ልዩ ቃለ ምልልስ- ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ጋር

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በርከት ያሉ ወጣት ባለሙያዎች በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተመድበው ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፤ በጥቅምት 2011 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህርነታቸው ለቅቀው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መስሪያ ቤትን በምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግነት ተቀላቅለዋል። እስካለፈው ነሐሴ ወር በዚሁ የኃላፊነት ቦታቸው የቆዩት ዶ/ር ጌዲዮን፤ ተጨማሪ ሹመት በማግኘት በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ቁልፍ የሚባለውን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መስሪያ ቤትን የመምራት ዕድል አግኝተዋል። 

ወጣቱ ባለሙያ የጠቅላይ ዐቃቤ ህግነት ስልጣኑን የተረከቡት የገዢው ፓርቲ ሁነኛ ሰው ናቸው ከሚባሉት ወ/ሮ አዳነች አበቤ ሲሆን ሹመታቸውም በተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ሳምንት  ጸድቆላቸዋል። በአንድ ወር የስልጣን ጊዜያቸውም ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተቀሰቀሱ ሁከቶች ተጠርጥረው የታሰሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች ምርመራ ተጠናቅቆ ክስ እንዲመሰረት አድርገዋል። ከተጠርጣሪዎች እስር እና ምርመራ፣ በእነርሱ ላይ ከተከፈቱባቸው ክሶች እንዲሁም ከፍርድ ሂደት ጋር በተያያዘ መስሪያ ቤታቸውን የተመለከቱ ጥያቄያዎችን በመያዝ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ተስፋለም ወልደየስ ከዶ/ር ጌዲዮን ጋር ረዘም ያለ ቆይታ አድርጓል። የመጀመሪያው ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል።   


ጥያቄ፦ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣኖች አንዱ ፖሊስ በምርመራ ወቅት ሰብዓዊ መብትን እንዳይጥስ የመቆጣጠር ኃላፊነት ነው። ነገር ግን በተደጋጋሚ ከተጠርጣሪዎች እና ተከሳሾች የምንሰማው ህይወታቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ እንደተያዙ፣ አንዳንዶቹ እንደተደበደቡ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከቤተሰብ ጋር እንደማይገናኙ ነው። ከኮሮና ጋር በተያያዘም በርካታ ብሶቶች ነው የሚቀርቡት። በተለይ በተጠረጠሩ እና በተከሰሱ ሰዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ላይ እንዲህ አይነት ጉዳዩች ተደጋግመው መነሳታቸው ዐቃቤ ህግ ኃላፊነቱን አልተወጣም አያስብለውም ወይ? 

ዶ/ር ጌዲዮን፦ከተጠርጣሪዎች አያያዝ ጋር በተያያዘ ያሉ የሚነሱ ጉዳዩችን በተመለከተ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምርመራን የመከታተል፣ ምርመራን የመምራት ኃላፊነት አለበት። የምርመራ ስራ የፖሊስ ነው። ግን ፖሊስ መርምሮ መዝገቡ ከተደራጀ በኋላ የሚከሰው ዐቃቤ ህግ ስለሆነ የምርመራ ሂደቱም ላይ የሆነ አይነት ሚና አለው። ከዚያ ጋር ተያያዞ ደግሞ የተጠርጣሪዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በምርመራው ሂደት ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ኃላፊነት አለበት። እርሱ ልክ ነው። ያንን በተመለከተ ተቋሙ ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት እያደረገ ነበረ። “ተደብድቤያለሁ” ያለ ተጠርጣሪ የሚጠቀስ ኬዝ ካልነገርከኝ፤ እኔ እንደዚያ ብዙ አልገጠመኝም። 

ጥያቄ፦ ከአንድም፣ ሁለት፣ ሶስት ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። አቶ እስክንድር ነጋ ሲያዙ “ተደብድቤያለሁ” ብለዋል። የአቶ የጃዋር መሐመድ የኮምፒውተር ባለሙያ ተብለው የሚታወቁት አቶ ሚሻ አደም የሚባሉት ግለሰብ መደብደባቸው ተገልጿል። አቶ ሸምሰዲን ጣሃ የተባሉ ተጠርጣሪም እንዲሁ መደብደባቸውን ለፍርድ ቤት ሲናገሩ ሰምተናል። እነዚህን የማውቃቸውን ሶስት ጉዳዮች ለምሳሌነት አነሳሁ እንጂ ሌሎችም እንዳሉ መረጃዎች ደርሰውናል። በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጻር አነስተኛ ሊመስል ይችላል ግን አሁንም በየቦታው የሚፈጸም ነው።

ዶ/ር ጌዲዮን፦እነዚህ ያልካቸውን ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ጣቢያ በነበራቸው ቆይታ ሄደን ጎብኝተናቸዋል። የዐቃቤ ህግ ባለሙያዎችም ጎብኝተዋቸዋል። ከእኔ በፊት የነበሩት አመራር ራሳቸው ሄደው በአካል ጉብኝት ተደርጓል። ያን ጊዜ “የሰብዓዊ መብት አያያዛችሁ እንዴት ነው? ፖሊስ ጋር ያለው ነገር ምንድነው?” ስንል ጠይቀናቸዋል። እና ያኔ ከመድኃኒት አቅርቦት፣ ከቤተሰብ ጋር በተገናኘ የተነሱ ጉዳዩች ነበሩ። “ተደብድቤያለሁ” የሚል ግን ያኔም እንደዚህ ያለ የከረረ ቅሬታ አላጋጠመኝም። ለዚያ ነው ያነሳሁት።

