ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ90 ዓመታቸው አረፉ

በተስፋለም ወልደየስ 

ከኢትዮጵያ የአደባባይ ምሁራን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ90 ዓመታቸው አረፉ። ፕሮፌሰር መስፍን ያረፉት ትላንት ማክሰኞ መስከረም 19፤ 2013 ምሽት አምስት ሰዓት አካባቢ እንደሆነ ቤተሰቦቻቸው እና የቅርብ ሰዎቻቸው ገልጸዋል። 

አንጋፋው ምሁር በኮሮና በሽታ ተይዘው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ሆስፒታል ላለፉት 11 ቀናት ህክምናቸውን ሲከታተሉ እንደነበር ልጃቸው መቅደስ መስፍን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እስከ ትላንትና ድረስ ከአባታቸው ጋር መነጋገራቸውን የገለጹት መቅደስ፤ እስካለፈው ቅዳሜ ድረስ በደህና ሁኔታ ላይ እንደነበሩ አስረድተዋል። 

ፕሮፌሰር መስፍን ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት አጠገባቸው የነበረ ሰው በመታመሙ ምክንያት እንደነበር የሚገልጹት ልጃቸው፤ ሁለቱም በተደረገላቸው ምርመራ በኮቪድ 19 በሽታ መያዛቸው ተረጋግጧል ብለዋል። ሆስፒታል ከገቡ ከቀናት በኋላም በእርሳቸው ህመም ለተጨነቁ ወዳጆቻቸው፤ ደህና መሆናቸውን የሚገልጽ መልዕክት በልጃቸው በኩል አስተላለፈው ነበር።    

“ሆስፒታል ገብቶ ራሱ፤ ‘እኔ አስታማሚ ሆኜ ነው የመጣሁት’ እያለ ይጫወት ነበር። [ባለፈው ሳምንት] ረቡዕ እንደውም አብሮት የነበረው ሰው እየተሻለው ሲመጣ ‘እንደገና መርምሩኝና ከሆስፒታል ልውጣ’ ብሎ ጠይቆ ነበር። ሐሙስ መታመም ጀመረ። ሆስፒታል በገባ በሳምንቱ ቅዳሜ ነው ‘ሲሪየስ’ የሆነ ነገር ያየነው። እንጂ ደህና ነበር” ሲሉ አባታቸው በሆስፒታል የነበሩበትን ሁኔታ ልጃቸው መቅደስ አብራርተዋል። 

ፕሮፌሰር መስፍን ወደ ሆስፒታል ከመግባታቸው ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ጭምር፤ ለረጅም ዓመታት ጉልህ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩበትን የኢትዮጵያን ፖለቲካ የተመለከቱ የተለያዩ ጽሁፎችን በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ሲያስነብቡ ቆይተዋል። መስከረም 7፤ 2013 በፌስ ቡክ ገጻቸው የወጣው የመጨረሻው ጽሁፋቸው “ትውልዶችን” የተመለከተ ነበር። “በምጽዋትና በሞግዚት አስተዳደር የሚኖር ትውልድ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስተላልፈው ዕዳ ብቻ ነው። ዕዳን በውርስ ተሸክሞ የሚፈጠር ትውልድ ያለምርኩዝ መንቀሳቀስ አይችልም” ሲሉ በመጨረሻ ጹሁፋቸው አስፍረዋል።

አድናቂዎቻቸው “የኔታ” እያሉ የሚጠሯቸው ፕሮፌሰር መስፍን፤ ማህበራዊ ትስስር ገጾችን ጨምሮ በመጽሐፍት፣ በመጽሔቶች፣ በመገናኛ ብዙሃን ቃለ መጠይቆች እና በአደባባይ ውይይቶች ትችቶችን እና ሸንቋጭ አስተያየቶችን በመሰንዘር ይታወቃሉ። ባለፈው ሳምንት ገበያ ላይ የዋለው “ዛሬም እንደትናንት” የተሰኘ የመጨረሻ መጽሐፋቸውን ጨምሮ አብዛኞቹ ለንባብ ያበቋቸው መጽሐፎችም በፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሂስ የተቃኙ ናቸው።

ከአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉ መሪዎችን በመገዳደር የሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ወደ ፖለቲካ ያመጣቸው ጉዳይ በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሰተው ረሃብ እንደሆነ ደጋግመው ይናገሩ ነበር። በኢትዮጵያ አስከፊ ከሚባሉት የረሃብ ጊዜዎች አንዱ የነበረውን የ1966ቱን ረሃብ በህዝብ ዘንድ እንዲታወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ፕሮፌሰሩ ያስተምሩበት በነበረው የያኔው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ዘመቻ በማድረግ ጭምርን የረሃቡን እውነታ ለአደባባይ አብቅተዋል።         

በየጊዜው በሚያነሷቸው ሀሳቦች ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ የቆዩት ምሁሩ፤ በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ከአንድም ሁለት ጊዜ በእስር ለማሳለፍም ተገድደዋል። በ1997 ዓ. ም. በኢትዮጵያ የተካሄደው የኢትዮጵያ ምርጫ ተከትሎ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ለእስር በተዳረጉበት ወቅት እርሳቸውም ከአጋሮቻቸው ጋር ሁለት ዓመት የሚጠጋ ጊዜን በእስር አሳልፈዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ምርጫው ከመካሄዱ ወራት አስቀድሞ የተቋቋመው የቀስተ ደመና የማህበራዊ ፍትህ ንቅናቄን ከመሰረቱት ውስጥ አንዱ ነበሩ። ንቅናቄው በምርጫው ወቅት ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ላገኘው የቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ ጥምረት ምስረታ ቁልፍ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይነገርለታል። 

የኢትዮጵያ ሚሊኒየምን ምክንያት በማድረግ እርሳቸውን ጨምሮ የቅንጅት አመራሮች በይቅርታ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በተመሰረተው የአንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲም ፕሮፌሰር መስፍን ተሳትፎ ነበራቸው። ፕሮፌሰሩ በፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበሩ። 

ፕሮፈሰር መስፍን በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብት መከበር ባደረጉት አስተዋጽኦም ይዘከራሉ። በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥ እና በመሰነድ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ (ኢሰመጉ) የተመሰረተው በእርሳቸው ነበር።  የዲሞክራሲ፣ ለህግ የበላይነት እና የሰብዓዊ መብት መከበርን ዓላማው አድርጎ የተቋቋመው ኢሰመጉ የተመሰረተው በ1984 ዓ.ም ነው። 

በፖለቲካ ተሳትፏቸው እና በአደባባይ ምሁርነታቸው ይበልጥ የሚታወቁት ጎምቱው ምሁር፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጂኦግራፊ የትምህርት ክፍል ለረጅም ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል። በሚያስተምሩበት የትምህርት ክፍል የኮሌጅ መማሪያ መጽሐፍን ለመጀመሪያ ጊዜ ማዘጋጀታቸውንም በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። 

ከዚያ በኋላ ባሉ ዓመታትም ከሙያቸው ጋር ከተያያዙ መጽሐፍት ባሻገር በኢትዮጵያ ረሃብ እና ፖለቲካ ላይ ያተኮሩ በርካታ መጽሐፍትን በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ አሳትመዋል። ፕሮፌሰር ከጻፏቸው መጽሐፍት መካከል “ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ”፣“አገቱኒ፤ ተምረን ወጣን”፣ “አዳፍኔ፤ ፍርሃትና መክሸፍ”፣ “እንዘጭ እምቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ”፣ “ሥልጣን – ባህልና አገዛዝ፤ ፖለቲካና ምርጫ”  እና “ዛሬም እንጉርጉሮ” ይጠቀሳሉ። 

የፕሮፌሰር መስፍን የቀብር ስነ ስርዓት መቼ እንደሚከናወን ገና እንዳልተወሰነ ልጃቸው መቅደስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እርሳቸውን ጨምሮ በውጭ ሀገር ያሉ ቤተሰቦቻቸው ወደ ሀገር ቤት ከመጡ በኋላ የኮሮና በሽታን ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደሚፈጸምም ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)