ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ (ክፍል ሁለት)

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግነት ስልጣንን ከተረከቡ አንድ ወር ሞልቷቸዋል። በዚህ ጊዜም ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተቀሰቀሱ ሁከቶች ተጠርጥረው የታሰሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች ምርመራ ተጠናቅቆ ክስ እንዲመሰረት አድርገዋል። ከተጠርጣሪዎች እስር እና ምርመራ፣ በእነርሱ ላይ ከተከፈቱባቸው ክሶች እንዲሁም ከፍርድ ሂደት ጋር በተያያዘ መስሪያ ቤታቸውን የተመለከቱ ጥያቄያዎችን በመያዝ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ተስፋለም ወልደየስ ከዶ/ር ጌዲዮን ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል። ሁለተኛው ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል።


ጥያቄ፦ በመጀመሪያው ክፍል ቃለ ምልልሳችን የክልሎችን ጉዳይ አንስተው ነበር። ክልሎች የራሳቸው ስልጣን እንዳላቸው ብረዳም የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ደግሞ አጠቃላይ በሀገሪቱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ይመለከታል። ለእነርሱም መከበር ይሰራል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። አሁን ግን በክልል ደረጃ የተያዙ ጉዳዩች ላይ ልክ በፌደራል ያነሳነቸው አይነት ጥሰቶች ሲከናወኑ ይታያል። ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ሲፈጸሙ እያየን ነው።

ለምሳሌ እኛ እንኳ የዘገብናቸውን ብንጠቅስ ዋስትና የፈቀዱ ዳኞች ታስረዋል። ፖሊስ እንዲህ አይነት ጉዳይ ሲፈጽም እስካሁን ምንም አይነት እርምጃ ሲወሰድ አላየንም። እንዲህ አይነት እርምጃ የሚወስዱት፣ ዳኞችን በማሰራቸው እና መሰል ድርጊቶችን በመፈጸማቸው በዲስፕሊን ብቻ ሳይሆን በወንጀል ጭምር ሊጠየቁ ይገባ እንደነበር ባለሙያዎች ይሞግታሉ። ነገር ግን ምንም አይነት እርምጃ አላየንም። ከበላይ ሆኖ የሚቆጣጠረው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ነው ተብሎ ቢታሰብም በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ምንም ያደረገው ነገር የለም። ስለዚህ በእንደዚህ አይነት ጉዳዩች ላይ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሃላፊነቱን አልተወጣም አይደለም ወይ? ምንም አይነት እርምጃ አለመወሰዱ የመስሪያ ቤታችሁን ደካማነት አያሳይምን? በሌሎች የፍትህ አካላት ዘንድ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠርስ ምን አይነት የእርምት እርምጃ ለመውሰድ አቅዳችኋል? 

ዶ/ር ጌዲዮን፦ በክልል ያለውን ጉዳይ በተመለከተ የፌደራል ስርዓት ስላለ አሰራሮቹ በቀጥታ የክልልን ፖሊስ ወይም ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የማዘዝ አይደለም። “ይሄንን አድርግ፣ ያንን አታድርግ” የሚል የቁጥጥር ስልጣን አይደለም ያለን። እሱ ግልጽ ይመስለኛል። የፌደራል ፖሊስ፣ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሚመረምራቸው፣ ክስ የሚመሰርትባቸው ጉዳዩች አሉ። የክልል ፖሊሶች እና የክልል ዐቃቤ ህጎች ክስ የሚመሰርቱበት እና የሚሰሩበት ጉዳይ አለ። የሆነ ያህል የስልጣን ክፍፍል አለ። ያም ሆኖ እኛ የማስተባበር፣ የመከታተል ሚና አለን። አንዳንዶቹ ጉዳዩች ላይ ደግሞ የፌደራል ስልጣን ስር ሆነው፤ በውክልና ለክልሎች የተሰጡ ጉዳዩች አሉ። 

