በቀድሞ የወላይታ ዞን አመራሮች እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

በተስፋለም ወልደየስ

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የወላይታ ዞን የቀድሞ አመራሮችን ጨምሮ ለ20 ተጠርጣሪዎች የስር ፍርድ ቤት በፈቀደው ዋስትና ላይ እና ፖሊስ በጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ላይ ብይን ለመስጠት ለመጪው ረቡዕ መስከረም 27፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ረፋዱን በነበረው ችሎት፤ በዋስትናው ጉዳይ እና ተጠርጣሪዎች ባቀረቡት አቤቱታ ላይ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በጹሁፍ ያቀረበውን የመልስ መልስ ተቀብሏል። 

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሐሙስ መስከረም 21 ለፍርድ ቤቱ ያቀረበውና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ሶስት ገጽ ምላሽ፤ በተጠርጣሪዎች የቀረቡ አቤታቱዎችን የሚመለከት ነው። በዘጠኝ ተጠርጣሪዎች አማካኝነት ከቀረቡ አራት አቤቱታዎች ውስጥ አንዱ፤ በስር ፍርድ ቤት “በዋስትና የተለቀቅንበት ሂደት አግባብነት ያለው ነው” የሚል ነው። ተጠርጣሪዎቹ በዚሁ አቤቱታቸው ሂደቱ “ህጉን የተከተለ” መሆኑን ጠቅሰው፤ በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን ቢከታተሉ ፖሊስ እያካሄድኩ ነው በሚለው ምርመራ ላይ የሚያስከትለው እንከን እንደሌለ ጠቅሰዋል። 

ፖሊስ ለዚህ መከራከሪያ በሰጠው ምላሽ፤ የወላይታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና እንዲወጡ ያደረገው “የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግ አንቀጽ 63ን በሚቃረን መልኩ ነው” ብሏል። “የወንጀሉ ክብደት በራሱ ተጠርጣሪዎቹ ጉዳዩን በማረፊያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ግድ የሚል ሆኖ ሳለ፤ ዋስትናው አግባብ ነው የሚያስብል አይደለም” ሲል ፖሊስ በምላሹ ሞግቷል። ከዚህ ቀደም በነበሩት ችሎቶች የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች አለመቅረባቸውን የጠቀሰው ፖሊስ፤ በችሎት ተገኝተው የነበሩትም “እየጠፉ ነበር” ሲል በምላሹ ወንጅሏል። ይህም “ተጠርጣሪዎቹ አደገኛ መሆናቸውን ያሳያል የሚያስብል ነው” ሲል ተከራክሯል።        

ፖሊስ ሌላው ምላሽ የሰጠበት ጉዳይ “ችሎቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለውም” በሚል በተጠርጣሪዎች የቀረበውን አቤቱታ ነው። ተጠርጣሪዎቹ ፖሊስ ያቀረበው “ይግባኝ መታየት ያለበት በወላይታ ዞን በሚገኘው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንጂ በሀዋሳ ከተማ በሚሰየመው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አይደለም” በሚል አቤት ብለው ነበር። 

ፖሊስ ለዚህ በሰጠው ምላሽ “የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወላይታ ምድብ ችሎት ለተደራሽነት የተከፈተ ቢሆንም በደቡብ ክልል ውስጥ ማንኛውም ይግባኝ ጉዳዩችን የሀዋሳው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት ከማየት የሚከለክል ህግ የለም” ብሏል። “በወላይታ ዞን በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት በፍርድ ቤት ቀጠሮ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በሶዶ ከተማ ጎዳናዎች ላይ እየወጣ የዳኞችን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ከማስገባቱም በላይ አለመረጋጋትና ለሰው ህይወት አስጊ ሁኔታዎችን ፈጥሯል” ሲልም አብራርቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በአካባቢው ያላቸውን ከፍተኛ ተሰሚነት በተጨማሪነት የጠቀሰው ፖሊስ፤ ይህም በወላይታ በሚያስችሉ ችሎቶች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑንም አንስቷል። በዞኑ የሚገኘው ፍርድ ቤትም የጉዳዩን ክብደት እና ውስብስብነት ወደ ጎን በማድረግ ዋስትና መፍቀዱ፤ በአካባቢው ያሉ ተቋማት ተጽዕኖ ውስጥ መግባታቸውን ያሳያል ሲል ተከራክሯል። በእነዚህ ምክንያቶች ተጠርጣሪዎቹ በችሎት ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።  

“የተጠረጠርንበትን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምንም፤ ተሳትፏችንም በግልጽ ተለይቶ አልቀረበልንም” በሚል በተጠርጣሪዎች ለቀረበው አቤቱታ፤ ፖሊስ ገና በምርመራ ላይ መሆኑን በምላሹ አስፍሯል። “የምርመራ ውጤቱ ታይቶ ውሳኔ የሚሰጥበት እንጂ ለመቃወሚያነት የሚቀርብ” አይደለም ያለው ፖሊስ፤ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀ ያለውም ጉዳዩን በአግባቡ አጣርቶ፤ ተጠርጣሪዎችን በተገቢው መንገድ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ መሆኑን በምላሹ አትቷል።  

ተጠርጣሪዎቹ “ከሙስና አንጻር በስር ፍርድ ቤት የቀረበው የፖሊስ ይግባኝ አቤቱታ፤ በስር ፍርድ ቤት ያልቀረበና ክርክር ያልተደረገበት” መሆኑን በመጥቀስ ላቀረቡት አቤቱታም ፖሊስ ምላሽ ሰጥቷል። ፖሊስ “የተፈጸመው ወንጀል በሚጣራበት ወቅት የተገኙ ሌሎች ወንጀሎች ካሉ አብሮ ከመታየት የሚከለክላቸው የህግ አግባብ የለም” ብሏል። ፖሊስ በሃያዎቹ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ ሲያደርግ የቆየው “ህገመንግስታዊ ስርዓትን በሃይል በመናድ ወንጀል” ነው። 

በዛሬው ችሎት ማናቸውም ተጠርጣሪዎች በፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን የስድስቱ ጠበቃ ተመስገን ዋጃና ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ከተደረጉ 15 ተጠርጣሪዎች ውስጥ አስራ ሁለቱ በዛሬው ችሎት የተወከሉት፤ በሶስት ጠበቆች መሆኑንም ገልጸዋል። ቀሪዎቹ ሶስት ተጠርጣሪዎች በራሳቸው የሚከራከሩ እንደሆኑም አክለዋል።  

የደቡብክ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ በነበረው ችሎት በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት፤ ተጨማሪ ስምንት ተጠርጣሪዎች በሶዶ ማረሚያ ቤት በእስር እንዲቆዩ መደረጋቸው ይታወሳል። በማክሰኞው የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ወደ ሶዶ ከተማ ማረሚያ ቤት ከተወሰዱ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የቀድሞው የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እና የዞኑ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ዩሃንስ ይገኙበታል። ሁለቱ አመራሮች ከስልጣናቸው የተነሱት ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)