ከቤተሰብ ጥየቃ ጋር፣ ጠበቃን ከማግኘት ጋር እንደዚህ አይነት የመሳሰሉ በተደጋጋሚ እንደተነሱ እኔም አውቃለሁ። እርሱ ያው በኮቪድ 19 የተነሳ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በማረሚያ ቤት እና በፖሊስ ጥበቃ ያሉ ሰዎችን አስመልክቶ፤ የጉብኝት መብትን ትንሽ ጠበብ የሚያደርግ ነገር ከአምስት ወር በፊት የወጣ ነበር። ማረሚያ ቤት ያሉ ሰዎች አንድ ቦታ ተስብስበው ነው የሚቀመጡት። ማህበራዊ ርቀትን ጠብቀህ የምትቆይበት ቦታ አይደለም። ብዙ ለዚያ አይመችም። ስለዚህ አንዴ ቫይረሱ ወደ ማረሚያ ቤት ወይም ወደ ማረፊያ ቤት ቢገባ “በቀላሉ ብዙ ሰው ሊያዝ ይችላል፣ ከፍተኛ ጉዳት ሊያድርስ ይችላል” ተብሎ ስለታሰበ፤ እስረኞችን፣ ታራሚዎችን ወይም ጥበቃ ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችን የሚጠይቁ ሰዎች ላይ የተጣለ ገደብ ነበር።

አስገድዶ፣ አስፈራርቶ፣ በድብደባ ቃል የመቀበል፤ ጥፋተኛ ነኝ ብለህ እመን የሚባለው አይነት ነገር እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስየፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

ስለዚህ በቅርቡ ከተከሰቱ ጉዳዩች ጋራ በተያያዙ የመጡ ሳይሆኑ ቀደም ብለው ለኮቪድ 19 ጥንቃቄ የተደረጉ ገደቦች ነበሩ። የጠያቂ ወይም የሚጎበኝ ሰው ቁጥር እና እነርሱን የሚያገኙበት የጊዜ ብዛት ተቀንሶ ነበር። እርሱም ከኮቪድ 19 ጋር በተገናኘ የነበረ ነው። ከዚያም አልፎ የተነሱ ቅሬታዎች አንዳንዶቹ በፍርድ ቤት እንዲስተካከሉ ተደርጓል። አንዳንዶች በፖሊስ አመራሮች በራሳቸው እንዲታረሙ ተደርገዋል። በእኛም ተቋም እንዲታረሙ የተደረጉ አሉና በዚህ መንገድ ምላሽ ለመስጠት እየተሞከረ ነው። 

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር በሚውሉበት ጊዜ የሚከሰተውን በተመለከተ ቅድም ያነሳኸው ነገር አለ። እኛ በቅርበት የምንከታተለው በምርመራ ሂደት ላይ ያለውን ነው። አስገድዶ፣ አስፈራርቶ፣ በድብደባ ቃል የመቀበል፤ “ጥፋተኛ ነኝ ብለህ እመን” የሚባለው አይነት ነገር እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው። እኛ ብቻ ሳንሆን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በተደጋጋሚ ተጠርጣሪዎቹን ጎብኝቶ በይፋ መግለጫ አውጥቷል። ከዚያ አንጻር በተባለው ልክ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ ብዬ አላስብም። አልፎ አልፎ ግን የደረሰ ነገር ካለ እርሱን ማጣራት እንችላለን።   

ጥያቄ፦ ተጠርጣሪዎች “ህይወታችንን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ተይዘናል” ብለው በተደጋጋሚ ከሚጠቅሱት ውስጥ በእስር ቤት ውስጥ ያለው የኮቪድ 19 ሁኔታ ነው። የተወሰኑቱ እንደውም በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጦ ማስረጃው ለፍርድ ቤት ሲቀርብ አይተናል። አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ በሺህዎች የሚቆጠሩ እስረኞች በትምህርት ቤት ሳይቀር፣ ለጤናቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ ነው ታስረው ያሉት። አንድ ላይ እየበሉ እና አንድ ላይ እየዋሉ፣ አንዳቸው በኮቪድ ከተያዙ ሌሎቹም በበሽታው የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል።  በዚያ ላይ የንጽህና መጠበቂያዎችን ጨምሮ መሰረታዊ ቁሳቁሶች እንደማይገባላቸው ለፍርድ ቤት ሲናገሩ አድምጠናቸዋል። ከመካከላቸው አንዱ በኮሮና በሽታ መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ ለሌሎቹ ምርመራ እንደማይደረግላቸው አቤቱታ ሲያቀርቡም ሰምተናል። ተጠርጣሪዎች እንዴት በእንደዚህ አይነት ሁኔታ እንዲያዙ ይደረጋል? 

ዶ/ር ጌዲዮን፦መጀመሪያ አያያዛቸውን በተመለከተ ላስረዳ። ለምሳሌ ቀድመህ ያነሳሃቸው ሰዎችን ራሴም ጉብኝት ባደረግን ጊዜ አይቼያቸዋለሁ። ተለቅ ባለ ክፍል ውስጥ አንዳንድ ወይም ሁለት ሆነው ያሉት። ሀገሪቱ ባላት አቅም እና ሀብት ከዚህ በተሻለ መንገድ ማድረግ ይቻል ነበረ ብዬ አላስብም። ባለፈው ሁለት ወር በተለይ ከአርቲስት ሃጫሉ ሞት በኋላ የነበረውን ክስተት፣ የነበረውን ሁከት እና ብጥብጥ ሁሉም ሰው የሚያውቀው ነው። ከዚያ ጋር በተያያዘ የሞተው ሰው ቁጥር ብዙ ነው። የጠፋው ንብረትም በጣም ብዙ ነው። ከፍተኛ ወንጀል ነው የተፈጸመው። የተጠርጣሪ ቁጥር በጣም ብዙ ነው። ስለዚህ ያን ሁሉ ተጠርጣሪ መደበኛ በሆኑት ፖሊስ ጣቢያዎች፣ መደበኛ በሆኑት የማቆያ ቦታዎች እንያዝ ብንል በጣም መጨናነቅ ይኖራል፣ በጣም መጠጋጋት ይኖራል። ስለዚህ ከመደበኛ ማቆያ ቦታዎች በተጨማሪ በመጠኑም ቢሆን በሽታውን ለመከላከል የሚመች ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል ነው ትምህርት ቤቶችን እንደ ጊዜያዊ ማቆያ ለመጠቀም የተሞከረው። 