በውክልና የተሰጡ ስልጣኖችን አስመልክቶ ውጤታማ ስራዎችን ሊሰራ የሚችል የክትትል እና የድጋፍ ስርዓት እስከዛሬ አልዘረጋንም። በውክልና የሰጠነው ስልጣን እንዴት ነው ተግባር ላይ እየዋለ ያለው? ክልሎች ጋር ምን ክፍተት አለ? ምን ድጋፍ ማድረግ አለብን? የሚለውን ነገር ለይተን ድጋፍ ማድረግ የምንችልበት ስርዓትን ለመዘርጋት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በሀገር አቀፍ ያለን ተደራሽነት ለመጨመር የምንሰራቸው ስራዎች ይኖራሉ። አሁን ባለው ሁኔታ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ብቻ ነው ጽህፈት ቤት ያለን። ከዚያም ጋር ተያያዞ የሚመጣ ውሱኑነት አለ። ክልሎች ውስጥ ምርመራ ማድረግ በሚኖርብን ጊዜ ለዚያ ምርመራ ተብሎ፤ ሰው ከዚህ ነው የሚላከው። ያም የስራውን ውጤታማነት ይገድበዋል። ስለዚህ እርሱን ለማስተካከል ይበልጥ ተደራሽ እንድንሆን ክልሎችንም ይበልጥ ለመደገፍ አንዳንድ ማሻሻያዎችን ማድረጋችን አይቀርም። 

ክልሎች ውስጥ በወንጀል መክሰስ አንችልም። መነጋገር ይቻላል ወይ? አዎ ይቻላል። መነጋገርም ተነጋግረናል። አንድ የተወሰነ ጉዳይ ላይ ሳይሆን የምልህ በአጠቃላይ ጉዳዩች ላይ እንነጋገራለን። ግን ከንግግሩ አለፍ ብሎ የተሻለ በቅርበት ለመደገፍ የሚያስችለንን ስርዓቱን ነው መዘርጋት ያለብን። ተደራሽ ካልሆንን አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ብቻ ቁጭ ብለን በቂ መረጃውም አይኖረንም። የስማ በለው ነገር ነው የሚሆነውና ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ልንደግፋቸውም፣ የእኛ ስልጣን በሆኑ ጉዳዩች ላይም ክትትል ልናደርግ አንችልም። ያንን ደግሞ ለመለወጥ ተደራሽ መሆን አለበን፣ ጽህፈት ቤቶች መክፈት አለብን። ህጉ በሚጠይቀው መሰረት የክትትል እና የድጋፍ ስርዓትም መዘርጋት አለብን። 

ጥያቄ፦ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መምጣት በኋላ ለውጥ ተደርጓል ተብሎ በሚነገርበት ጊዜ ከሚጠቀሱ ጉዳዩች አንዱ በህጎች ላይ የተደረገው ማሻሻያ ነው። በዚሁ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ስር አማካሪ ምክር ቤት ተቋቁሞ በርካታ ህጎች ላይ ማሻሻያ ተደርጓል። ይህ አካሄድ እንደ አንድ ትልቅ እድገት ይጠቀሳል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን መንግስት እነዚሁኑ ህጎች “ተቺዎቹን ለማጥቃት ይጠቀምበታል” የሚል ውንጀላ ይቀርብበታል። ለዚህ በምሳሌነት የሽብር ህጉን መጥቀስ እንችላለን። የሽብር ህጉ ዋና ዓላማ ሽብር እና አሸባሪነትን ለመቆጣጠር ነው ተብሎ ቢነገርም አሁንም በሽብር እየተከሰሱ ያሉት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የመሳሰሉት ናቸው። ይህንን ካየን ከፍተኛ ትችት እና ቅሬታ ይቀርብበት ከነበረው የቀደመው መንግስት ምን የተሻለ ነገር ታዲያ ኖረ? ህጎቹ ቢሻሻሉም፣ የተሻሉ ለውጦች ቢኖሩም፣ ባለሙያዎች ተሳትፈው ጥረቶች ቢደረጉም ተመልሶ እዚያው አይደለም ወይ?   

ዶ/ር ጌዲዮን፦ እኔ እርሱ ትክክል ነው ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ከአሁን ወዲያ የሽብር ክስ ኢትዮጵያ ውስጥ አይመሰረተም ካልክ ህጉን የምታሻሻል ሳይሆን የምትሽረው ነው የሚሆነው። ህግ የምትሻሽለው ህጉ ያስፈልጋል ብለህ ስለምታምን ነው። ለማጥቂያ፣ ለመጨቆኚያ ቢሆን የበፊቱን ህግ ባለበት ታስቀጥላለህ። የህዝቡን ጥቅም እና የተከሳሽን መብት በተሻለ መልኩ ሚዛን የሚያስጠብቅ ህግ የምታወጣው፤ እንዲህ ያለ ችግር ቢከሰት፣ የሽብርተኝነት ባህሪ ያለው ተግባር ቢፈጸም፣ በህጉ ክስ እመሰርታለሁ ማለት ነው። ህጉ እንዲሁ ለማሳየት ብቻ የወጣ ካልሆነ፤ “ለምን ተግባር ላይ ዋለ?” ተብሎ ቅሬታ ሊቀርብ ይችላል ብዬ አላስብም። 

