በተስፋለም ወልደየስ
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አምስት አባላት አንዱ የሆኑት ዶ/ር ጌታሁን ካሳ ያቀረቡት የመልቀቂያ ጥያቄ በተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ተቀባይነት አገኘ። የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ጥያቄውን መቀበላቸውን ያስታወቁት ትላንት መስከረም 26፤ 2013 በጻፉት ደብዳቤ ነው።
አፈ ጉባኤው በደብዳቤያቸው ዶ/ር ጌታሁን ከምርጫ ቦርድ አባልነታቸው በፈቃዳቸው ለመልቀቅ መስከረም 18 ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰው፤ በራሳቸው ውሳኔ መሰረትም ከኃላፊነታቸው የተነሱ መሆኑን አስታውቀዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የአፈ ጉባኤው ደብዳቤ ለዶ/ር ጌታሁን የተላከ ሲሆን በግልባጭም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ለተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤቶች እንዲደርስ ተደርጓል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትም ጉዳዩን “እንዲያውቁት” መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተደንግጓል። ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡለትን የቦርዱ ስራ አመራር አባላትን የመሾም ስልጣንም በሕገ መንግስቱ ጭምር ተሰጥቶታል። በ2011 የተሻሻለው የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ የስራ አመራር ቦርድ አባላትን ቁጥር ከዘጠኝ ወደ አምስት የቀነሰ ሲሆን የስራ ሁኔታቸውንም ለውጧል። በአዲሱ አዋጅ መሰረት የስራ አመራር ቦርድ አባላቱ እንደ ቀድሞው በትርፍ ጊዜ የቦርድ አባልነት ሳይሆን በሙሉ ጊዜ የሚያገለግሉ እንዲሆን ተደርጓል።
አሁን በስራ ላይ ያሉት የቦርድ አባላት በተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው የጸደቀላቸው በሰኔ 2011 ነበር። አምስቱ አባላት የተመረጡት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዋጁ መሰረት ያቋቋሙት ገለልተኛ ኮሚቴ ካደረገው ከፍተኛ ጠንክር ካለ የማጣራት ሂደት በኋላ እንደነበር በወቅቱ ተነግሯል። ኮሚቴው ከቀረቡለት 200 ዕጩዎች መካከል ስምንቱን መርጦ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረበ ሲሆን እርሳቸውም አራቱን መርጠው ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።
ከአራቱ ተመራጮች አንዱ የነበሩት ዶ/ር ጌታሁን ሹመቱን በተቀበሉበት ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር ነበሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ስር በተቋቋመው የሕግ እና የፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤም በአባልነት ሰርተዋል። ቀደም ባሉ ዓመታት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በዋና ዳይሬክተርነት እንደዚሁም በትግራይ ክልል አቃቤ ህግ ሆነው አገልግለዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ተቋሞች በአማካሪነት የሰሩት የህግ መምህሩ ለኤምባሲዎች፣ መንግስታዊ ላልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የመንግስት ተቋማትም ተመሳሳይ አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን የስራ ታሪካቸው ያስረዳል። በህግ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ዶ/ር ጌታሁን፤ ሰሜን አይርላንድ ቤልፋስት ከሚገኘው ኩዊንስ ዩኒቨርስቲ በህግ እና የሰብዓዊ መብት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።
የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ የስራ አመራር ቦርድ አባላት የስራ ዘመን ስድስት ዓመት መሆኑን ቢደነግግም ዶ/ር ጌታሁን ግን ከስራ መልቀቃቸውን ያሳወቁት አንድ ዓመት ገደማ ከሰሩ በኋላ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መስከረም 18፤ 2013 በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ፤ የቦርድ አባሉ “በገዛ ፍቃዳቸው ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለተወካዮች ምክር ቤት ማስገባታቸውን” አስታውቆ ነበር። ቦርዱም ሆነ ዶ/ር ጌታሁን ከስራ መልቀቂያው ጀርባ ያለውን ምክንያት ከማብራራት ተቆጥበዋል።
አንድ የስራ አመራር ቦርድ አባል ከኃላፊነቱ የሚነሳው በራሱ ፍቃድ ስራውን ከለቀቀ አሊያም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተሰናበተ እንደሆነ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ያስቀምጣል። ምክር ቤቱ አንድን የቦርድ አባል ሊያሰናበት የሚችለው በህመም ምክንያት ተግባሩን በተገቢው ሁኔታ ማከናወን የማይችል ከሆነ፣ ግልጽ የሆነ የስራ ችሎታ ወይም ብቃት ማነስ ከታየበት፣ ከባድ የስነ ምግባር ጉድለት ካለበት አሊያም ለተከታታይ ስድስት ወራት በስራ ገበታ ላይ ካልተገኘ እንደሆነ በአዋጁ ተብራርቷል።
አንድ የቦርድ አባል ከቦርድ ኃላፊነቱ በፈቃዱ ከለቀቀ ወይም ጊዜውን ጨርሶ ከተሰናበተ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በማንኛውም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ሊሾም እንደማይችልም የቦርዱ ማቋቋሚያ አዋጅ ያመለክታል። ሆኖም አዋጁ፤ በፈቃዱ በለቀቀ አባል እንዴት ተተኪ ሊመረጥ እንደሚችል በግልጽ ያስቀመጠው ድንጋጌ የለም።
የአንድ አባል መልቀቅ የስራ አመራር ቦርዱ ውሳኔ ለማሳለፍ በሚያካሂዳቸው ስብሰባዎች ላይ ጉልህ ተጽዕኖ እንደማያሳድር የሚጠቁም አንቀጽ ግን በአዋጁ ተካትቷል። አዋጁ “ከስራ አመራር ቦርዱ አባላት ሶስቱ ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል” ሲል ደንግጓል። ከተሰናባቹ ዶ/ር ጌታሁን ውጪ አሁን በስራ ላይ ያሉት የስራ አመራር ቦርድ አባላት፤ የቦርድ ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ምክትላቸው ውብሸት አየለ፣ ብዙወርቅ ከተተ እና ዶ/ር አበራ ደገፋ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)