ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያን የጎበኙ ሁለት የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኮሮና ስጋት ራሳቸውን አገለሉ

ባለፈው ሳምንት ከፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጋር የተገናኙ ሁለት የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኮሮና ስጋት ራሳቸውን አገለሉ። ሁለቱ ባለስልጣናት ራሳቸውን ያገለሉት አብረዋቸው ወደ ኢትዮጵያ ከተጓዙ የልዑካን ቡድን አባላት መካከል አንዱ በኮሮና መያዛቸው በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ ነው። 

ከትናንት ጀምሮ ራሳቸውን ማግለላቸውን የገለጹት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ እና የጸጥታ ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል እና የህብረቱ የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች ናቸው። ሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የኮቪድ 19ን ለመዋጋት የሚያገለግሉ 7.5 ቶን የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፎችን ይዘው ነበር።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ መስከረም 28፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጋር የተገናኙት ባለስልጣናቱ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በነበራቸው ቆይታ “በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዩች” ላይ መነጋገራቸው ተገልጾ ነበር። ሁለቱ ባለስልጣናት በማግስቱ ከፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።   

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ባለስልጣናቱ ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን በጊዜያዊነት የሚያርፉበትን የተባበሩት መንግሥታት መጠለያን እና በሶማሌ ክልል የሚገኘውን የቆሎጂ የስደተኞች መጠለያን ጭምር ጎብኝተው ነበር። በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አድርገው የታዩት ሁለቱ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ቀናት በኋላ በኮሮና ቫይረስ ስጋት ራሳቸውን ማግለላቸውን በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንትን በጣምራ ሃላፊነት የያዙት ቦሬል፤ ባለፈው እሁድ ከአዲስ አበባ ሲመለሱ ባደረጉት የኮሮና ምርመራ “ነጻ” እንደነበሩ ገልጸዋል። ሆኖም ትላንት የሰሙት ዜና ራሳቸውን አግልለው እንዲቀመጡ ምክንያት ሆናቸዋል። 

“ከእኔ እና ያኔዝ ሌናርቺች ጋር ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ ከተጓዘው ልዑክ መካከል፤ አንድ ሰው በምርመራ በኮሮና መያዙ እንደተረጋገጠ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ተነግሮኛል። በሕጉ መሠረት ራሴን ለይቼያለሁ። ሁለተኛውን የምርመራ ውጤት እጠብቃለሁ” ሲሉ ትላንት ምሽቱን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል። 

የአውሮፓ ህብረትን የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስተባብሩት ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች በበኩላቸው፤ አንድ የሥራ ባልደረባቸው በኮሮና መያዙን ቢያረጋግጡም ወደ አዲስ አበባ የተጓዘው ልዑክ አባል እንዳልሆነ ግን ገልጸዋል። ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘው የእርሳቸው ቡድን አባላት፤ ከጉዞው በፊት እና ወደ ብራስልስ ከተመለሱ በኋላ ባደረጉት ምርመራ ውጤታቸው “ነጻ” እንደነበርም አመልክተዋል።

“ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘው ልዑክ አባል ያልሆነ የእኔ ቡድን አባል በተደረገለት ምርመራ በኮሮና መያዙ መረጋገጡ ዛሬ ተነግሮኛል። በማህበረሰብ ጤና መመሪያ መሠረት ራሴን ለይቼ ከመኖሪያ ቤቴ ስራዬን እያከናወንኩ ሁለተኛውን ውጤት እጠባበቃለሁ” ሲሉ ሌናርቺች ጽፈዋል። “ምንም አይነት የበሽታ ምልክት” አለማሳያታቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ “ጤንነታቸውም ጥሩ” እንደሆነ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)