የተወካዮች ምክር ቤት የ90 ዳኞችን ሹመት አጸደቀ

የተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 12፤ 2013 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የ90 ዕጩ ዳኞችን ሹመት አጽድቋል። ከዳኞቹ ውስጥ አርባዎቹ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት የታጩ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተመለመሉ ናቸው።   

ዛሬ ሹመታቸው ከጸደቀላቸው 40 የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ውስጥ አስራ አንዱ ሴቶች ናቸው። በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞቹ ሹመት ላይ አምስት የምክር ቤት አባላት ድምጸ ተዓቅቦ አድርገዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ሹመትም በተመሳሳይ ሶስት ድምጸ ተዓቅቦ አስተናግዷል።

ከበርካታ ተወዳዳሪዎች መካከል የጽሑፍ እና የቃለ-መጠይቅ ፈተናን አልፈው ለሹመት መብቃታቸው የተነገረላቸው እነዚህ ዳኞችን የመለመለው የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታውቋል። ዳኞቹ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቅራቢነት በምክር ቤቱ ሹመታቸው ከመጽደቁ በፊትም፤ በጉባኤው በተቀመጠው መስፈርት እና በሕዝብ አስተያየት መመዘናቸው ተገልጿል። 

የዳኞቹ ሹመት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘውን የማሻሻያ ስራ ለማሳካት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ትላንት አስታውቆ ነበር። ሹመቱ በፍርድ ቤቶች የዳኛ እና የመዝገብ ቁጥርን በማመጣጠን የዳኞችን የስራ ጫና (case load) መቀነስ እንደሚያስችልም ዳይሬክቶሬቱ ገልጿል።

ዛሬ በተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው የጸደቀላቸው ዳኞች፤ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ እየተመሩ ቃላ መሃላ ፈጽመዋል።  አዲስ ተሿሚዎቹ የፌደራል የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች፤ በተሾሙበት ፍርድ ቤት ዋና መስሪያ ቤት ቅጽር ግቢ ተገኝተው ከኃላፊዎች ጋር የመታሰቢያ ፎቶግራፍ ተነስተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)