ባለው አቅም፤ ሰዎች በተለይ ምልክቶች ሲያሳዩ ምርመራ እንዲያገኙ ለማድረግ ተሞክሯል። ኮቪድ 19 በተለይ በማረሚያ ቤቶች፣ በማቆያ ወይም በማረፊያ ቤቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቦታዎችም በቀላሉ የሚተላለፍ ነው። የተቻለውን ያህል ጥንቃቄ ቢደረግም፤ ሙሉ ለሙሉ ሰው እንዳይያዝ ማረጋገጥ ይቻላል ማለት ይከብዳል። ቤተሰብ በመጠየቅ የሚያመጣለት ነገር አለ፣ ፍርድ ቤት ሄዶ መመለስ አለ፣ በዚያ ሁሉ ተጋላጭነት አለ። ተጋላጭነታቸውን ነው ለመቀነስ ጥረት የተደረገው ግን ሀገሪቱ ባላት አቅም እና ከነበረውም የተጠርጣሪዎች ብዛት አንጻር ከዚህ የተሻለ ነገር ለማድረግ አቅማችን ይፈቅዳል ብዬ አላስብም። መጨናነቁንም ለመቀነስ በርካታ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲወጡ ተደርጓል። ባለን አቅም፣ ሁኔታው በሚፈቅደው ልክ የተጠርጣሪዎችንም ሆነ የታራሚዎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ የምንችላቸውን ጥንቃቄ ወስደናል። ተጋላጭነታቸውን መቀነስ እንጂ ሙሉ ለመሉ ማስወገድ አይቻልም። 

ጥያቄ፦ አንዱ የዐቃቤ ህግ ሚና የሆነው የሀገሪቱ ህጎች በአግባቡ እና በትክክል መፈጸማቸውን ማረጋገጥ ነው። አሁን ግን በተደጋጋሚ በምናያቸው የፍርድ ቤት ሂደቶች ላይ ፍርድ ቤት በዋስትና የሚለቃቸው ተጠርጣሪዎች ወይም ተከሳሾችን ፖሊስ መልሶ ይዞ ሲያስር እናያለን። ለምሳሌ በዋስትና እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው የኢዴፓ ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው የመፈቻ ትዕዛዝ መጥቶላቸው ጭምር እስካሁን አልተለቀቁም። እርሱ አንድ ምሳሌ ነው ግን እንዲህ አይነት ነገሮች ተደጋጋሚ ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ አለማክበር ይታያል። ከዚህ ባሻገርም የሰዎችን የአካል ነጻነት ያለማክበር ሁኔታ አለ። የዋስትና መብት ህገመንግስታዊ መብት ነው። ሆኖም ዜጎች በዋስትና ወጥተው ጉዳያቸውን የመከታተል መብታቸው አይከበርም። ችግሮቹ ጎላ ብለው ቢታዩም ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምንም ሲያደርግ አይስተዋልም። እርምጃ ለመውሰድ ሲሞክርም አልታየም። በዚህ ላይ የእርስዎ መስሪያ ቤት የሚሰጠው ምላሽ ምንድነው? 

ዶ/ር ጌዲዮን፦ እንደዚያ ያሉ ጉዳዮች እንዳሉ እንረዳለን። አንዳንዶቹ ላይ እንዳልከው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወዲያው ተፈጻሚ ሳይሆን ሲንጓተት፣ ተጠርጣሪዎቹንም የመያዝ ነገር አለ። እርሱን ለማረም የምንወስደው እርምጃ፤ ፊት ለፊት ወጥቶ በአደባባይ በመግለጫ የሚደረግ አይደለም። ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር አብዛኞቹን ችግሮች ለመፍታት ሞክረናል። እንደዚህ ያሉ እክሎች፣ እንደዚህ ያሉ ችግሮች ሽግግር ላይ ከመሆናችን አንጻር ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ግን ትክክል አይደለም፤ መታረም አለባቸው። አልፎ አልፎ ተጠርጣሪ በዋስ ተለቅቆ ይግባኝ ሊጠየቅበት ይችላል። እሱንም በተመሳሳይ ልክ እንደዚሁ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለማክበር ተደርጎ ይታያል። ተጠርጣሪውን አስመልክቶ ዐቃቤ ህግ ይግባኝ የመጠየቅ መብት ስላለው፤ እርሱ tolerate መደረግ ያለበት ነገር ነው። 

የአቶ ልደቱ ጉዳይ በፌደራል ደረጃ ሳይሆን በክልል ደረጃ በኦሮሚያ ፖሊስ፣ በኦሮሚያ ዐቃቤ ህግ፣ በኦሮሚያ ፍርድ ቤት እየታየ ያለ ነው። ግን አንድ ዘርፍ ላይ እንደተሰማሩ ተቋማት መረጃ መለዋወጥ፣ መመካከር ስላለ በዚያ መልክ እኛም ክትትል ማድረጋችን አይቀርም። በአጠቃላይ ግን እነዚህን ጉዳዩችን በተመለከተ ችግር መኖሩን እንቀበላለን። ልክ ነው፤ አዎ አለ። ለማረምም ከፖሊስ ጋር፤ ከፍርድ ቤትም ጋር እየተነጋገርን የምንሰራው ስራ አለ። ተጨማሪም ስራ መስራት ግን ይጠበቅብናል። 