ጥያቄ፦ ለምን ተግባር ላይ ዋለ ሳይሆን በተለምዶ ወይም conventionally የሚታሰበው የሽብር ብያኔ አለ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያ የሽብር ብያኔ ተቀይሮ ፖለቲከኞችን ሊያውም ተቃዋሚ፣ ተቃናቃኝ እና ተቺ የሆኑትን እንደዚሁም ጋዜጠኞችን ለማጥቃት ነው እየዋለ ያለው። በፊትም እንደዚያው ነበር፤ አሁንም ያው እየሆነ ነው። ሽብር ተፈጽሞ፤ የሽብር ህጉ ለዚያ ጉዳይ ለምን ተግባራዊ ተደረገ አይደለም ክርክሩ። 

ዶ/ር ጌዲዮን፦ ጥያቄው መሆን ያለበት አንደኛ እኛ ሆኗል እያልን ያለነው፣ እያቀረብን ያለው ውንጀላ (allegation) “የሽብርን ብያኔ ያሟላል፤ አያሟላም?” ነው። ተከሳሹ “ስራው እንዲህ ነው፤ እገሌ ነው” ሳይሆን፤ አድርጓል የሚባለው ነገር የሽብር ብያኔ ውስጥ ይወድቃል ወይ? እውነትም አድርጎታል ወይ? የሚለው ነው ዋና ንግግር መሆን ያለበት። ከዚህ ጋር አብሮ ተያያዞ መታየት ያለበት ነገር አሁን high profile በሆኑት ጉዳዩች ላይ የሽብር አዋጁ የተጠቀሰው በዝግጅት፣ በማቀድ ደረጃ ነው። እዚያ ላይ ያለው ቅጣት ራሱ መደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ላይ ካለው በጣም የተለየ ቅጣት የሚጥል ወይም ክርክሩ በሚካሄድበት፣ ማስረጃ በሚቀርብበት ሂደት ላይ፣ ለዐቃቤ ህግ ወይም ለመንግስት የተለየ የሚሰጠው ጥቅም ቢኖር ኖሮ “አዎ! ይህን አዋጅ absue ለማድረግ እየተጠቀመበት ነው” ማለት ይቻላል። ነገር ግን የሚቀርቡትን ክሶች ብታያቸው በመደበኛው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ የቀረቡት፤ ይበልጥ ክብደት ያለው ቅጣት አላቸው። 

ከእነርሱ ያነሰ ቅጣት የያዘ፣ ከእነርሱ ያነሰ ክብደት ያለው፣ ከሽብር ጋር የተያያዘ ክስ ነው ያለው። ስለዚህ ከመደበኛው የወንጀል ህግ ካለው ክስ በተለየ ሁኔታ ይሄ አከራካሪ የሆነው፤ ከዚህ በፊት የነበረው ህግ ትዝታ ነው እንጂ አሁን የቀረበውን ክስ ብታየው እና ብትመዝነው የተለየ procedural advantage አይሰጥም። ከማስረጃም አንጻር የተለየ ልዩ ጥቅም (privilege) አይሰጥም። ስትመረምር ይበልጥ ለማቆየት የሚፈቅድ ነገር የለውም። ስለዚህ “አይ! በሽብር ህግ መክሰሱ እኛን ይጠቅመናል፣ ተከሳሹን ይጎዳል” የምትልበት ነገር የለውም። ክሱም ደግሞ በዝግጅት ነው። ሽብር ከወንጀሉ ባህሪ አንጻር ሲፈጸም እና ሲሞከር ብቻ ሳይሆን፤ ከሙከራ ቀደም ብሎ ባለ ጊዜም ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎች ሊያስከስሱ የሚችሉ ናቸው። እርሱን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል። 

