የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የቀብር ስነስርዓት ተፈጸመ

15

በአለምፀሀይ የኔዓለም

ባለፈው ሳምንት ህይወታቸው ያለፈው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የቀብር ስነ ስርዓታቸው ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 26፤ 2013 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል። አንጋፋው ምሁር ለበርካታ ዓመታት ባስተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ወዳጅ፤ ዘመዶቻቸው በተገኙበት የሽኝት ስነ ስርዓትም ተካሄዶላቸዋል። 

በዩኒቨርስቲው ልደት አዳራሽ በተካሄደው የሽኝት ስነ ስርዓት ላይ 500 ገደማ የሚሆኑ እድምተኞች እንዲገኙ ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን በስፍራው ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸውን ጨምሮ በርካታ ሰው ተገኝቷል። የአንጋፋው ምሁር ልጅ ዶ/ር መቅደስ መስፍን፣ የቅርብ ጓደኛቸው አርቲስት ደበበ እሸቱ እንዲሁም የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመርሃ ግብሩ ላይ በቅድሚያ ንግግር አድርገዋል። 

በሽኝት ስነ ስርዓቱ ላይ የቀብር አስተባባሪ ኮሚቴው “የፕሮፌሰር መስፍን ቅርስና ሰነዶችን ለመጠበቅም ምን ታስቧል?” በሚል የውይይት መነሻ ሀሳብ አንስቶ ውይይት ተደርጎበታል። ለብዙ ዓመታት ባስተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንድ ማዕከል እንዲሰየም፣ ተወልደው ባደጉበት በሽሮሜዳ አካባቢ አደባባይ እንዲሰየምላቸው እንዲሁም የእሳቸው ስራ ለትውልድ እንዲሻገር “መንግስት ማዕከል ቢያቋቁም” የሚሉ ነጥቦች ተነስተዋል። 

የሽኝት ስነ ስርዓቱ እንደተጠናቀቀ በመርሃ ግብሩ የታደሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ጨምሮ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፤ የፕሮፌሰሩን አስክሬን የያዘውን ተሽከርካሪ አጅበው ስድስት ኪሎ ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ መግቢያ እስከ ስላሴ ቤተክርስቲያን በእግር ተጉዘዋል። የፖሊስ ማርሽ ባንድም የተለያዩ የሀዘን ዜማዎችን በማሰማት የሽኝት ስነ ስርዓቱን መርቷል። 

በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን በነበረው ስነ ስርዓት፤ የ90 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የነበሩት የፕሮፌሰር መስፍን የህይወት ታሪክ በደራሲ አያልነህ ሙላት በንባብ ቀርቧል። የሃይማኖት አባቶችም ለፕሮፌሰሩ ጸሎተ ፍትሃት አድርገዋል። 

በዚሁ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ከተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በተጨማሪ የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሂሩት ካሳው፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዲሁም የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተገኝተዋል። የሃይማኖት አባቶች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ የሙያ ባልደረቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና ሌሎች በርካታ ታዳሚዎችም በቀብር ስነ ስርዓቱ በመገኘት ዕውቁን የአደባባይ ምሁር እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተሰናብተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)