ጥያቄ፦ ግን መደጋገሙስ? አሁን እናንተ “በይፋ ወጥተን አንናገርም፤ ውስጥ ለውስጥ ለማስተካከል እየሰራን ነው” ትላላችሁ። አለመናገራችሁ አይደለም ወይ ይሄ ነገር መልሶ መላልሶ እንዲደገም ያደረገው? ችግሩ በፌደራልም ይሁን በክልል ደረጃ ባሉ ተቋማት በተደጋጋሚ የሚታይ ነው። በተለይ ፖለቲካ ቀመስ በሚባሉ ጉዳዩች ላይ በደንብ የሚስተዋል ነው። እንደውም ለውጥ መጣ ከተባለ ጊዜ ጀምሮ “ፍርድ ቤቶች የተሻለ ነጻነት አላቸው፤ ፖሊስ እና ዐቃቤ ህግ ናቸው ችግር ያለባቸው” የሚል አንደምታ ነው በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው። ምክንያቱም ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎችን በዋስትና ይለቃል፤ ዐቃቤ ህግ እና ፖሊስ ደግሞ ታስረው እንዲቆዩ ያደርጋሉ። እንደውም አንዳንዴ “መመካከር በሚመስል ሁኔታ ነው” የሚያደርጉት የሚል ቅሬታ ይቀርባል። ለዚህም ዐቃቤ ህግ ክስ እስኪመሰረት ድረስ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን ይዞ ማቆየቱ በማሳያነት ይነሳል።

ክርክሩ ዐቃቤ ህግ እና ፖሊስ በዋስትና ላይ “ይግባኝ መጠየቅ ይችላሉ፤ አይችሉም” አይደለም። እርሱ የማንም መብት ነው። ግን ተጠርጣሪዎች መፈታት ባለባቸው ቀን ሳይለቀቁ ቆይተው ከአምስት እና ስድስት ቀን፤ ከዚያም በላይ ያለ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በእስር ይቆያሉ። ለዚህ ደግሞ ችግሮች እየተስተዋሉ ያሉት “በፖሊስ እና በዐቃቤ ህግ በኩል ነው” የሚል ቅሬታ ነው ያለው። የምንከታተላቸው ጉዳዩችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው። ጥያቄው ምንም ባለማድረጋችሁ ነው ችግሩ በተደጋጋሚ የሚስተዋለው ነው። 

ዶ/ር ጌዲዮን፦ እነርሱን ጉዳዮች እንዳልኩት ለመፍታት የሰራነው ስራ አለ። እንደማስበው ይግባኝ ሲጠየቅባቸው ሁኔታውን በተመሳሳይ መንገድ ማየቱ ላይ ያለው አረዳድ መጥራት ያለበት ይመስለኛል። ለምሳሌ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዋስትና መለቀቅ አለበት ሲል፤ ፖሊስ “አይ! ይሄ ሰው ይሸሻል፣ ያመልጣል፣ ይጠፋል” ብሎ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢል፤ ይግባኙ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ያ ሰው ሊቆይ ይችላል ማለት ነው። ይግባኝ ብሎ ሳለ፤ “ይጠፋል፣ ያመልጣል፣ ይሸሻል” ብሎ እየፈራ ሊለቀው አይችልም። ስለዚህ እግድ ይጠይቃል። የይግባኝ ክርክሩን የሚያደርገው የዋስትና ትዕዛዙን አሳግዶ ነው። ስለዚህ መጀመሪያ የተሰጠው ትዕዛዝ አለመፈጸሙን በተመሳሳይ መንገድ የማየት አለ። ይህ ትዕዛዙ እንደታገደ በአግባቡ ካለመግለጽ ጋር በተያያዘ የሚመጣ ይሆናል። 

ከዚያም ያለፈ ግን በአስቸኳይ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያልተፈጸመባቸው እንዳሉ እኛም አይተናል። እነርሱንም ከተቋማቱ ጋር ተነጋገርን እርማት ማድረግ ተችሏል። ወጥቶ መግለጫ በመሰጣጣት ሳይሆን እኛ ቀን ተቀን ተገናኝተን አብረን የምንሰራ ተቋማት ነን። ስለዚህ በጋዜጣዊ መግለጫ ሳይሆን እርስ በእርስ በጋራ፣ ቀን በቀን በሚኖረን ግንኙነት ነው ምክክር የምናደርገው። ስለዚህ ያኛው ተገቢ አካሄድ አይመስለኝም። 

ጥያቄ፦ እንዲህ አይነት ነገር ሲከሰት ግን ያጠፉ ሰዎች ላይ ግን እርምጃ መወሰድ የለበትም? ለምሳሌ አሁን ክስ እስኪመሰረት ድረስ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ሰዎች አሉ። አካልን ነጻ ማውጣት (habeas corpus) እስኪመሰረት ሁሉ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ አሉ። 

ዶ/ር ጌዲዮን፦ አይ! እርሱ እንኳን የሰዎች ስም መጥቀስ ባልፈልግም ክስ ለመመስረት በፍርድ ቤት በተሰጠው ቀን habeas corpus ይቀርባል። እዚህኛው ፍርድ ቤት ክስ እያቀረብን ሌላኛው ፍርድ ቤት ደግሞ የhabeas corpus መዝገብ ይቀርባል። ተከሳሹ ያንን የማቅረብ መብት አለው። እኛም ደግሞ ክሱን ለማጠናቀር፣ ክሱን ለማቅረብ የተሰጠን ጊዜ አለ። ስለዚህ ያንን ተጠቅመን ማቅረብ ነው። 