ሌላው ሽብር የትም ሀገር ያለው ብያኔ ለሆነ የፖለቲካ ዓላማ ስትል ጉልበትን፣ ኃይልን ስትጠቀም ነው። ኃይል እና ፖለቲካ ሲደመሩ ነው። ሽብር የሚባለው ወይ ሃይማኖታዊ፣ ወይ ፖለቲካዊ፣ ወይ ርዕዮተ ዓለማዊ አጀንዳን ለማስፈጸም ስትል ህዝብን እና መንግስት ላይ ተጽዕኖ ለማሳረፍ፣ እጅ ለመጠምዘዝ ስትል የምታደርገው እንቅስቃሴ ነው። የፖለቲካ ንቅናቄ የሚያደርጉ ሰዎች ከሽብር ህግ ጋር በምንም ሊገናኙ አይችሉም ብለን መጠበቅ የለብንም። ጤነኛ በሆነ መንገድ ፖለቲካ ሲካሄድ “አዎ! አይገናኙም”። ምክንያቱም ጤነኛ በሆነ መንገድ ፖለቲካ ሲካሄድ፤ የፖለቲካ እንቅስቃሴው ሰላማዊ ነው የሚሆነው። ኃይልን፣ ጉልበትን የሚጠቀም አይሆንም። ስለዚህ የሚያስከስስም፣ ወንጀልም የሚሆን ነገር የለም። ግን ፖለቲካን ኃይል በቀላቀለ መንገድ የማራመድ ዝንባሌ እና አባዜ ሲኖር ያ የሽብር ብያኔ ውስጥ ይወድቃል ማለት ነው። 

ጥያቄ፦ መንግስት፤ ተቺዎችን ለማጥቃት ህጎችን ይጠቀማል ከሚለው ቅሬታ ጋር ተያይዞ የሚነሳው አንዱ ጉዳይ ምርጫ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ሊካሄድ በነበረበት ወቅት ላይ በጣም የተጋጋሉ የፖለቲካ ክርክሮች እና የተለያዩ አመለካከቶች ፊት ለፊት ወጥተው በሚፋጩበት ጊዜ ነው እንዲህ አይነት ጉዳይ የተከሰተው።  

ዶ/ር ጌዲዮን፦ Correlation እና causation መለየት አለብን። አብረው የሚከሰቱ ነገሮች እንዳለ ምክንያታዊ ግንኙነት አላቸው ማለት አይደለም። አዎ! እነዚህ ሰዎች መንግስትን ይተቻሉ። ግን መንግስትን ስለተቹ አይደለም የታሰሩት ወይም ክስ የቀረበባቸው። ያንን correlation ወደ causation መለወጥ የለብንም። ለምንድነው እንዲህ የምለው? ሰሞኑን በነበረው ክስተት “የሽብር ክስ ቀርቦባቸዋል” የሚባሉት ሰዎች ላይ የተለያዩ ክሶች ናቸው ያሉት አይደል? ያንን ራሱ ብታወጣው እነዚህ ሰዎች ከባድ በሆነ፣ ለሽብር ዝግጅት በከበደ ወንጀል ተከስሰዋል። ህዝብን በህዝብ ላይ ማነሳሳት፤ ግጭት መፍጠር በሚል ተከስሰዋል። ስለዚህ ይሄ ከዚህ በፊት ከነበረው የሽብር ህግ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው ልምድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው መጥፎ ትዝታ አንጻር ሰዎች እንደዚህ አይነት ጥያቄ ቢያነሱ እረዳለሁ። ግን ሙሉ ምስሉን ማየት አለብን። 

እና ደግሞ እዚህ ጋር ማየት ያለብን ከዚህ ቀደም ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎች ታስረዋል። በዚያ ጊዜ አይደለም የሞተ ሰው፣ የተሰበረ መስኮት ነበር ወይ? ብዙ ፖለቲከኛ፣ ተቺ የታሰረ ጊዜ፤ እንደው እዚህ ጋር እንኳ፤ እንዲህ ሆኗል የምትለው ምንም አይነት ክስተት አልነበረም። አሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። ብዙ ንብረት ወድሟል። አንዳንድ ከተሞች ghost town መስለዋል። እነዚያን ነገር ያደረጉት ሰዎች ዝም ብለው በግብታዊነት ተነስተው፣ እንዲሁ ወጣቶች በባዶ ሜዳ ተነስተው ድንገት ያደረጉት ነገር አይደለም። ከተገደለው ሰው፣ ከጠፋው ንብረት ጀርባ ያንን የቀሰቀሰ፣ ያንን ያነሳሳ የንግግር እና የቅስቀሳ ስራ አለ። ጽንፍ የሆነ ኃይልን የቀላቀለ ብሔርተኝነትን ያቀነቀኑ እንስቃሴዎች አሉ። የደረሰው ነገር ላይ violent የሆነ ultranationalism ከጀርባው ነበረ። 

