የኦሮሚያ ክልል በቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና የክልሉ ፕሬዝዳንት በነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ ለተመሰረተው ዲቦራ ፋውንዴሽን 10 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ገባ። የክልሉ መንግስት ገንዘቡን ለመስጠት ቃል የገባው ፋውንዴሽኑ በለገጣፎ ለሚያሰራው ትምህርት ቤት፣ የጤና አገልግሎት መስጫ እና ማሰልጠኛ ማዕከል ነው።
ዲቦራ ፋውንዴሽን በአቶ አባዱላ አራተኛ ልጅ የተሰየመ እና “ዳውንሲንድረም” ተብሎ በሚታወቀው የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት የተጠቁ ህጻናትን ለመደገፍ በሐምሌ 2011 ዓ.ም. የተቋቋመ ነው። ፋውንዴሽኑ በተቀዳሚ ዓላማነት የያዘው ለእንደዚህ አይነት ህጻናት በሀገሪቱ የሕክምና ማዕከላት እና በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል ሙያዊ አቅም መፍጠር መሆኑን በድርጅቱ ማስተዋወቂያ መጽሐፍ ላይ ጠቅሷል።
ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ይህንን ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ሊገነባው ላቀደው ትልቅ ማዕከል፤ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት 65 ሺህ ስኩዌር ሜትር መሬት መረከቡን የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራች አቶ አባዱላ ገመዳ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ መስከረም 9፤ 2013 ምሽት በተካሄደ ስነ ስርዓት ላይ ተናግረዋል። በኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን፤ በለገጣፎ ከተማ የሚገነባው ይህ ማዕከል የአጥር መከለል ስራው መጠናቀቁን እና በቅርቡ ግንባታው እንደሚጀምር ለስነ ስርዓቱ ታዳሚያን ገልጸዋል።
ፋውንዴሽኑ የሚያስገነባው ይህ ማዕከል በውስጡ ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ትምህርት ቤቶች ይኖሩታል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪ ማዕከሉ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናትን ዕድገትና ባህሪያቸውን የሚከታተሉ ሐኪሞች፣ የቴራፒ ነርሶች እና በትምህርት ቤት ውስጥ ድጋፍ የሚሰጧቸው መምህራኖችን የሚሰለጥኑበት ህንጻ ያካትታል። የባለሙያዎቹ ስልጠና የለገጣፎው ዋናው ማዕከል ተገንብቶ እስኪያልቅ በአዲስ አበባ ቦሌ መንገድ ሜጋ አካባቢ በሚገኘው የዲቦራ ፋውንዴሽን ዋና ጽህፈት ቤት ባሉ ክፍሎች እንደሚጀመር ተገልጿል።
በቅዳሜ ምሽቱ የፋውንዴሽኑ የማሰልጠኛ ማዕከል የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ከመንግስት እና ከግል ተቋማት ያልተጠበቁ ልገሳዎች በዚያው በመድረኩ ሲሰጡ ታይቷል። ከመንግስት በኩል ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደው የኦሮሚያ ክልል ነው። ለማሰልጠኛው ግንባታ የክልሉ መንግስት ለመስጠት ቃል ከገባው 10 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ የክልሉ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የመዋዕለ ህጻናት ግንባታውን ራሱ ለማከናወን መወሰኑን አስታውቋል።
የኦሮሚያ ክልሉ የትምህርት ቢሮ በበኩሉ ሽያጩ ለፋውንዴሽኑ እንዲውል በሚል በአቶ አባዱላ የተጻፉ 10 ሺህ መጽሐፍትን ለመግዛት ቃል ገብቷል። መጽሐፍቱ በክልሉ ባሉ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፋፈሉ በስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል። ከትምህርት ቢሮ በተጨማሪ የተለያዩ የግል ድርጅቶች እና ግለሰቦች ወደ አራት ሺህ ገደማ መጽሐፍት ለመግዛት ቃል ገብተዋል።
በቅዳሜው የምርቃት ስነ ስርዓት ሌላው ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጸው የመንግስት ተቋም የጤና ሚኒስቴር ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ወክለው በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ፤ የጤና ሚኒስቴር ዋናውን የማሰልጠኛ ግንባታ ወጪ እንደሚሸፍን አስታውቀዋል። ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውም በለገጣፎው ማዕከል የሚገነባውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሚያስገነቡ ቃል መግባታቸውን አቶ አባዱላ በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ይፋ አድርገዋል። ወይዘሮ ዝናሽ ከባለቤታቻው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በመሆን ባለፈው ሳምንት በዘመን መለወጫ በዓል ዕለት የዲቦራ ፋውንዴሽን ዋና ጽህፈት ቤትን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
ከትላንት በስቲያም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በስፍራው ተገኝተው የምርቃት ስነ ስርዓቱን ታድመዋል። የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ፣ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ዓለሙ ስሜ በቦታው ከነበሩ ባለልስጣናት መካከል ይገኙበታል። የቀድሞው የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሳሞራ የኑስም ከመርኃ ግብሩ ተካፋዮች አንዱ ነበሩ።
በቅዳሜው ስነስርዓት ላይ በርከት ያሉ ባለሀብቶች የተገኙ ሲሆን ከጥሬ ገንዘብ አንስቶ ለግንባታው ማዕከል የተለያዩ ድጋፎች ለማድረግ ቃል ሲገቡ ታይቷል። ፋውንዴሽኑ ከምስረታው ጀምሮ የበርካታ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እገዛ እንዳልተለየው የገለጹት አቶ አባዱላ የተወሰኑትን በስም እየጠሩ ሲያመሰግኑ ተደምጠዋል። ከተመስጋኞቹ መካከል አኪኮ ስዩም፣ ጌቱ ገለቴ፣ ሳቢር አርጋው፣ የምሩ ነጋ እና አመለወርቅ ግደይ ይገኙበታል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)