በተስፋለም ወልደየስ
እስክንድር ነጋን ጨምሮ አራት ተከሳሾች ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ። በተመሳሳይ መዝገብ ተከስሰው በእስር ላይ የሚገኙት ጌትነት በቀለ የተባሉ ተከሳሽ ደግሞ በ30 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕገመንግስትና የሽብር ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ማክሰኞ መስከረም 19፤ 2013 ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ካቀረባቸው ሁለት ክሶች መካከል አንደኛውን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ነበር። ዐቃቤ ህግ ክሱን እንዲያሻሻል ትዕዛዝ የተሰጠው፤ ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ የዋስትና መብት ላይ በቀረበው ክርክር ላይ ውሳኔ ለመስጠት ያስችለው ዘንድ “ክሱ በግልጽ መቅረብ ይገባዋል” በሚል ምክንያት ነው።
ይሻሻል የተባለው በመጀመሪያው ክስ፤ ተከሳሾቹ “አንዱን ወገን በሌላው ላይ የጦር መሳሪያ እንዲያነሳ አነሳስተዋል” ሲል ይወነጅላል። በዚህም አድራጎታቸው በመንግስት ላይ በሚደረግ ወንጀል ፈጽመዋል” መከሰሳቸውንም ያትታል። ጉዳዩን የሚመለከተው ፍርድ ቤት ግን ባለፈው ሳምንት በነበረው ችሎት፤ በክሱ ውስጥ “ድርጊቱ መቼ እና እንዴት እንደተፈጸመ እንዲሁም ያስከተለው ጉዳት በዝርዝር መቅረብ ነበረበት” ሲል ክሱ በምን አግባብ መሻሻል እንዳለበት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ዐቃቤ ህግ በዚህ መሰረት ያሻሻለውን ክስ ለፍርድ ቤቱ ዛሬ ያቀረበ ሲሆን ለተከሳሾቹ እና ጠበቆችም እንዲደርሳቸው ተደርጓል። በችሎቱ በንባብ በተሰማው የተሻሻለው የክስ ክፍል ላይ ሰኔ 23 እና 24፤ 2012 በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጠሩ የተባሉ የእርስ በእርስ ግጭቶች በዝርዝር ቀርበዋል።
የዘጠኝ ሰዎች ህይወት የጠፋበት የሰኔ 23ቱ ግጭት በአዲስ አበባ አራዳ፣ ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ፣ ኮልፌ እና ልደታ ክፍለ ከተሞች መከሰቱን የሚገልጸው የተሻሻለው የክስ ሰነድ፤ ድርጊቱም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት እስከ 12 መፈጸሙን ጠቁሟል። በበነጋታው ሰኔ 24 የነበረው ግጭት የተቀሰቀሰው ከማለዳው 12 ሰዓት ከ30 እንደነበር የሚያብራራው የክስ ሰነዱ፤ ሁከቱ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ቀጥሎ እንደነበር ይገልጻል። ይህን ግጭት ተከትሎ በንፋስ ስልክ እና አራዳ ክፍለ ከተሞች አምስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉንም ይጠቅሳል።
ተከሳሾቹ አነሳስተውታል በተባለው በዚህ ግጭት ከሞቱት 14 ሰዎች በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ በስምንት ክፍለ ከተሞች በአጠቃላይ 187 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የዐቃቤ ህግ የተሻሻለ ክስ ያስረዳል። ተከሳሾቹ በቀጥታ በወንጀሉ ድርጊት እና በሚሰጠው ሙሉ ውጤት ተካፋይ በመሆን፤ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት ወንጀል መከሰሳቸውንም አመልክቷል።
በተሻሻለው ክስ ላይ በመመርኮዝ ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች የዋስትና መብት ጉዳይ የቀረበውን ክርክር መመልከቱን በዛሬው የችሎት ውሎ ተገልጿል። የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኞቻቸውን የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ያቀረቧቸውን መከራከሪያዎች በዝርዝር የተመለከተው ፍርድ ቤቱ፤ ከተነሱት ነጥቦች አንዱን ብቻ በመቀበል ሌሎቹን ውድቅ አድርጓቸዋል። ፍርድ ቤቱ በክስ መዝገቡ ላይ ከአንደኛ እስከ አራተኛ የተዘረዘሩት ተከሳሾች ያቀረቡቱን የዋስትና ጥያቄ በመንፈግም፤ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ብይን ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ዋስትናውን ለመከልከል በምክንያትነት ከጠቀሳቸው ውስጥ ተከሳሾቹ በተጠረጠሩበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን ነው። ከዚህም ባሻገር በተከሳሾች አነሳሽነት የ14 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ዐቃቤ ህግ በክስ ዝርዝሩ ውስጥ መግለጹ ከግምት ውስጥ መግባቱን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።
