በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተከሰቱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በዋናነት ከህዳሴ ግድብ ጋር የሚያያዙ ናቸው- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፌደራል መንግስቱ ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጋር የገባው ውዝግብ “በህግ እና በህግ” ብቻ መልስ እንደሚያገኝ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ መንግሥታቸው ከትግራይ ክልል ስራ አስፈጻሚ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲቋረጥ ባስተላለፈው ውሳኔ እንደሚገፋበት ዛሬ በሰጡት ማብራሪያ አረጋግጠዋል።

“የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚወስነው ውሳኔ፣ [የተወካዮች] ምክር ቤት የሚወስነው ውሳኔ፣ የአስፈጻሚው አካል ይህንን ብቻ የሚያስፈጽም ይሆናል። እዚያ ካለው ሃይል ጋር የሚያያዘው ጉዳይ ግን በህግ እና በህግ ብቻ የሚመለስ ይሆናል” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። 

አብይ “የትግራይ ህዝብ ሀገር ወዳድ ህዝብ ነው። የትግራይ ህዝብ መለወጥ ይፈልጋል። ይሄን ታሳቢ ያደረገ ስራ የፌደራል መንግስት እየሰራ ያለው ህዝብ አለኝ ብሎ ነው። አስር፣ አስራ አምስት፣ ሃያ የማያስፈልጉ ግለሰቦች አሉ ሳይሆን ‘በሚሊዮን የሚቆጠር፤ አስፈላጊ፣ ባለመብት፣ የምንታገልለት ዜጋ አለን’ ብለን ነው እየሰራን ያለነው። ወደፊትም ይሄው ይቀጥላል” ሲሉ ተናግረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የምክር ቤት ውሎ የመንግሥታቸውን የአወቃቀር ስርዓት፣ አገሪቱ የገጠሟትን የጸጥታ ቀውሶች፣ የፍትህ ሥርዓቱ የገጠሙትን ችግሮች ጨምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የጸጥታ ተቋማት ፈተና እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ግጭት 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እርሳቸውን ወደ ሥልጣን ካመጣው እና ኢሕአዴግ ፈርሶ በብልጽግና ከተተካበት “ለውጥ” በኋላ ያለውን ጊዜ የአገሪቱ የጸጥታ አስከባሪ ተቋማት “በብዙ የተናጡበት” ሲሉ ገልጸውታል። የጸጥታ አስከባሪ ተቋማቱ “ቁመና ተዳክሞ፣ ሉዓላዊነታችን አደጋ ውስጥ ገብቶ አገር እንዳትፈርስ የሚል ፍራቻ ነበር” ያሉት አብይ “አዲስ ኃይል ማሰልጠን፣ አዲስ ትጥቅ ማስገባት፣ አደረጃጀት ማስተካከል፣ የአመራር ሽግሽግ ማድረግ እና በስልጠና እና በሁኔታ ትንተና አቅም የማስፋት” ስራዎች እንደተከናወኑ አስረድተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሁለት አመታት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተከሰቱ ተደጋጋሚ ግጭቶች በደቡብ ሱዳን ከሚገኘው ብሉ ናይል ግዛት ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንደሚገናኝ ተናግረዋል። “ትንሽ ወሰብሰብ ያለ ነገር ነው። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉዳይ፣ የአማራ ክልል ጉዳይ ወይም የኦሮሚያ ክልል ጉዳይ አይደለም” ያሉት አብይ “በብሉ ናይል [ግዛት] በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሰለጥናሉ፤ ዘመናዊ መሣሪያ ይታጠቃሉ፤ ቤኒሻንጉል መላ ድንበሩን ተዉና፤ ከወረዳ ወረዳ የሚያገናኝ መንገድ በስፋት የሌለበት ክልል ነው። በዚያ አድርገው በመግባት ከጉዳዩ ጋር ትስስር የሌላቸውን ዜጎች ህይወት አደጋ ውስጥ ከትተዋል” ብለዋል። 

“በተደጋጋሚ እርምጃ ተወስዶ ሲረግብ፤ ወደዚያ ወጥተው፤ ሰላም ነው ሲባል ሲረግብ የመምጣት” ኩነት መታየቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፤ በሚዲያ ድጋፍ እንደሚደረግ እና “ግጭቶቹን የብሔር የማስመሰል ፍላጎት አለ” ሲሉ ከስሰዋል። “ብዙ ተዋናይ በውስጡ ያለው ቢሆንም ትልቁ ድርሻ ከህዳሴ [ግድብ] ጋር ይያያዛል። በዚያ በኩል ያለውን የህዳሴን መንገድ መቁረጥ እና ማስቀረት ጋር ይያያዛል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።  

