የወላይታ ዞን የቀድሞ አመራሮችን ጨምሮ 20 ተጠርጣሪዎች በእስር እንዲቆዩ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰጠ

በተስፋለም ወልደየስ

የወላይታ ዞን የቀድሞ አመራሮችን ጨምሮ 20 ተጠርጣሪዎች በእስር እንዲቆዩ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰጠየደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የቀድሞ የወላይታ ዞን አመራሮች የነበሩ ግለሰቦችን ጨምሮ 20 ተጠርጣሪዎች በወላይታ ሶዶ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጠ። 

ፍርድ ቤቱ፤ በስር ፍርድ ቤት ለተጠርጣሪዎች ተፈቅዶ በነበረው ዋስትና ላይ ፖሊስ የመልስ መልስ ይዞ እንዲቀርብ ለመጪው ሳምንት ማክሰኞ መስከረም 19፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ ተመስገን ዋጃና ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የተጠርጣሪዎችን አቆያየት በተመለከተ በትላንትናው ዕለት ከሰዓት ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም በጠዋት ችሎት ቀርበው የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች አልተገኙም በሚል ብይኑን ለዛሬ ማሳደሩን ጠበቃው ገልጸዋል። 

እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሲጠብቁ የቆዩ ሰባት ተጠርጣሪዎችም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሐዋሳ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ መደረጋቸውንም አክለዋል። ዛሬ ረቡዕ መስከረም 13፤ 2013 ረፋዱን በነበረው ችሎት፤ በህመም ምክንያት ትላንት ከሰዓት ያልተገኙት ሁለት ግለሰቦችን ጨምሮ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር ተብሏል። 

ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን ተከትሎም ከዛሬ ችሎት መጠናቀቅ በኋላ ዘጠኙም ተጠርጣሪዎች በፖሊስ መኪና መወሰዳቸውን የስድስት ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ ተመስገን ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በፖሊስ ከተወሰዱት ተጠርጣሪዎች መካከል የወላይታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉነህ ወልደጻዲቅ፣ የዞኑ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ምህረት ቡኬ እና የወላይታ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዲን አቶ ተከተል ላቤና ይገኙበታል።

“ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል በመናድ” ወንጀል በተጠረጠሩት 20 ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ከስልጣናቸው የተነሱት የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እና የዞኑ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ዩሃንስም ተካትተዋል። ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸው ነበር።

በነሐሴ ወር መጀመሪያ በወላይታ ሶዶ በስብሰባ ላይ የነበሩ የዞኑ አመራሮች እና ሌሎች ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ተቃውሞ መቀስቀሱ ይታወሳል። ለአራት ቀናት በእስር ቆይተው በዋስትና ከተፈቱት 26 ግለሰቦች መካከል ስድስቱ የሀገር ሽማግሌዎች ነበሩ። ፖሊስ የወላይታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፈቀደውን ዋስትና ላይ ለደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሲያስገባ ስድስቱን የሀገር ሽማግሌዎች ሳያካትት ቀርቷል።

ጉዳዩ በሽምግልና እንዲፈቱ የሚሹ የሀገር ሽማግሌዎች በትላንትናው የችሎት ውሎ ተገኝተው እንደነበር ጠበቃ ተመስገን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የሀገር ሽማግሌዎቹ ጉዳዩን ይህንኑ ጥያቄቸው ለፍርድ ቤቱ አቅርበው እንደነበርም ማቅረባቸውንም አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)