በበለጠ ሙሉጌታ
የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን “ሐሰተኛ የዋጋ ቅናሽ ማስታወቂያዎችን በመደብሮቻቸው ላይ ለጥፈዋል” ላላቸው 14 የንግድ ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ ሰጠ። ባለስልጣኑ ማስጠንቀቂያውን ያስተላለፈው በአዲስ አበባ ከተማ በስቴዲዮም፣ ለገሀር፣ ቸርችል ጎዳና እና ፒያሳ አካባቢ ለሚገኙ ድርጅቶች ነው።
የባለስልጣኑ አቤቱታ ምርመራና ክስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌትነት አሸናፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት የንግድ ድርጅቶቹ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት እርሳቸው በሚመሩት ክፍል ስር ባሉ ባለሙያዎች በተደረገ ቅኝት ነው። በቅኝቱ “ጉድለት ተገኝቶባቸዋል” የተባሉት ድርጅቶች፤ የሴቶችና የወንዶች ጫማዎችን፣ የቆዳ ውጤቶችን፣ የእንጨት ስራዎችን፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እና የልብስ ማጠቢያ ማሽኖችን በመሸጥ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አብዛኛዎቹ የቅናሽ ማስታወቂያዎች ካለፈው ጳጉሜ ወር ጀምሮ እስከ መስከረም 30፤ 2013 ዓ.ም. የሚቆዩ መሆኑን የሚያመለክቱ እንደሆኑ የጠቆሙት አቶ ጌትነት ሆኖም የሚያስተዋውቁት ቅናሽ ምን ያህል እንደሆነ እና ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ያልገለጹ ድርጅቶች እንደነበሩም አስረድተዋል።
ከድርጅቶቹ መካከል የተወሰኑቱ “ታላቅ የበዓል ቅናሽ” የሚሉ የወረቀት እና የባነር ማስታወቂያዎች ለጥፈው ነገር ግን በማስታወቂያው መሰረት ሽያጭ አለመፈፀሙን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የዕቃዎቹን የቀደመ ዋጋ ያለመጻፍ ችግር የታየባቸው እንዳሉ ሁሉ የትኛው ምርት ላይ ቅናሽ እንደተደረገ በግልጽ ያላስቀመጡ እንደነበሩም አመልክተዋል።
የባለስልጣኑ ባለሙያዎች ባደረጓቸው ድንገተኛ ፍተሻዎች፤ ድርጅቶቹ በግልፅ የሚታይ የዋጋ ታግ በዕቃዎቹ ላይ አለመለጠፋቸው ወይም አለማንጠልጠላቸው ታይቷል ተብሏል። በውጪ ቅናሽ እንዳለ የሚያስተዋውቁ የንግድ መደብሮች ወደ ውስጥ ተገብቶ ማጣራት ሲደረግ በቅናሽ እንደማይሸጡ እንደተደረሰባቸው ባለስልጣኑ አስታውቋል። የአንዳንዶቹ መደብሮች ደረሰኞች ከቅናሽ በፊት የነበረ ዋጋ እና በቅናሽ የተሸጠበትን ዋጋ በግልጽ የማሳዩ መሆን በችግርነት ከተሱት መካከል ይጠቀሳል።
በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ መሰረት “ሸማቹ ማግኘት ያለበት መረጃ ሙሉ እና የማያደናግር እና በግልፅ እና በእውነተኛ ነገር ላይ የተደገፈ መሆን አለበት” ያሉት አቶ ጌትነት፤ የንግዱ ማህበረሰብ በዓላትን ምክንያት በማድረግ አላግባብ ሸማቹ ላይ ዋጋ ከመጨመርና “ታላቅ ቅናሽ” የሚል ሐሰተኛ ማስታወቂያ ከመለጠፍ እንዲቆጠብ አሳስበዋል። በቀጣይ በተለይም በበዓላት ወቅት በሚሰሩ የንግድ ተቋማት፣ መሰል የማጭበርበር ስራዎች እንዳይኖሩ ክትትል እንደሚደረግ እና አዋጁ በሚያዘው መሰረት ወደ ቅጣት እንደሚገባም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)