ስለዚህ እነዚህ ኃይልን የቀላቀለ ጽንፍ ብሔርተኝነትን ያራመዱ ሰዎች ፖለቲከኛ ስለሆኑ፣ መንግስትን ስለሚተቹ ያለመከሰስ መብት (immunity) ሊኖራቸው አይችልም። መንግስትን የመተቸት መብት አላቸው፤ ያ መከበር አለበት። ግን ደግሞ መንግስትን ስለሚተቹ ሌላ ወንጀል ሲፈጽሙ፣ ሌላ ነገር ሲያጠፉ፣ መንግስት “አይ! በቃ ተቺዎች ስለሆኑ አልታመንም” ብሎ ጸጥ ካለ፤ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ጉዳት እና ኪሳራ ከዚህም የባሰ ይሆናል። 

አንዳንዱን ሰው እንደውም ብትጠይቅ የሚነግርህ፣ እኛም በተለያዩ መድረኮች መንግስት ላይ ሲነሳ የሰማነው “እርምጃ እየወሰደ አይደለም፤ ህግ እያስከበረ አይደለም፤ እኛን እየተከላከለ አይደለም” የሚል ነው። “ለውጥ ላይ ነኝ፣ ወደ ዲሞክራሲ ሽግግር እያደረግኩ ነኝ በሚል ካለመጠን በመታገስ ለጥቃት ተጋላጭ እያደረገን ነው” የሚልም ብዙ ህዝብ አለና መንግስት አማራጭ የለውም። መንግስት፤ መንግስት እስከሆነ ድረስ፤ ኃይልን እየተጠቀመ፣ የኃይል እርምጃ እየወሰደ የሚንቀሳቀስን ፖለቲከኛ ወይም አክቲቪስት tolerate አድርጎ፣ መንግስትም ሆኖ መቀጠል አይችልም። ህዝብ ቢያንስ ቢያንስ ያንን እንዲከላከልው ይጠብቃልና በዚያ መንገድ መታየት አለበት ብዬ አስባለሁ። 

ጥያቄ፦ መጪው ምርጫ ከመሆኑ አንጻር እነዚህ በጣም የታወቁ እና በበርካታ ህዝብ ዘንድ ድጋፍ ያላቸው ወይም ተከታይ ያላቸውን ሰዎች አስቀድሞ ማድረግ የሚቻል ሆኖ ሳለ ልክ ምርጫው ሲቃረብ እንዲህ አይነት ነገር ማድረግ ተቀናቃኞችን ለማጥፋት የሚደረግ ወይም ምርጫውን በብቸኝነት ለማሸነፍ የሚደረግ ጥረት አይደለም ወይ?

ዶ/ር ጌዲዮን፦ እንግዲህ በባዶ ሜዳ፣ ዝም ብሎ ድንገት መንግስት እነዚህን ሰዎች አስሮ ክስ እየመሰረተ ቢሆን እንደዚያ የሚለው ነገር ሊያሳምን ይችላል ግን በዚህ ንግግር ላይ ትንሽ ጥያቄ የሚሆንብኝ ነገር የሞቱትን ሰዎች፣ የቆሰሉትን፤ እነርሱን ለምንድነው የምንረሳቸው? ረጅም ጊዜ እኮ አይደለም፤ ከሁለት፣ ከሶስት ወር በፊት የሆነ ነገር ነው። እና “ከምርጫ እገሌን ወይም እገሌን አስወጣለሁ” በሚል ሂሳብ ነው ተብሎ የሚመጣው ክስ እየረሳ ያለው ነገር፤ የደረሰውን ጉዳት፣ የደረሰውን ውድመት፣ የደረሰውን ጥፋት ነው። ይህን ሁሉ ረስቶ ምርጫ እና ፖለቲከኞች ብቻ ያሉብት ያስመሰለ ነው። 

በዚህ ሀገር ላይ ፖለቲከኛ እና ፓርቲ ብቻ አይደለም ያለው። የቀን ተቀን ኑሮውን የሚገፋ፣ መደበኛው ዜጋ እየደረሰበት ያለው ጉዳት፣ የደረሰበት ሰቆቃ፣ የደረሰበት በደል እና ጥፋት መታየት አለበት። ምርጫው እንዲደምቅ፣ ምርጫው ፉክክር ያለበት እንዲሆን ተብሎ፣ ተጠያቂነት ቀርቶ፣ ሰዎች እንደዚህ አይነት ጉዳት እየደረሰባቸው መቀጠል አይቻልም። መንግስት ህግ ከማስከበር፣ እንዲህ ያለ እርምጃ ከመውሰድ ውጪ አማራጭ የለውም። ምርጫ እኮ የሚኖረው ሀገር ሲኖር ነው። በመቶ የሚቆጠር ሰው እየሞተ፣ እንደዚያ ያለ ጥቃት እየደረሰበት፣ ሀገርም ምርጫም ማሰብ አይቻልም። ስለዚህ ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል እንዲህ ያለ እርምጃ መወሰድ አለበት። 