በአካባቢው ባለው ውስን መሠረተ ልማት እና ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ምክንያት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጭምር “የሕይወት ዋጋ” መክፈላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ጠቁመዋል። ግጭቶቹን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መማረካቸውን፣ ብዙዎች መሸሻቸውን የተናገሩት አብይ “ምንጩ ካልደረቀ፤ እየዋለ እያደረ እየመጣ ዜጎች ላይ ጥቃት ማድረሱ አይቀርም” በማለት ሙሉ በሙሉ መፍትሔ ካልተበጀለት ጥቃቱ ቀጣይ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የፍትህ ስርዓቱ ፈተና

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ቆይታቸው፤ ከሰኔ 2010 እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር፣ በሐዋሳ፣ በጅግጅጋ እና በአሶሳ በተፈጸሙ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድያዎችና የግድያ ሙከራ፤ ግጭቶች እና ኹከቶችን የሚመረምሩ ሰባት ዋና ዋና የክስ ሒደቶች ያሉበትን ደረጃ አለፍ አለፍ ብለው ዘርዝረዋል። በእነዚህ ክሶች የዳኞች እጥረት እና የኮሮና ወረርሽኝ ፈተና ጋርጠው እንደነበር ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የፍትህ ስርዓቱ ገለልተኛ ይሁን፣ ነጻ ይሁን ያለው [የለውጥ] ሃይል፣ የፍትህ ስርዓት ነጻነትን የሚቃረን መሆን የለበትም። አሁንም ያልተፈቱ ድክመቶች አሉ” ብለዋል።  

“ፍርድ ቤት ለሚሰጣቸው ፍርዶች፣ ብያኔዎች፤ ምንም ሳናወላዳ መቀበል ያስፈልጋል። እኛ ያላከበርነውን ፍርድ ቤት፣ እኛ ያልታዘዝንለትን ፍርድ ቤት ነጻ እና ገለልተኛ ሁን ማለት ከንቱ ነገር ነው የሚሆነው” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም ለፓርለማ አባላት አንጸባርቀዋል።   

“የፍትህ ስርዓቱ የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች አስፈጻሚ አካላት ማክበር ይጠበቅበናል። ከዚህ አንጻር ተጨማሪ ስራ ያስፈልጋል። አንዳንዱ ወንጀለኛ ይደብቃል። አንዳንዱ ሲታዘዝ አይፈጽምም። ይሄ ትክክል አይደለም። የራሳችንን ግብ፤ የእኛን ፍላጎት ነው የሚቃረነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥታቸው ውስጥ አለ ያሉትን እንከን ዘርዝረዋል። 

“የፍትህ ስርዓቱ የተሟላ እንዲሆን፤ የምናስበውን ነገር እንዲያሳካ መታለፍ ያለባቸው፣ አስፈጻሚው በጣም በጥንቃቄ ማየት የሚገባው ነገሮች አሉ። እኛ የመንግስት ቢሮ ስንይዝ እና ስንወጣ፤ የግል ስም፣ የግል ክብር፣ የግል ማንነት የሚባል ነገር መተው አለብን። ሰዎች መናገር፣ መጻፍ፣ መተቸት እንዲችሉ መፍቀድ አለብን። የማንፈቅደው ነገር ሰዎች ባላቸው ብዕር፣ ባላቸው ሚዲያ ‘ተነስ፣ ግደል፣ ተጋደል’ ማለት የለባቸውም እንጂ እኛን መተቸት እና ስለ እኛ መጻፍ መፍቀድ አለብን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። 

“በእርግጥ አንዳንድ የሚጻፈው ነገር ስህተት ሊሆን ይችላል። መረጃ የሌለው ሊሆን ይችላል። በህግ ዓይን የሚያስጠይቅ ሊሆን ይችላል። ሆደ ሰፊ ሆነን የጀመርነውን የዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን የመፍጠር ጉዳይ እያረጋገጥን ካልሄድን መልሰን የእኛኑ ትግል፣ ግብ መልሰን ነው የምንበላው” ሲሉ የራሳቸውን የመንግሥት መዋቅር ሞግተዋል።        

“በእርግጥ አንዳንድ የሚጻፈው ነገር ስህተት ሊሆን ይችላል። መረጃ የሌለው ሊሆን ይችላል። በህግ ዓይን የሚያስጠይቅ ሊሆን ይችላል። ሆደ ሰፊ ሆነን የጀመርነውን የዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን የመፍጠር ጉዳይ እያረጋገጥን ካልሄድን መልሰን የእኛኑ ትግል፣ ግብ መልሰን ነው የምንበላው።”

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የመናገር ነጻነት መከበር እንዳለበት ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከተናገሩት

የኮሮና ወረርሽኝ፣ የአንበጣ ወረርሽኝ እና ጎርፍ 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፤ ሀገሪቱ ከገጠሟት ሰው ሰራሽ እና በየቦታው ከተከሰቱ ችግሮች በተጨማሪ የኮሮና እና የአንበጣ ወረርሽኞች እንደዚሁም የጎርፍ አደጋ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓም ድረስ 89,860 ሰዎች የያዘው እና 1,365 ሰዎች ለሞት የዳረገውን የኮሮና ወረርሽኝ በመከላከል ረገድ፤ “በጣም የተዋጣለት መንገድ ተከትለናል” ሲሉ በበሽታው ላይ መንግስታቸው አሳክቷል ያሉትን የስራ አፈጻጸም አድንቀዋል። 

አብይ እንዳሉት በወረርሽኙ ሕይወታቸውን ካጡ 90 በመቶ ገደማው በኮሮና መያዛቸው የተረጋገጠው በአስከሬን ላይ በተደረገ ምርመራ ነው። ኢትዮጵያ በየዕለቱ በኮሮና የተያዙ ሰዎችን ለመለየት የምታደርገው ምርመራ ቁጥር መጨመሩን፤ “የቴስት ኪት” ማምረት መጀመሯን እንደ ስኬት ጠቅሰዋል።

ይሁንና ወረርሽኙ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን መፈታተኑን፤ የንግድ ባንክ የዋና መሥሪያ ቤት ግንባታን ማስተጓጎሉን አልሸሸጉም። “የንግድ ባንክ ህንጻን ከሚገነቡ ሰዎች መካከል ከ50 በላይ ሰዎች በኮሮና በመያዛቸው፤ ቁልፍ ቁልፍ ስራ የሚሰሩ የቻይና ባለሙያተኞች ስለፈሩ አንሰራም ብለው ወደ ሀገራቸው ሄደዋል። እስካለፈው ወር ድረስ ከፍተኛ ፍጥነት የነበረው የንግድ ባንክ ህንጻ ግንባታ በዚህ ሁለት ሶስት ሳምንት ቀንሷል” ብለዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“የጤና ሚኒስቴር ያወጣውን መመሪያ በትክክል ተከትሎ መተግበር አስፈላጊ ነው” ያሉት አብይ “ገፍቶ ስላልመጣ እንጂ ገፍቶ ቢመጣ በጣም ብዙ ነገር ሊያናጋ ይችላል” በማለት ቸል ማለት እንደማይገባ አስጠንቅቀዋል። 

የ30 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትምህርት በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ተቋርጦ እንደነበር አስታውሰው “ክረምቱን በበጎ ፈቃድ ከ60 ሺህ በላይ የመማሪያ ክፍሎች መሰራታቸውን” እና የትምህርት ሚኒስቴር ከ52 ሚሊዮን በላይ “የሚታጠቡ” የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛዎች በማከፋፈል አገልግሎቱን በጥንቃቄ መልሶ ለመጀመር መንግስታቸው ያከናወነውን ስራ ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል።  

ከኮሮና ሌላ በምክር ቤት አባላት ጥያቄ ያስነሳው ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰራጨው የአንበጣ መንጋ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በሶማሌ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በ94 ወረዳዎች በ705 ቀበሌዎች የአንበጣ ወረርሽኝ ማጋጠሙን ገልጸዋል። 

“በእነዚህ አካባቢዎች በድምሩ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ታርሷል የሚል መረጃ ያለን ሲሆን ከዚህ ውስጥ ጥቃት የደረሰበት 420 ሺህ ሄክታር መሬት ገደማ ነው።”

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የአንበጣ ወረርሽኝን በተመለከተ ለፓርላማ አባላት ከተናገሩት

“በእነዚህ አካባቢዎች በድምሩ አራት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ታርሷል የሚል መረጃ ያለን ሲሆን ከዚህ ውስጥ ጥቃት የደረሰበት 420 ሺህ ሄክታር መሬት ገደማ ነው” ብለዋል። “የበረሃ አንበጣውን አሁን ባለበት ደረጃ ካስቆምነው ዘንድሮ ቢያንስ 35 ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ ምርት እናመርታለን ብለን ነው የምንጠብቀው” ሲሉም አክለዋል። 

የጎርፍ አደጋን በተመለከተ መንግስታቸው አደጋውን ለመከላከል የተሻለ ዝግጅት አድርጎ እንደነበር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጥቃት ያደርሳል የሚል ስጋት ነበር። 600 ሺህ ሰው ገደማ ተጠቅቷል። ከዚህ ውስጥ 220 ሺህ ሰው ተፈናቅሏል” ሲሉ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። “የጎርፍ አደጋው ባለፉት 20 እና 30 አመታት ካጋጠመው በላይ በጣም ከፍተኛ ነበር” ያሉት አብይ “ነገር ግን አንድም ሰው አልሞተብንም” ሲሉ ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)