አምስተኛ ተከሳሽ በሆኑት አቶ ጌትነት በቀለ ላይ የቀረበው ክስ የተፈጸመው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሆኑን ያስታወሰው ፍርድ ቤቱ፤ ሆኖም ዐቃቤ ህግ አሻሽሎ ባቀረበው ክስ ላይ በዚህ ክፍለ ከተማ የሞተ ሰው አለመኖሩንም ጠቅሷል። ይህም የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግ አንቀጽ 63ን የሚያሟላ ሆኖ አለማግኘቱን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፤ በዚህ መሰረት ተከሳሹ ዋስትና ሊነፈግ እንደማይገባው አብራርቷል። ዐቃቤ ህግ ተከሳሹ በዋስትና ቢወጣ “ሌላ ወንጀል ይፈጽማል” ቢልም ፍርድ ቤቱ ግን ተከሳሹ በዋስ ከእስር ተለቅቆ፣ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል በሙሉ ድምጽ ብይን መስጠቱን በችሎቱ ከተሰየሙት ሶስት ዳኞች አንዷ ተናግረዋል።
የአቶ ጌትነትን የስራ ሁኔታ በተመለከተ የማጣሪያ ጥያቄዎች ያቀረቡት ዳኛዋ፤ ተከሳሹ 30 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ ከእስር እንዲፈታ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱን ገልጸዋል። ተከሳሹ ከሀገር እንዳይወጣ ፍርድ ቤቱ እገዳ ማድረጉን የተናገሩት ዳኛዋ ይህንኑ የሚያመለክት ደብዳቤ ለኢሜግሬሽን እና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ እንደሚጽፍም አክለዋል።
የፍርድ ቤቱን ብይን ተከትሎ አንደኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ ሶስት አቤቱታዎችን ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል። በቀጣዩ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እየተዘጋጁ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሊቀመንበር፤ ከእስር ወጥተው በምርጫው መሳተፍ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ለምርጫው “የሚጠብቀን ህዝብ አለ” ያሉት አቶ እስክንድር ምርጫው እንዳያመልጣቸው ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸውን በአፋጣኝ እንዲመለከት ጠይቀዋል። የፍርድ ሂደቱ እንዳይጓተትም ዳኞች ከበላይ አካላት ጋር ተነጋግረው መፍትሄ ይፈልጉ ዘንድም አሳስበዋል። አሁን ከቀረበባቸው ክስ “በነጻ እንደምንወጣ ምንም ጥርጥር የለኝም” ሲሉም እምነታቸውን ገልጸዋል።
አቶ እስክንድር በሁለተኛነት ያቀረቡት አቤቱታ ባለፈው በነበረው የችሎት ውሎ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝ አለመፈጸሙን የተመለከተ ነበር። ችሎቱ ባለቤታቸውን እና ልጃቸውን በስልክ ማግኘት እንደሚችሉ ባለፈው ችሎት ትዕዛዝ መስጠቱን የጠቀሱት ተከሳሹ ሆኖም አሁን ያሉት ማረሚያ ቤት ትዕዛዙ በጹሁፍ አልደረሰኝም በማለት ቤተሰባቸውን በስልክ ማነጋገር እንዳልፈቀደላቸው ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ለማረሚያ ቤት እንዲያደርስም የችሎቱን ዳኞች ጠይቀዋል።
ተከሳሹ ወደ ማረሚያ ቤት ከወረዱ አስራ አምስት ቀናት ማለፉን ጠቅሰው ወደዚያ ይዘዋቸው የመጧቸው 20 መጽሐፍት እና 30 ገደማ መጽሔቶችን ማግኘት እንዳልቻሉ ለፍርድ ቤቱ በተጨማሪነት አመልክተዋል። የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር መጽሐፍቱን እና መጽሔቶቹን “ሳንሱር አድርገን እንሰጣሃለን” ማለታቸውን፤ ነገር ግን በተደጋጋሚ እስከ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ድረስ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን አብራርተዋል።
“ከክሱ በነጻ እንደምንወጣ ምንም ጥርጥር የለኝም”
– እስክንድር ነጋ ዛሬ በፍርድ ቤት ከተናገረው
የአቶ እስክንድርን አቤቱታዎች የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ምላሽ እና ትዕዛዞች ሰጥቷል። ተከሳሹ ያቀረቡትን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት ጥያቄ ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርቡ የተናገሩት የግራ ዳኛ፤ ጉዳዩ ወደፊት በሁለት ችሎቶች ሊታይ እንደሚችል ጠቁመዋል። ፍርድ ቤቱ አቶ እስክንድር ከቤተሰባቸው ጋር በስልክ እንዲገናኙ በድጋሚ “ጥብቅ ትዕዛዝ” የሰጠ ሲሆን ይህንንም በጹሁፍ ለማረሚያ ቤቱ እንደሚልክ አስታውቋል። የመጽሐፍትን ጉዳይ በተመለከተም “ሳንሱር ተደርጎ ለምን ለተከሳሹ እንዳልተመለሰ” ማረሚያ ቤቱ በቀጣይ ቀጠሮ ምላሹን በጹሁፍ እንዲያቀርብም ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ ጠበቆች፤ በተሻሻለው ክስ ላይ የሚያቀርቡትን መቃወሚያ በጽህፈት ቤት ለመቀበል ለመስከረም 29 ቀጠሮ ሰጥቷል። ዐቃቤ ህግ በክስ መቃወሚያ ላይ የሚሰጠውን ምላሽ ተከሳሾች በሚገኙበት በችሎት ለመቀበል ደግሞ ለጥቅምት 12፤ 2013 ቀጥሯል።
በዛሬው ችሎት ሁለተኛ ተከሳሽ ስንታየሁ ቸኮል፣ ሶስተኛ ተከሳሽ ቀለብ ስዩም እና አራተኛ ተከሳሽ አስካለ ደምሌ በማረሚያ ቤት ካለው አያያዛቸው እና ከቀረበባቸው ክስ ጋር በተያያዘ አቤቱታቸውን አሰምተዋል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከሃይማኖት አባቶቻቸው እና ከጠበቆቻቸው ጋር የመገናኘት መብት እንዳላቸው በመጥቀስ ይህንን እንዲያስፈጽም ማረሚያ ቤቱን አዝዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)