ ወንጀል የተፈጸመበት በመሆኑ በወንጀል ፍሬነት የተመዘገበ መሆኑን አብራርቷል። በዚህም ምክንያት በጉምሩክ አዋጅ መሰረት በአስተዳደራዊ መንገድ የሚወረስ በመሆኑ አቤቱታው ተቀባይነት ሊያገኝ እንደማይገባ ገልጿል። 

በተጠርጣሪዎቹ እና በቅርብ ዘመዶቻቸው ስም የታገዱ የባንክ አካውንቶች በሚመለከት ጠበቆችን ላቀረቡት አቤቱታም አቃቤ ህግ በሶስተኛነት ምላሽ ሰጥቷል። እግዱ የተሰጠው በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ መሰረት መሆኑን አቃቤ ህግ በምላሹ ጠቅሷል። 

“አመልካቾች በባለቤቶቻችን እና በልጆቻችን ስም ያሉ ንብረቶቻችን እንዲሁም የባንክ አካውታችን ታግዶብንል በማለት የቀረበው አቤቱታ ከተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የስነ ስርዓትና የማስረጃ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 9 (1) አንጻር የሚጣለው እግድ የትዳር ጓደኛ እንዲሁም የተጠርጣሪውን ልጆች ላይ ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል የሚደነግግ በመሆኑ በአመልካቾች የቀረበው የእግድ ይነሳልን አቤቱታ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም” ሲል አቃቤ ህግ በምላሹ አትቷል። 

የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የስነ ስርዓትና የማስረጃ አዋጅ፤ ተጠርጣሪዎች ለልጆቻቸው የትምህርት እና ሌሎች ወጪዎችን በተመለከተ ባቀረቡት አቤቱታ ላይም ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል አቃቤ ህግ በማመልከቻው ላይ በመጨረሻ ነጥብነት አንስቷል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ የራሱን ማረጋገጫ ተጠቅሞ ለዚህ ጉዳይ የሚሆን ገንዘብ ቢፈቅድ ተቃውሞ እንደሌለውም በምላሹ አመልክቷል።        

“ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች የተባለውን ወጪ ለመሸፈን ከተያዘው ገንዘብ ውጪ ሌላ ገቢ የሌላቸው፣ ልጆቻቸው ስለመሆናቸው እና ስለሚያስፈልጋቸው ወጪ በማስረጃ ማስደገፋቸውን አረጋግጦ፤ ለዚህ ወጪ ብቻ የሚሆን ተመጣጣኝ ገንዘብ ሊፈቅድ የሚችል ይሆናል”

– የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በንብረት እግድ ላይ የሰጠው ምላሽ

“ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት የሌለው ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች የተባለውን ወጪ ለመሸፈን ከተያዘው ገንዘብ ውጪ ሌላ ገቢ የሌላቸው፣ ልጆቻቸው ስለመሆናቸው እና ስለሚያስፈልጋቸው ወጪ በማስረጃ ማስደገፋቸውን አረጋግጦ፤ ለዚህ ወጪ ብቻ የሚሆን ተመጣጣኝ ገንዘብ ሊፈቅድ የሚችል ይሆናል” ሲል አቃቤ ህግ በምላሹ አስቀምጧል።    

አቃቤ ህግ በምላሹ ማጠቃለያም የተያዙት ንብረቶች “በወንጀል ፍሬነት ተጠርጥረው የተያዙ እና ሊወረሱ የሚችሉ” መሆናቸውን በመጠቆም፤ ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ታግደው መቆየታቸው በሕግ አግባብ የተደረገ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል። በዚህም መሰረት ተጠርጣሪዎች ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ሊደረግ እንደሚገባ ለችሎቱ አመልክቷል። 

ተጠርጣሪዎች በሌሉበት፣ በጽህፈት ቤት ጉዳዩን የተመለከቱት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ችሎት ዳኛ፤ ጠበቆች የመልስ መልስ ካላቸው ከቀጣይ ቀጠሮ በፊት ለችሎቱ እንዲያስገቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለመስከረም 19፤ 2013 ቀጠሮ በመስጠት ጠበቆችን አሰናብቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)