የመከላከያ ሰራዊት በሕወሓት ላይ እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመከላከያ ሰራዊት በሕወሓት ላይ እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙን አስታወቁ። ለሰራዊቱ ትዕዛዝ የተላለፈው በትግራይ ክልል በሚገኘው ካምፑ ላይ ጥቃት ከተሰነዘረበት በኋላ እንደሆነም ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ማክሰኞ ጥቅምት 24 ከለሊቱ ሰባት ገደማ በይፋዊ ፌስቡክ ገጻቸው ባሰራጩት አጭር መግለጫ ነው። ከለሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ በ“ሰበር ዜና” በብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ በተደጋጋሚ በተላለፈው በዚህ መግለጫ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕወሓት “ጦርነት ከፍቷል” ሲሉ ወንጅለዋል። 

ጦርነት የተጀመረበት ቦታ “ዳልሻሕ” በሚባለው አካባቢ በኩል መሆኑ ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል” ብለዋል። የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት አብይ ሕወሓት “የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነስቷል” ሲሉ ከስሰዋል። የሰራዊቱን የሰሜን ዕዝ ለመዝረፍ “ሙከራ አድርጓል” ሲሉም አክለዋል።  

“መንግሥት የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ በማሰብ፣ ጦርነት እንዳይፈጠር የትእግሥቱ ጫፍ ድረስ ታግሷል” ሲሉ በመግለጫቸው ያሰፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጦርነት የሚቀረው ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ አይደለም” ብለዋል። መንግስታቸው ኃይልን “በመጨረሻ አማራጭነት” መጠቀም የጀመረው “ሀገር እና ሕዝብን ለማዳን ሲባል” መሆኑንም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።  

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ከመሰማቱ ሰዓታት በፊት ለመደበኛ ስብሰባ ተቀምጠው የነበሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ሕወሓትን ጨምሮ “የጥፋት ኃይሎች” በጠሯቸው አካላት ላይ፤ መንግስት “የማያዳግም ርምጃ መውሰድ እንዳለበት” ጠይቀው ነበር። ጠንከር ባሉ ቃላት እና በእምባ ጭምር በታጀበው የምክር ቤቱ አባላት አስተያየት ላይም መንግስት እነዚህን ኃይሎች በአሸባሪነት እንዲፈረጅም ሀሳብ ቀርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)