ጥያቄ፦ አንዱ ክርክር የሚነሳው እዚህ ላይ ነው። በተጠርጣሪዎች እና ጠበቆቻቸው በኩል ዐቃቤ ህግ “በፍርድ ቤት ከተሰጠው ጊዜ በላይ ነው የሚወሰደው” የሚል ቅሬታ ይቀርባል። ለምሳሌ ክስ ለመመስረት 15 ቀን ተብሎ ከተሰጠ በኋላ ከ15 ቀንም በኋላ ክስ አይመሰርትም ማለት ነው። ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው ጊዜ ጭምር አንዳንድ ጊዜ የአተረጓጎም ክርክር ሲያስነሳ እንመለከታለን። የክስ መመስረቻ ጊዜው መቆጠር ያለበት የምስክሮች ቃል ግልባጭ ከደረሰበት ቀን ጀምሮ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ከሰጠበት ቀን ጀምሮ ነው መቆጠር ያለበት በሚል የሚከራከሩም አሉ። 

ፍርድ ቤት “እስከዚህ ቀን ድረስ ዐቃቤ ህግ ክስ መመስረት አለበት” ብሎ ቀን ከቆረጠ በኋላ ቀነ ገደቡም አልፎ ክስ ሳይመሰረት የሚቀርበት ጊዜ አለ። የእነ አቶ ጃዋር መሐመድን ጉዳይ ለማሳያነት መጥቀስ እንችላለን። በርከት ያለን ጋዜጠኞች ይህን ጉዳይ በቦታው ተገኝተን ስንከታተል ነበር። በተከታታይ ቀናት “ሰዎቹ ይመጣሉ” ተብለን ስንጠብቅ ከቆየን በኋላ ጥያቄ ስናቀርብ፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የትኛውም ቦታ የክስ መዝገብ እንዳልተከፈተ ነው የተነገረን። ነገር ግን ባለፈው ቅዳሜ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ነው የክስ መዝገቡ መከፈቱ “ሰበር ዜና” ተብሎ የወጣው።  የእነ አቶ እስክንድር ነጋም ጉዳይ እንደዚሁ ተመሳሳይ ነው። ለጠበቆች እንኳ ሳይነገራቸው ነው የክስ ሰነዱ ለተከሳሾች የተሰጠው። እነዚህ የሚታወቁ ሰዎች በመሆናቸው እዚህ በምሳሌነት አነሳሁት እንጂ ጉዳዩ በተደጋጋሚ የሚታይ ነው። በፖለቲካ ምክንያት የተከሰሱ፣ በየቦታው ያሉ ሰዎች፣ ለረጅም ጊዜ ሳይከሰሱ እንደተቀመጡ እንሰማለን። ለዚህ ነው “የዐቃቤ ህግ አካሄድ ወደ ፖለቲካ ያዘነበለ ሆኗል፤ ነጻነቱ የለውም” የሚል ጥያቄ የሚነሳው። 

ዶ/ር ጌዲዮን፦ ምሳሌዎች ስላነሳህ ያነሳኋቸው ምሳሌዎች ላይ ትንሽ አስተያየት መስጠት ይኖርብኛል። ለምሳሌ በእነ አቶ ጃዋር ጉዳይ እኛ ባለፈው አርብ [መስከረም 8፤ 2013] ክስ መስርተናል። ክስ መመስረታችንን መዝገብ ቁጥሩን፣ ያስገባነውን የክስ ቻርጅ ሁሉ ማቅረብ የሚቻል ነው። ክሱ ቢመሰረትም ያንኑ ቀን እነርሱ ተገኝተው፣ ያንኑ ቀን ክሱ አይነበብም። ያው አካሄዱን የምታውቀው ነው። 

የክስ መመስረቻ ጊዜን በተመለከተ የምስክሮች ድምጽ ተገልብጦ፣ ትራንስክሪፕቱ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ነው። “ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ወይስ ከዚያ በፊት?” የሚለውም፤ እርሱም ህጉ ራሱ በግልጽ የሚያስቀምጠው ነው። የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህጉ ላይ ባለው መሰረትም ሆነ አመክኖአዊ ሆነንም ስናየው፤ ክሱ የሚመሰረተው በምስክሮች ቃል ላይ ነው። ስለዚህ የምስክሮች ቃል ሳይመጣ፣ እርሱ ተገልብጦ ሳይሰጥ በፊት ክሱን ለመመስረት አይቻልም። ስለዚህ ያ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ነው የሚቆጠረው። እኛ ያለን መረጃ በተሰጡት ቀናት፣ ባለው ጊዜ ውስጥ አብዛኞቹ ክሶች ተመስርተዋል የሚል ነው ። 

 “ባለው ውስን ሀብት እና የሰው ኃይል፣ ያውም ለማሻሻል፣ ለመለወጥ፣ ነገሮችን ለማስተካከል በሚጣርበት ጊዜ ላይ፤ ይሄን ሁሉ ግዙፍ ስራ መስራት ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል እርሱ ከግምት ቢገባ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ”

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስየፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

ከዚሁ ጋር አያይዘን እንድናየው የምፈልገው ነገር በዚያ ክስተት፣ ከአርቲስት ሃጫሉ ሞት በኋላ የሟቾቹ ቁጥር፣ የጠፋው ንብረት የሚታወቅ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል፤ በቢሊዮን የሚቆጠር ንብረት ወድሟል። አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ኬዞች ያሉት ኦሮሚያም ላይ ኬዞች አሉ። ወንጀሉን በመቀስቀስ፣ በማስተባበር ብቻ ሳይሆን በቀጥታ በወንጀሉ በመሳተፍ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች አሉ። በጣም ግዙፍ (massive) የሆነ ኬዝ ነው። እንዲህ ያለ ሁከት ያጋጥማል ብለህ ተዘጋጅተህ፣ አቅደህ፣  እንዲህ ያለ ክስ እመሰርታለሁ የምትጠብቀው ነገር አይደለም። ክስተቱ ይከሰታል፤ ከክስተቱ በኋላ ነው ምርመራውን የምታደርገው። እና ባለው ውስን ሀብት እና የሰው ኃይል፣ ያውም ለማሻሻል፣ ለመለወጥ፣ ነገሮችን ለማስተካከል በሚጣርበት ጊዜ ላይ፤ ይሄን ሁሉ ግዙፍ (massive) ስራ መስራት ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል እርሱ ከግምት ቢገባ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። 

