ዋስትና ተፈቅዶላቸው በድጋሚ ታስረው የነበሩት አቶ ሚሻ አደም ከእስር ተለቀቁ

በተስፋለም ወልደየስ

ባለፈው ጳጉሜ 4፤ 2012 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቁ ከተወሰናላቸው በኋላ በኦሮሚያ ፖሊስ በድጋሚ የታሰሩት አቶ ሚሻ አደም ዛሬ አመሻሹን መለቀቃቸውን ቤተሰቦቻቸው እና ጠበቃቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ለጃዋር መሐመድ የሳተላይት መሳሪያ በመግጠም የተከሰሱት አቶ ሚሻ የተለቀቁት፤ ታስረው ከነበረበት የቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ዛሬ ከሰዓት ወደ ሱሉልታ ከተማ ከተወሰዱ በኋላ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ሚሻ በ20 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ፤ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተከሳሹ ላይ ይግባኝ እስኪጠይቅባቸው ድረስ ለአምስት ቀናት በእስር መቆየታቸው አነጋግሮ ነበር። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መስከረም 4፤ 2013 ባስቻለው ችሎት “ዋስትናው ሊፈቀድ አይገባም” ሲል አቃቤ ህግ ያቀረበውን ይግባኝ ተመልክቶ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቷል። 

ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማግስት ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተጻፈን የእስር መፈቻ የያዙት የአቶ ሚሻ ቤተሰቦች፤ ተከሳሹ ወደታሰሩበት ቦታ ቢያመሩም መለቀቃቸው ተነግሯቸዋል። ሆኖም የተከሳሹ ጠበቆች እና ቤተሰቦች ባደረጉት ማጣራት አቶ ሚሻ በኦሮሚያ ፖሊስ መወሰዳቸውን እና በቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን እንደደረሱበት ለፍርድ ቤት አቤት ብለው ነበር። 

የአቶ ሚሻን ክስ የሚመለከተው እና ዋስትናቸውንም የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት፤ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በችሎት ፊት ቀርበው ስለ ጉዳዩ እንዲያስረዱ መስከረም 11፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ይታወሳል። ሰኞ መስከረም 11 በነበረው ችሎት የወንጀል ምርመራ ኮማንደር የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን ወክለው በችሎቱ መገኘታቸውን ጠበቃ ከዲር ገልጸዋል። ሆኖም ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንም ሆነ ተከሳሹ ታስረው ከሚገኙበት የቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ የቀረበ ተወካይ እንዳልነበርም አስረድተዋል። 

ፍርድ ቤቱ በችሎት የተገኙትን የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኮማንደር፤ የቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥን አስረው እንዲያቀርቡ ለትላንት ረቡዕ መስከረም 13 ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ጠበቃው ተናግረዋል። በትላንቱ ችሎት የፌደራል ፖሊስ በጹሁፍ በሰጠው ምላሽ “ወደ ስፍራው በሄዱበት ወቅት የቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥን በአካል ማግኘት እንዳልቻሉ” መግለጹንም አብራርተዋል።

ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የችሎቱን ትዕዛዝ ያላስፈጸሙት የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኮማንደር እና የቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ በ48  ሰዓት ውስጥ ታስረው እንዲቀርቡ ትላንት ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበርም አቶ ከዲር ጠቁመዋል። ይህንን ትዕዛዝ ተከትሎም አቶ ሚሻ ዛሬ አመሻሹን ከእስር መለቀቃቸውን አመልክተዋል። አንድ የተከሳሹ ቅርብ የቤተሰብ አባልም የአቶ ሚሻን መፈታት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

ተከሳሹ ዛሬ ከሰዓት ወደ ሱሉልታ ተወስደው የነበሩት በከተማይቱ ፍርድ ቤት ለመቅረብ እንደነበር በስፍራው ተገኝተው ጉዳዩን የተከታተሉት እኚሁ የቤተሰብ አባል ተናግረዋል። የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አቶ ሚሻን በቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ እንዲታሰሩ ከማድረጉ በፊት፤ በሱሉልታ ከተማ ፍርድ ቤት አቅርቦ የ14 ቀናት የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶለት እንደነበርም አስታውሰዋል። አቶ ሚሻ  የምርመራ ጊዜያቸውን ለማጠናቀቅ ስድስት ቀናት ቀርቷቸው የነበረ ቢሆንም፤ ፖሊስ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት በፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ እንዲነሳላቸው መደረጉን የቤተሰብ አባላቸው ገልጸዋል።  

የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅን በመተላለፍ የተከሰሱት አቶ ሚሻ የዋስትና መብታቸው ከተከበረላቸው በኋላ ጉዳያቸውን በሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነበሩ ሶስት የችሎቶች ውሎዎች በአካል አልቀረቡም። አቃቤ ህግ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸውን አቶ ሚሻን የከሰሳቸው “ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን መሰረተ ልማት ወደ ጎን በመተው፤ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ከአሜሪካን ሀገር በማስመጣት በአቶ ጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት ዘርግተዋል” በሚል ነው። 

ተከሳሹ ዘርግተዋቸዋል ተብለው በክስ ሰነዳቸው ውስጥ ከተጠቀሱ መሳሪያዎች ውስጥ በግለሰብ ደረጃ መያዝ የማይፈቀዱ ነው የተባለው “ሮኬት ፕሪዝም ጂን 2 ሲስተም፤ ዩቢኪውቲ ኤጅ ራውተር” ይገኝበታል። ተከሳሹ ከሳተላይት የሚመጣውን ሲግናል ለመሰብሰብና የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቪሳት ዲሽም በአቶ ጃዋር ቤት መግጠሙ በክስ ሰነዱ ተጠቅሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)