ኢዴፓ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥረት በነገሰበት “ምርጫ በፍፁም መታሰብ የለበትም” አለ

በተስፋለም ወልደየስ 

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ኢትዮጵያ በፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት “አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በፍፁም መታሰብ የለበትም” አለ። ፓርቲው ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በሀገሪቱ ላሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች መፍትሄ ማመንጨት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የውይይትና የድርድር ሂደት (National Dialogue) በአስቸኳይ እንዲጀመርም ጠይቋል።

ኢዴፓ ይህን አቋሙን ይፋ ያደረገው፤ የፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 3፤ 2013 ባወጣው መግለጫ ነው። ፓርቲው “የምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል” በሚል ርዕስ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ከውድቀት ለመዳን “ዛሬም ዕድል አላት” ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።   

ይህ ዕድል እውን ሊሆን የሚችለው “በአንድ ገዥ ፓርቲ የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት አይደለም” የሚለው ኢዴፓ፤ “ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ የይስሙላ ምርጫ” ሀገሪቱ ላለችበት “ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት እና ቀውስ” መፍትሄ እንደማይሆን ጠቁሟል። ሀገሪቱ ከተደቀነባት “አሳሳቢ የህልውና አደጋ” ወጥታ ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመሸጋገር አራት ተጨባጭ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባም አሳስቧል።

ፓርቲው በቀዳሚነት እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል ብሎ በመግለጫው የጠቀሰው፤ በኢትዮጵያ “እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ እየከፋ መጥቷል” ባለው “የህግ የበላይነት መጥፋት” ጉዳይ ላይ ነው። ኢዴፓ ለዚህ በምሳሌነት ያነሳው የፓርቲው መስራች እና የብሔራዊ ምክር ቤት አባል በሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው እና ሌሎች የፖለቲካ ሰዎች ላይ የተከሰቱትን የህግ ጥሰቶች ነው። 

አቶ ልደቱ እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች “በፈጠራ ክስ ያለአግባብ የሚንገላቱበት” ሁኔታ መፈጠሩን የሚያትተው የኢዴፓ መግለጫ፤ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ እና ትዕዛዝ የማይከበርበት አካሄድ መታየቱንም አመልክቷል። “ያለ ፍርድ ቤት ነፃነት በአንድ አገር ላይ የህግ የበላይነት ሊከበር ስለማይችል ፍርድ ቤቶችን ለፖለቲካ ጉዳይ ለመጠቀምና፤ የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመጣስ እየተፈፀመ ያለው ህገ-ወጥ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም አለበት” ሲልም ፓርቲው አሳስቧል።

ፓርቲው የታሰሩ የፖለቲካ አመራሮችን ጉዳይን በሁለተኛነት እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል ባለው ነጥብ ላይም በድጋሚ አንስቷል። ኢዴፓን ጨምሮ የኦፌኮ፣ የኦነግ እና የባልደራስ ከፍተኛ አመራሮች በእስር ላይ እንደሚገኙ የጠቀሰው መግለጫው፤ ከእነርሱ በተጨማሪ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታውሷል። የዜጎች እስር በተለይ በኦሮሚያ ክልል ጎልቶ እንደሚታይም አመልክቷል።  

በዚህ ምክንያት በሀገሪቱ “አሳሳቢ የፖለቲካ ውጥረት መንገሱን” ፓርቲው ጠቁሟል። ውጥረቱ “ወደ ሌላ አሳሳቢ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ሁሉም ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ” እንዲፈቱ ጥያቄ አቅርቧል። 

የምርጫን ጉዳይ በሶስተኛነት የተመለከተው ፓርቲው፤ “አገራችን በዚህ አይነት የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ሆና በፍፁም አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ መታሰብ የለበትም” ሲል ጠንከር ያለ አቋሙን ይፋ አድርጓል። ኢዴፓ “ከምርጫ አስቀድሞ መካሄድ ይኖርበታል” ባለው ሁሉን አቀፍ የውይይትና የድርድር ሂደት ላይ “መነሳት ይገባቸዋል” ያላቸውን ጥያቄዎችንም ሰንዝሯል። 

ፓርቲው “መሰረታዊ” ሲል ከመደባቸው ጥያቄዎች ውስጥ “ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ምን ዓይነት ውይይት እና ድርድር ይካሄድ?” የሚለው ይገኝበታል። ሀገሪቱ “ከአሁን ጀምሮ እስከሚቀጥለው አገራዊ ምርጫ ድረስ አገሪቱ እንዴት ትተዳደር?” የሚለውም ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባም በመግለጫው አንስቷል።  

ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በደቡብ ክልል ያለውን የፖለቲካ ውጥረት ማርገብ እና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በሀገሪቱ መደረግ የሚገባቸው ጉዳዮች ሌሎቹ በፓርቲው በመሰረታዊነት የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው። አገሪቱ ያለ “ቋሚ መንግስት” ልትቆይ እንደምትችል በመግለጫው ፍንጭ የሰጠው ኢዴፓ፤ እስከዚያ ድረስ “የኢኮኖሚ ደህንነቷን ለማስጠበቅ መወሰድ ይገባዋል” ያለውን እርምጃ ከመሰረታዊ ጥያቄዎች መድቦታል። 

“በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል እየታየ ያለው ተገቢ ያልሆነና አሳሳቢ ፍጥጫ በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ ጉዳዩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በውይይትና በድርድር መፈታት አለበት”

– የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)

ፓርቲው ባነሳቸው እና በሌሎችም መሰረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መፍትሄ ማመንጨት የሚያስችል “ሁሉን አቀፍ የውይይት እና የድርድር ሂደት” በአስቸኳይ እንዲጀመር በመግለጫው ጠይቋል። የውይይት እና ድርድር እርምጃው ፓርቲው በአራተኛነት ላነሳው ጉዳይም ተግባራዊ እንዲደርግ አሳስቧል። 

በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል “ተገቢ ያልሆነ እና አሳሳቢ ፍጥጫ” እየታየ መሆኑን የጠቀሰው ፓርቲው፤ ይህ አካሄድ “በአስቸኳይ መቆም አለበት” ብሏል። ጉዳዩ “ከአገሪቱ ሰላምና አንድነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ እንደምታ ያለው ነው” ያለው ኢዴፓ፤ መፍትሄው “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” የሚካሄድ “ውይይትና ድርድር” እንደሆነ አመልክቷል።  

ፓርቲው ያነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች “በአግባቡ መመለስ ሳይችሉ ከቀሩ እና በአገሪቱ ላይ የሚታየው ውጥረት የበለጠ የሚባባስ ከሆነ”፤ ለሚደርሰው ማንኛውም ጉዳት ተጠያቂው ገዢው “ብልፅግና ፓርቲ” መሆኑንም ኢዴፓ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)