እነዚህ ኬዞች ከዚህ በፊት በነበረው ሽብር ህግ ቢሆን “መዝገቡን እዚህ አደረስኩኝ” ሳይባል፤ ለምርመራ ብቻ ዐቃቤ ህግ እና ፖሊስ አራት ወር ያህል ይወስዳሉ። አሁን አዲስ አበባ ብቻ ያሉት ጉዳዩች ሳይሆኑ ኦሮሚያ ብቻ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች ነው መርምረን አሁን በዚህ ሳምንት ክስ እየመሰረተን ያለነው። የብሔር እና የሃይማኖት ቀመስ ግጭቶች ሲሆኑ ፌደራልም ስለሚገባበት ማለት ነው። እንደው እንደተባለው “አርብ ክስ አልተመሰረተም” እንበል፤ ቅዳሜ ወይም ሰኞ ተመሰረተ ብንል ራሱ ካለው ከዚህ ጫና አንጻር ነው መታየት ያለበት። “ያ ባይሆን ተገቢ ነው፤ ያ መሆን አልነበረበትም” ልንል እንችላለን። ግን ተቋሙ ላይ፣ ፖሊስ ላይ፣ ህግ አስከባሪ አካላት ላይ ያለውን ሸክም መረዳት ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ። 

ጥያቄ፦ ለዚህ ሁሉ መሰረት የሚሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ የተናገሩት ቃል ነው። “ማስረጃ ሳንይዝ፣ አንከስም ወይም አናስርም” የሚል ቃል ገብተው ነበር። ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በእርስዎ መስሪያ ቤት ይሰጡ የነበሩት መግለጫዎች ያሳዩ የነበረው ሁሉም ማስረጃ እጃችሁ ላይ እንዳለ፣ ሁሉ ነገር እንደተጠናቀቀ ነበር። በምርመራ የጊዜ ቀጠሮ የነበሩ መጓተቶች፣ ክስ ለመመስረት የነበሩት አካሄዶች ግን ያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገባው ቃል እና በኋላ ላይ በመስሪያ ቤታችሁ የተሰጠውን መግለጫ የሚያፈርሱ ስለሆነ ነው እንዲህ አይነት ጥያቄዎች የሚነሱት። 

ዶ/ር ጌዲዮን፦ “ሳናጣራ፤ አናስርም” የሚለውን እንደ መርህ ተግባራዊ ልታደርግባቸው የምትችል አይነት ወንጀሎች አሉ። እርሱን ደግሞ ተግባራዊ ልታደርግ የማትችልባቸው የወንጀል አይነቶች አሉ። ለምሳሌ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መሞት በኋላ በተከሰተው ሁከት፣ በደረሰው ጥቃት ሰዎች ተገድለዋል። በጣም በሚያሰቅቅ ሁኔታ ሳይቀር ሰዎች ሞተዋል፤ ንብረት ወድሟል። ከዚያ በኋላ “ቆይ! ይሄን ነገር ሳላጣራ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አላውልም” ብትል ያንን ጥፋት ያጠፉት ሰዎች መጀመሪያ ማስረጃውን ያጠፋሉ። ያንንም ካልቻሉ ራሳቸው ይጠፋሉ። ከዚያ በኋላ ለተጎዱት ሰዎች፣ ቤተሰባቸው ለሞተ፣ ንብረታቸው ለወደመ ሰዎች፣ ለእነርሱ ምንድነው የምታቀርበው? ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ሰዎች ተጠያቂ ማድረግ አትችልም ማለት ነው። ስለዚህ ከወንጀሉ ባህሪ እና ከተከሰተው አንጻር እነዚህን ሰዎች ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ማዋል ግድ ይላል። 

ስለዚህ “ሳናጣራ አናስርም” የሚለውን በዚህ አውድ ስታየው እንደዚህ ላለው ጉዳይ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አይደለም የሚለው አንድ እርሱን ከግምት ብናስገባው። ሁለተኛ ደግሞ እንዳልኩህ ነገሩ በጣም ግዙፍ የሆነ ኬዝ ነው። ምርመራው በአንድ ወር በሆነ ጊዜ ውስጥ ነው ያለቀው። ከዚያ በኋላ ክስ ያልተመሰረተው እንዴት ነው የሚለውን እናንተም ሂደቱን በይፋ ስትከታተሉት ስለነበር ታውቁታላችሁ። ቀዳሚ ምርመራ (preliminary hearing) በማካሄድ የምስክሮች ቃል በፍርድ ቤት እንዲያዝልን ነው አንድ ወር ከምናምን ጊዜ የተወሰደው። ስለዚህ ምርመራው በአንድ ወር አካባቢ ማለቁ፤ እኔ በጣም በተፋጠነ ሁኔታ ተከናውኗል [ነው የምለው]። ከነበረው ሸክም፣ ከነበረው ጫና አንጻር፤ በአንድ ወር ውስጥ መከናወኑ ለፖሊስም፣ ለዐቃቤ ህግም ጥሩ ሰርቷል የሚያስብል ነው ባይ ነኝ። በፊት በእንደዚህ ያለ ኬዝ በቀላሉ አራት ወር እንዲሁ ይወሰድ ነበር።     

