የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮሮና ምርመራ ውጤት እንደማይቀበል አስታወቀ። አየር መንገዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከሆስፒታሉ ከኮሮና ነፃ መሆናቸውን የሚገልጽ የምርመራ ውጤት ያቀረቡ መንገደኞች በቻይናዊቷ ከተማ ሻንጋይ ከደረሱ በኋላ በበሽታው መያዛቸው በመረጋገጡ ነው።
ከአዲስ አበባ ወደ ሻንጋይ በሳምንት አንድ ቀን በረራ የሚያደርገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ካጓጓዛቸው መንገደኞች ውስጥ የተወሰኑቱ የኮሮና በሽታ ስለተገኘባቸው ወደ ከተማይቱ የሚያደርገውን በረራ እንዲያቋርጥ መታዘዙ ቀደም ብሎ ተሰምቶ ነበር። የቻይና ጋዜጦች ትላንት እንደዘገቡት ለአየር መንገዱ በረራ መታገድ ምክንያት የሆኑት 15 በኮሮና መያዛቸው የተረጋገጠ መንገደኞች ወደ ሻንጋይ የተጓዙት ባለፈው መስከረም ወር መገባደጃ እና በጥቅምት ወር መጀመሪያ ነበር።

የመንገደኞቹን የምርመራ ውጤት ተከትሎ፤ የቻይና የበረራ ቁጥጥር ባለስልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሻንጋይ የሚያደርጋቸውን በረራዎች ለአምስት ሳምንታት አግዷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ይህ ትዕዛዝ እንደደረሰው አረጋግጧል።
“ከአዲስ አበባ ወደ ሻንጋይ የምናደርጋቸውን በረራዎች እንድናቋርጥ ከቻይና ባለሥልጣናት ትዕዛዝ እንደደረሰን ለክቡራን ደንበኞቻችን ማሳወቅ እንፈልጋለን” ያለው አየር መንገዱ “በረራዎቻችንን መልሶ ለመጀመር በጉዳዩ ላይ ከቻይና ባለስልጣናት ጋር እየተወያየን ነው” ብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትላንት መግለጫው እንዳለው፤ ከዚህ በኋላ ለእገዳው ምክንያት ከሆነው የሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮሮና የምርመራ ውጤት አይቀበልም። “ከሆስፒታሉ የሚቀርቡ የፒሲአር የምርመራ ውጤቶችን ስለማንቀበል ደንበኞቻችን በተጠቀሰው ሆስፒታል ምርመራ እንዳያደርጉ እናሳውቃለን” ሲልም አየር መንገዱ ደንበኞቹን አሳስቧል።
ሆስፒታሉ ከአምስት ቀናት በፊት በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው አጭር መልዕክት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የጉዞ ሰርተፍኬት ማቅረብ ማቆሙን ገልጿል። ይኸው መግለጫ እንደሚለው “ሆስፒታሉ ወደ ቻይና በየትኛውም አየር መንገድ ለሚጓዙ የጉዞ ሰርተፍኬት አያቀርብም።”
የሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮሮና ምርመራ ማድረግ የጀመረው ባለፈው መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሆነ በፌስቡክ ገጹ የተሰራጨ መረጃ ይጠቁማል። የሆስፒታሉ ደንበኞች አገልግሎቱን ለማግኘት ፓስፖርት እና ቪዛ፤ ዋናውን ከአንድ ቅጂ ጋር ማቅረብ አለባቸው። የህክምና ተቋሙ ለኮሮና ምርመራው በግለሰብ 15 ሺህ ብር ያስከፍላል።
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ሥራ የጀመረው ሲልክ ሮድ አጠቃላይ ሆስፒታል፤ የቻይና እና አፍሪካ ወዳጅነት ለማጎልበት ከታለሙ ፕሮጀክቶች አንዱ እንደሆነ በተቋሙ ድረ ገጽ የሰፈረው መረጃ ያመለክታል። በቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የተጠነሰሰው የ“ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ” ማመለካቻ ነው የተባለለት ይህ ሆስፒታል ለግንባታው ብቻ 920 ሚሊዮን ብር መፍጀቱ ተነግሮለታል። የራሱን ባለ 14 ፎቅ ህንጻ ያስገነባው ይህን ሆስፒታል በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ኤ ኤፍ ኢ አይ በተባለ የቻይና ኩባንያ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)