“ ምርጫው እንዲደምቅ፣ ምርጫው ፉክክር ያለበት እንዲሆን ተብሎ፣ ተጠያቂነት ቀርቶ፣ ሰዎች እንደዚህ አይነት ጉዳት እየደረሰባቸው መቀጠል አይቻልም። መንግስት ህግ ከማስከበር፣ እንዲህ ያለ እርምጃ ከመውሰድ ውጪ አማራጭ የለውም”

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ – የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

ከዚህ ጋር አያይዤ ደግሞ የማነሳው አሁን በጣም ታዋቂ የሆኑ ሰዎች እነርሱን ተጠያቂ ለማድረግ እርምጃ ሲወሰድ ነው እንዲህ ያለ ጥያቄ የሚመጣው። ቀደም ሲል ተመሳሳይ የሆኑ ግጭቶች በተለያየ አካባቢዎች፣ ክልልም ላይ ሲደርሱ በቁጥጥር ስር የሚውሉ፣ ተመሳሳይ ክስ የሚመሰረትባቸው ሰዎች አሉ። ስለዚህ የተወሰኑ ሰዎች ታዋቂ ስለሆኑ ተጠያቂ ሳያደረጉ፣ የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ ታዋቂ ስላልሆኑ ተጠያቂ እየተደረጉ፤ እንደዚያ ልትለያይ አትችልም። ደም ፈስሶ፣ እንደዚህ ያለ ጉዳት ደርሶ፣ ሰዎች ሞተው በዚህ ጉዳይ ላይ በትንሹ መንግስት ማድረግ የሚችለው እርምጃ መውሰድ ነው።

ጥያቄ፦ ይሄ ጥያቄ እየተነሳ ያለው “ጥቃቱን በትክክል የፈጸሙት ሰዎች እየተጠየቁ አይደለም” ከሚል መነሻ ነው። በተለያዩ ቦታዎች ያንን ወንጀል ፈጸሙ የተባሉ ሰዎች የደረሱበት አይታወቅም። “ከተለያዩ አካባቢዎች ነው የመጡት፤ አናውቃቸውም” ይባልና እንደገና የሆነ አጋጣሚ በሚፈጠርበት ወቅት ተመሳሳይ ጥቃት እየተከሰተ ነው። 

ዶ/ር ጌዲዮን፦ አሁን ኦሮሚያ ውስጥ ምን ያህል ሰው በቁጥጥር ስር እንደዋለ እንግዲህ ታውቃለህ። ተጠርጣሪ ብለን የለየናቸው ሁሉም ሰዎች አልተያዙም። ያመለጡ፣ የሸሹ፣ አሁንም እየተፈለጉ ያሉ አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ እየተፈለጉ፣ ከተለያየ ቦታም ተይዘው የተወሰዱ አሉ። በሺህዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች ላይ ነው በዚህ ሳምንት ክስ እየተመሰረተ ያለው። ስለዚህ ታች መሬት ላይ ድርጊቱን የፈጸሙትን ሰዎች ባገኘነው ማስረጃ ልክ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ክስ እየተመሰረተ ነው።

ግን እነርሱ ብቻቸውን አይደለም ተጠያቂ መሆን ያለባቸው። በየደረጃው ተጠያቂ መሆን ያለበት አለ። ድርጊቱን የፈጸሙት ብቻ ሳይሆኑ በዚያ አካባቢ በመንግስት መዋቅር ስር ያሉ ሰዎች ራሱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት ተጠያቂ እየተደረጉ ነው። ስለዚህ ከተቃዋሚ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ከገዢው ፓርቲ ራሱ ተጠያቂ እየተደረጉ ያሉ ሰዎች አሉ። እዚያው ቅርብ ቦታ ሆነው “እንዲህ ቢያደርግ፣ በዚህ መልክ ጣልቃ ቢገባ ኖሮ በቀላሉ የደረሰውን ጉዳት መከላከል ይቻል ነበረ” ተብሎ አሳማኝ መረጃዎች በቀረበባቸው ቦታዎች ማለት ነው። ስለዚህ እኔ በዚህ መንገድ ነው የማየው። 