ሁለተኛ “መረጃዎችን እዚህ ጋር አግኝተናል፤ ሂደቱ እዚህ ጋር ደርሷል” እየተባለ መረጃ ከስር ከስር እየተሰጠ ነው ምርመራው ያለቀው። ከዚያ በኋላ ቀዳሚ ምርመራው ነው አንድ ወር የፈጀው። ብዙ ምስክሮችን ነበሩን። ቀዳሚ ምርምራው ዋናው ምርመራ አልቆ ማስረጃን ጠብቆ የማቆያ (evidence preserve) ሂደት ነው። ያገኘነው ማስረጃ እነዚህን ሰዎች “እንከሳለን፣ አንከስም፤ ጥፋት አጥፍተዋል፣ አላጠፉም” በሚል ለፖሊስ እና ለዐቃቤ ህግ ለመመርመሪያ ወይም ለማጣሪያ የሚውል አይደለም። ምግብ እንዳይበላሽብህ ፍሪጅ ውስጥ እንደምትከትው፤ ማስረጃ እንዳይበላሽብህ በቀዳሚ ምርመራ ተጠብቆ እንዲቆይ (preserve) ታደርገዋለህ። ያንን ማድረግ ደግሞ በኋላ ላይ “ምስክር ጠፋ” ተብሎ የሚስተጓጎል ነገር እንዳይኖር፤ የፍርድ ሂደቱ፣ የክርክር ሂደቱ የተፋጠነ እንዲሆን ስለሚረዳ ነው። ቀዳሚ ምርመራ ራሱ አድርገን ሁለት ወር ከግማሽ ወይም ከዚያ አለፍ በሚል ጊዜ ውስጥ ቀዳሚ ምርመራውም አልቆ ክስ ለመመስረት ችለናል። በሳምንትም በ15 ቀንም ነገሩ ቢያልቅ፤ ከዚህ የተሻለ ብናደርግ ደስ ይለናል ግን ከሁኔታው አንጻር ትንሽ የተሻለ ስራ ሰርተናል ብዬ አስባለሁ።  

ጥያቄ፦ ሌላው ጥያቄ የሚነሳበት የክሶች ጉዳይ ነው። ክሶቹን በተመለከተ ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክሶች ተረድተው ራሳቸውን በአግባቡ ለመከላከል እንዲችሉ ተደርገው መቅረብ ሲኖርባቸው በዚያ መልኩ አይደለም የሚዘጋጁት የሚል ቅሬታ ይነሳባቸዋል። ለምሳሌ “ወንጀሉ የት እና መቼ ነው የተፈጸመው? እያንዳንዱ ሰው ተጠያቂነቱ ምንድነው?” የሚለው ሳይካተት ክሶቹ ግልጽነት በጎደለው መልኩ ይቀርባሉ። በዚህ ሳምንት በነበረ አንድ የችሎት ሂደት ላይ እንኳ በዚህ ምክንያት የዐቃቤ ህግ ክስ እንዲሻሻል በዳኞች ትዕዛዝ ተሰጥቷል። ከዚህ ቀደምም እንዲህ አይነት ነገሮች ቢኖሩም “አሁን ያሉት የተሻሻሉ ነገሮች ናቸው፤ ለውጦች አሉ” ተብሎ በሚነገርበት በዚህ ጊዜ የወንጀሉን ድርጊት የማያቋቋሙ ክሶች እየቀረቡ እንዳሉ ባለሙያዎች ይተቻሉ። 

ሌላው ደግሞ ወንጀል ያልሆኑ ነገሮች እንደ ወንጀል ድርጊት ተቆጥረው ክሱ ላይ ሲቀርቡ ይታያል። ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ መንግስትን እና ባለስልጣናትን መተቸት ልክ እንደ ወንጀል ተደርጎ በክሶቹ ቀርቧል። ይህ አይነቱ የክስ አቀራረብ “ወንጀል ያልሆነውን ነገር ወንጀል ነው” ብሎ ህብረተሰቡ እንዲያስብ የሚያደርግ ነው በሚልም ወቀሳ ይነሳበታል። ሌላ ከክስ ጋር የተያያዘ ጉዳይ፤ መጀመሪያ ተጠርጣሪዎች በጊዜ ቀጠሮ ባሉበት ወቅት የሚጠረጠሩበት ጉዳይ ትልቅ ይሆንና በስተኋላ ላይ በክስ መልክ ሲመጣ ግን አነስተኛ የሚባሉ ክሶች ይሆናሉ። ይሄ ሆን ተብሎ ሰዎቹን በእስር ለማቆየት የሚደረግ አካሄድ ነው በሚልም ቅሬታ ይቀርባል። እነዚህን በአጠቃላይ እንዴት ይመለከቷችዋል?

