እንጦጦ ፓርክ በመጪው ቅዳሜ ሊመረቅ ነው

በበለጠ ሙሉጌታ 

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አነሳሽነት ግንባታው የተጀመረው የእንጦጦ ፓርክ የመዝናኛ ስፍራ፤ በመጪው ቅዳሜ መስከረም 30፣ 2013 በይፋ ሊመረቅ ነው። በምረቃው ዕለት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ የህክምና ባለሙያዎች የመታሰቢያ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ  ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የፓርኩ የምረቃ መርሃ ግብር ቅዳሜ ከማለዳው ጀምሮ እስከ ማምሻው ድረስ እንደሚከናወን ምንጮች ገልጸዋል። ዛሬ በስፍራው የተገኘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ፓርኩ በጊዜያዊነት ለጎብኚዎች ዝግ ተደርጎ ለቅዳሜው የምረቃ ስነ ስርዓት ዝግጅቶች እየተካሄዱ መሆኑን ተመልክቷል።

በስነ ስርዓቱ ላይ በርካታ ባለስልጣናት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያሉ አንድ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ አስረድተዋል። ከአገር ውስጥ ባለስልጣናት ውጪ ከውጭ አገር የሚመጣ ተጋባዥ እንግዳ አለመኖሩንም አመልክተዋል።  

በምረቃው መርሃ ግብር ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ከሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች በተጨማሪ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ እኚሁ ምንጭ አስረድተዋል። በዕለቱም ከ200 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ቅርሶችን የያዘ አንድ የ“አርት ጋለሪ” ያሰባሰባቸው ታሪካዊ ቅርሶች ለዕይታ ይቀርባሉ ብለዋል።  

ከእሁድ ጥቅምት 1 ጀምሮ ለህዝብ ክፍት ሆኖ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመር የተነገረለት የእንጦጦ ፓርክ፤ በአምስት የተለያዩ ሳይቶች ላይ በርካታ መዝናኛዎች የተገነቡበት ነው። ፓርኩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቅርብ ክትትል የሚደረግበት “ሸገርን ማስዋብ” የተሰኘው ፕሮጀክት አካል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ፕሮጀክት ገንዘብ ማሰባሰቢያ የሚውል በነፍስ ወከፍ አምስት ሚሊዮን ብር የተከፈለበት የእራት መርሃ ግብር በግንቦት 2011 ማካሄዳቸው ይታወሳል።  

ሃያ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ ቅድሚያ ግምት የተሰጠው “ሸገርን ማስዋብ” ፕሮጀክት ከእንጦጦ እስከ አቃቂ ያሉ አረንጓዴ አካባቢዎችን እና የወንዝ ዳርቻዎችን ለማልማት ያለመ ነው። በሶስት ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው የዚህ ፕሮጀክት ሌላ አካል የሆነው “ሸገር ፓርክ” ጳጉሜ 5፤ 2012 መመረቁ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)