ጥያቄ፦ የመጨረሻው ጥያቄዬ ከክስ ጋር የሚያያዝ አይደለም። ከዚሁ መስሪያ ቤት ነጻነት እና ገለልተኝነት ጋር የተያያዘ ነው። እርስዎ ወደ ሹመት ሲመጡ በሚያውቁዎት ሰዎችም ይሁን፣ ከዚህ በፊት በነበሩት ስራዎችዎ በሚያውቁዎት ዘንድ የተነሳው ነገር፤ “ትክክለኛ ሰው ለቦታው ተሾመ ወይም ደግሞ ገለልተኛ ሰው ለቦታው መጣ” የሚል ነበር። ከእርስዎ በፊት በዚህ ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች፣ በገዢው ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ጭምር ያሉ ፖለቲከኞች ስለነበሩ “መቼ ነው ይሄ መስሪያ ቤት ከፖለቲካ ውጪ የሚሆነው” የሚል ጥያቄ ይነሳ ነበር። እርስዎ አሁን የገዢው ፓርቲ አባል ሆነዋል?  

ዶ/ር ጌዲዮን፦ እርሱን ክርክር እና ጥያቄ አይቼዋለሁ። Formally አባል አይደለሁም። ያው አባል የሚኮነው ፎርም ተሞልቶ ነው መሰለኝ። ስለዚህ እንደዚያ አይነት አባል አይደለሁም። አባል ባልሆንም አሁን እኔ የመንግስት አካል ነኝ። እያገለገልኩት ያለበት መንግስት ደግሞ የሆነ ፓርቲ የሚመራው ነው። ስለዚህ ከዚያ ፓርቲ አስተሳሰብ እና ፕሮግራም በጣም የተቃረንኩ ብሆን ኖሮ የመንግስት ኃላፊነትን አልቀበልም ነበር። 

ስለዚህ አጠቃላይ እየተወሰደ ባለው፣ ተግባራዊ ለማድረግ በሚሞከረው የለውጥ እንቅስቃሴ እርምጃ ስለማምን እና በእርሱ መደገፍ እችላለሁ ብዬ ስላሰብኩኝ ነው ይህን ኃላፊነት የተቀበልኩት። የፓርቲው አባል ባልሆንም ከፓርቲው ጋር እየሰራሁ ያለሁ ነኝ። “አባል ነው፤ አይደለም” የሚለው ክርክር ጠቀሜታው ለእኔ እምብዛም ነው። ተምሳሌታዊ (symbolic) የሆነ ነገር አለው። ግን ከአንድ ግለሰብ አባልነት ባለፈ ነው የተቋሙ ነገር መታየት ያለበት። 

ጥያቄ፦ እርሱ እኮ ነው ጥያቄው። የገለልተኝነት ጥያቄ ስለሚነሳ አሁን ያ እየተከበረ ነው ወይ? ወይስ ለመወለወጥ እየሞከራችሁ ነው?

ዶ/ር ጌዲዮን፦ እርሱን በተመለከተ አንደኛ ከእኔ አባልነት ጥያቄ ሰፋ ተደርጎ እንዲታይ ነው የምፈልገው። ሁለተኛ ደግሞ ሂደትም እንደሆነ ከግምት መግባት አለበት። ባለፈው ሁለት ዓመት ተግባራዊ የተደረገ ነገር፤ ከዚህ በፊት ባለሙያ የሆኑ ዐቃቤ ህጎች የፓርቲ አባል የሚሆኑበት አሰራር ነበር። አሁን በአመራር ደረጃ ካሉ ከዋናው እና ከምክትሉ በስተቀር ያሉትን ዐቃቤ ህጎች እንዳለ የፓርቲ አባልነት የሚከለክል መመሪያ አለ። ስለዚህ በህግ ደረጃ አሁን ለአንድ ዐቃቤ ህግ የፓርቲ አባል መሆን ክልክል ነው። 

ጥያቄ፦ ይሄ መመሪያ ወጥቶ ጸድቋል፤ ተግባራዊ እየተደረገ ነው እያሉኝ ነው?   