ዶ/ር ጌዲዮን፦ ከመጨረሻው ልጀምርና “ትላልቅ ነገር ተጠቅሶ በትናንሽ ተከሰሱ” የሚባለው የግለሰብ ጉዳዮች ጋር ሳንገባ እንዲሁ ጠቅለል አድርጌ እመልሳለሁ። አንዳንዴ ጥቆማው ወይም በመነሻ ላይ የተገኘው መረጃ በጣም ትልቅ ነገር አመልክቶ፤ እሱን ግን ፍርድ ቤት ተቀባይነት ሊኖረው በሚችል በሚያሳምን መልኩ ማስረጃ ላይገኝ ይችላል። ጥቆማው አሳማኝ ቢሆንም ያንን ጥቆማ በበቂ ሁኔታ የሚደግፍ ማስረጃ ስለሌለ ወደ ኋላ የምትልበት ነገር ሊኖር ይችላል። የወንጀል ጉዳይ ላይ የሚፈለገው የማስረጃ ደረጃ ከፍ ያለ ነው። በዚያ ደረጃ “ይህንን ነገር ላረጋግጥ አልችልም” ብሎ ዐቃቤ ህግ ካመነ፤ መጀመሪያ ከነበረው ጥርጣሬ አነስ ባለ ነገር ሊከስ ይችላል። “አንዴ በዚህ ጠርጥሬያለሁ፤ ማስረጃው እሱን ቢያሳይም፣ ባያሳይም በዚሁ እከሳለሁ” ሊባል ስለማይችል ማለት ነው። ያ ሰዎቹ ላይ የተለየ ተንኮል፣ ወይም እነርሱን ለማቆየት ተብሎ የሚደረግ ሳይሆን መጨረሻ ላይ ማስረጃው በሚደግፈው ልክ ክሱ ስለሚመሰረት ነው። ስለዚህ የጊዜ ቀጠሮ ላይ የተጠቀሰውን ጥርጣሬ ያህል ልክ በዚያው ነገር ክስ ላይመሰረት ይችላል። ያ ለተጠርጣሪውም የሚጠቅም ነው። በዚህ መሀል “መጀመሪያ የተጠረጠረው በዚህ ነው፤ አሁን ግን እየተከሰሰ ያለው ከዚያ በጣም አነስ ባለ ጉዳይ ነው” ብሎ ፍርድ ቤት ሲያምን የዋስትና መብቱንም ሊያከብር ይችላል።  

“የወንጀል ድርጊት ያልሆኑ ነገሮች በክሱ ውስጥ ተካተተዋል” የሚለው እርሱ ለምን እንደተባለ እረዳለሁ። እንግዲህ ይህንን ሊያስብሉ የሚችሉ ኬዞች በቀረቡባቸው ጉዳዩች ላይ አንዳንዱ እንደ ዳራ ከጀርባ ያለውን እሳቤ ወይም እይታ ለማቅረብ ብለው የገቡ ነገሮች ይኖራሉ። እነርሱ እንደዚያ ያለ የተሳሳተ ሀሳብ የሚሰጡ ከሆነ እነዚህን ግብዓቶችን ወስዶ መሻሻል የሚገባው ነገር መሻሻል አለበት። 

በቅርቡ የተሰጠውን ትዕዛዝ በተመለከተ በጥያቄው የተነሳውን ነጥብ እንመልከት። በፍርድ ቤት ጉዳይ ላይ ቀጥታ አስተያየት መስጠት እንዳይሆንብኝ እንጂ ለምሳሌ “ተስፋለም ቀሰቀሰ እና እርሱ በቀሰቀስው ሁከት ይሄን ያህል ሰው እዚህ አካባቢ ላይ ሞተ” ካልኩ፤ እነዚያ እዚያ አካባቢ ላይ የሞቱ ሰዎች የሞቱበትን ሰዓት፣ የሞቱበትን መሳሪያ ማካተቱ አስፈላጊ አይሆንም። ምክንያቱም አንተን እየከሰስኩህ ያለሁት እነዚያን ሰዎች “ራሱ በእጁ፣ በቦታው ተገኝቶ ወንጀል ፈጽሟል” ሳይሆን ለእነዚያ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን “ግጭት ቀስቅሷል፣ አነሳስቷል” በሚል ነው። ስለዚህ የወንጀሉ ባህሪ የሚጠይቀው ዝርዝር ነው መግባት ያለበት። ስለዚህ በግድያ ከከሰስኩህ “እዚህ ቦታ ነው የገደለው፣ አገዳደሉ እንዲህ ነበር” የሚለውን ዝርዝር ማቅረብ አለብኝ። ግጭት በመቀስቀስ ሲሆን ግን ያ ዝርዝር ያስፈልጋል ወይ የሚለውም መታየት አለበት። ለምሳሌ መቶ ምናምን ሰዎች በሞቱበት ግጭት ላይ የመቶ ምናምን ሰዎችን አሟሟት ከተዘረዘረ ክሱ ራሱ ትልቅ ጥራዝ ነው የሚሆነው እና ከወንጀሉ፣ ከክሱ ባህሪ አንጻር የሚቀርበውም ዝርዝር ያንን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት። 

ግን እንዲያም ሆኖ የሚመጡ ግብዓቶችን ከግምት በማስገባት፣ ልማድ ሆኖብን መስተካከል ኖሮባቸው ያልተስተካከሉ ነገሮችን እናስተካክላለን። የተደረገው ነገር ወንጀል የሚያቋቋም ሆኖ፣ የተሰራው ነገር ግን አብሮ ዙሪያውን (cirucmstance)፣ እሳቤውን ለማሳየት ተብሎ አብሮ የሚገቡ ነገሮች ደግሞ በራሳቸው ወንጀል የማያቋቋሙ ከሆነ ምናልባትም ደግሞ ማህብረሰቡ ጋር ሌላ የተሳሳተ ዕይታ የሚፈጥሩ መሆናቸው ያልተፈለገ መልዕክት (unintended consqeuence) ሊኖረው ስለሚችል እርሱ መስተካከል ይኖርበታል። ወንጀል የሚያቋቁም ነገር ሳይኖር አገላለጹ ላይ ትርፍ ነገር ተጨምሮ ሊኖር ይችላል። የጉዳዩን ዳራ እና አውድ ለመስጠት ሲባል ነገሮች የተሳሳተ መልዕክት አስተላልፈው ከሆነ ጠቃሚ ስለማይሆኑ ባይገቡ ይመረጣል። እንደሱ ያሉ ነገሮች ወደፊት መስተካከል ይኖርባቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ከዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ሁለተኛ ክፍል በቀጣይ እናቀርባለን። እንዲያነቡት ከወዲሁ እንጋብዛለን]