ዶ/ር ጌዲዮን፦ አዎ። ሁለት ዓመት ይሆነዋል። እንዳልኩህ ግን exception አስቀምጠዋል። ይሄ ዋናውን ዐቃቤ ህግ እና ምክትሎቹን አይጨምርም። ከእነርሱ ውጪ ዐቃቤ ህግ ሆኖ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆነ ካለ፤ እርሱ የዲስፒሊን ጥሰት ነው። እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ነው ማለት ነው። ይሄ ከሌሎች የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ካለው አሰራር የተለየ ነው። ይሄ ጅማሮ ነው። “ይሄ ብቻ ነው ወይ መሆን ያለበት? ዋናው እና ምክትሉ፣ እነርሱስ ቢሆኑ?” የሚል ክርክር ይነሳል። ተገቢነት ያለው ውይይት ነው። ግን ይሄንን እንደመጀመሪያ አድርጎ በተጨማሪነት ገለልተኝነትን እና ነጻነትን ለማጠናከር ምን እርምጃ መወሰድ አለበት የሚለውን መነጋገር ያስፈልጋል።

አንድ ከዚሁ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ነገር አሁን እኛ ጋር ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የዐቃቤ ህግ ሞዴል በራሱ ሁለት ሚናዎችን የቀላቀለ ነው። አንደኛ ይሄ ቢሮ መንግስትን በህግ ጉዳዩች የሚያማክር ነው። ህግ የሚያረቅቅ፣ የህግ ጥናት የሚያካሂድ ነው። የመንግስትን ፖሊሲ የሚያስፈጽም ነው። ይህ ልክ እንደማንኛውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባህሪ የሚያሰጠው ነው። የፖለቲካ አመራሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ምንድን ነው? ፖሊሲው ምንድን ነው? ከዚያ ያንን ዓላማ ለማሳካት ደግሞ ይሄንን መስሪያ ቤት ካለው ስልጣን እና ኃላፊነት አንጻር ምን ማድረግ አለበት? የሚለውን አቅዶ፣ አስቦ መንቀሳቀስ ይጠይቃል። 

 “እዚህ ጋር እኔ እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው ነገር፤ አሁን ባሉ ክሶች እና ክርክሮች ላይ ዐቃቤ ህጎቹ እና ባለሙያዎቹ ምንም አይነት የፖለቲካ ተጽዕኖ እንዳያርፍባቸው ማድረግ ተችሏል”

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ – የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

ሌላ ክንፍ ደግሞ አለ። ይህ ህግ ማስከበር፣ ምርመራ ማድረግን [ያካትታል]። በሁለቱም ጎኖች ያሉት የሚጠይቁት ነገር አለ። ይሄኛው በተቻለ መጠን ገለልተኝነት እና ነጻነትን ይጠይቃል። ያኛው ደግሞ የመንግስትን አጠቃላይ አቅጣጫ፣ ፖሊሲ፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች እና የፖለቲካ ዓላማዎች ራሱ መረዳት ይጠይቃል። ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ከህግ አስከባሪዎች ውጪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል ነው። መንግስት ሲባል በፓርላሜንታዊ ስርዓት፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው። ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል ነው ስለዚህ የመንግስት አካል ነው። ይህንን አሰራር በሂደት፣ አስፈላጊ በሆነው ደረጃ፣ በአወቃቀር እንዴት ነው መሆን ያለበት? የሚለው መታየት ሊኖርበት ይችላል። 

ግን እዚህ ጋር እኔ እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው ነገር፤ አሁን ባሉ ክሶች እና ክርክሮች ላይ ዐቃቤ ህጎቹ እና ባለሙያዎቹ ምንም አይነት የፖለቲካ ተጽዕኖ እንዳያርፍባቸው ማድረግ ተችሏል። የፓርቲ አባል አይደሉም፤ ባለሙያዎች ናቸው። ማስረጃውን ገምግመው ባደረጉት ምርመራ፣ ባደረጉት ማጣራት ልክ “ይሄን ክስ ነው መመሰረት ያለብን” ብለው፤ ሙያዊ በሆነ መንገድ ወስነው ራሳቸው ክስ እንዲመሰርቱ ነው እየተደረገ ያለው። ስለዚህ ይህንን በተመለከተ ከዚህ በፊት እዚህ ተቋም ላይ ነበረ ከሚባለው በጣም መሻሻል አለ ብዬ አስባለሁ። ለወደፊትም  ከዚህ የተሻለ መሻሻል አለበት ብዬ አምናለሁ። አንዳንዱ የመሻሻል ነገር የግንዛቤም ሊሆን ስለሚችል እርሱንም ለማሻሻል መጣር አለብን ብዬ አምናለሁ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)